Saturday, 24 January 2015 11:54

ሰዓሊ ጁሊ ምህረቱ የአሜሪካ የሥነ-ጥበባት ሜዳሊያን ተቀበለች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

“የስዕል ስራዎቿን ለእይታ በማብቃታችን ኩራት ይሰማናል”
                           - የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ
 
ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ሰዓሊ ጁሊ ምህረቱ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በአለማቀፍ ደረጃ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የስነ-ጥበባት ባለሙያዎች በየአመቱ የሚሰጠውን የ2015 የስነ-ጥበባት ሜዳሊያን ተቀበለች፡፡ኢትዮ- አሜሪካዊቷ ሰዓሊ ጁሊ ምህረቱ በአለማቀፍ ደረጃ እውቅና በተሰጠው የስነ-ጥበብ ስራዋ እና ባህላዊ ዲፕሎማሲን በማጠናከር ረገድ በፈጠረችው ተጽዕኖ ለዚህ ሽልማት መብቃቷን የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡የመስሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ለአርት ኒውስ ድረገጽ እንደተናገሩት፣ ሰዓሊዋ በሙያዋ ላሳየችው ጉልህ ቁርጠኝነት እንዲሁም አርት ኢን ኢምባሲስ በተሰኘው ፕሮግራምና በአለማቀፍ የባህል ልውውጥ መስክ ላበረከተችው አስተዋጽኦ እውቅና ለመስጠት፣ የዘንድሮውን ሽልማት ከተቀበሉት 7 ሰዓሊያን አንዷ ተደርጋ ተመርጣለች፡፡እ.ኤ.አ በ1970 በአዲስ አበባ የተወለደችው ሰዓሊ ጁሊ ምህረቱ፤ በተለያዩ የውጭ አገር ዩኒቨርሲቲዎች የስነጥበባት ትምህርቶችን የተከታተለች ሲሆን፣ በአለማቀፍ ደረጃ በተዘጋጁ በርካታ የግልና የጋራ የስዕል አውደ ርዕዮች ላይ ስራዎቿን ለእይታ በማብቃትና የታላላቅ ሽልማቶች አሸናፊ በመሆን ትታወቃለች፡፡ በአሁኑ ሰዓትም ነዋሪነቷ በአሜሪካ ኒውዮርክ ነው፡፡የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጆን ኬሪ በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የጁሊ ምህረቱን ስዕሎች በተመለከተ በሰጡት አስተያየት፣ በተለያዩ አገራት በሚገኙ ኤምባሲዎቻችን ለእይታ ያበቃናቸው የጁሊ ስዕሎች እጅግ ማራኪ ናቸው፣ በስራዎቿ ኩራት ይሰማናል ብለዋል፡፡ ላበረከተችው አስተዋጽኦም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

Read 1878 times