Saturday, 24 January 2015 12:01

በ100 ሚ. ብር የተመሠረተው “ባምቡ ስታር አግሮ ፎርስትሪ” አለም አቀፍ እውቅና አገኘ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(4 votes)

ፈረንሳዩ ኤርባስ የአውሮፕላኖቹን የውስጥ ክፍል ከቀርከሃ ለማሰራት ከፋብሪካው ጋር ንግግር ጀምሯል
በየአመቱ 500ሺ የቀርከሃ ችግኞችን በማፍላት ለአርሶ አደሮች ያከፋፍላል
           ለ24 ዓመታት በአሜሪካ በቆዩት አቶ ሚካኤል ገብሩ በቤኒሻንጉል የተቋቋመው “ባምቡ ስታር አግሮፎርስትሪ” የተሰኘ የቀርከሃ አምራች ኩባንያ ሰሞኑን “ልዩ ሃሳብ” በማፍለቅ አለም አቀፍ እውቅና አገኘ፡፡ የፈረንሳዩ ኤርባስ የአውሮፕላኖቹን የውስጥ ክፍል ከቀርከሃ ለማስራት ከኩባንያው ጋር ንግግር መጀመሩም ተገልጿል፡፡ ግለሰቡ በ1999 ዓ.ም ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ በ60 ሚሊዮን ብር ያቋቋሙት ይህ የቀርከሃ ፋብሪካ 400ሺህ ሄክታር መሬት በሊዝ ካገኙ በኋላ የቀርከሃ ችግኝ ከማፍላት ጀምሮ የሚሰራ ሲሆን፤ ከቀርከሃው የሚያመርታቸውን ምርቶች የሚሰራበት ፋብሪካው ደግሞ በ6ሺህ ስኩየር ካሬ ሜትር ላይ ማረፉን የፋብሪካው መስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሚካኤል ገብሩ ተናግረዋል፡፡ በጋራ ልዩ የቢዝነስ ሃሳብ አመንጪ የአፍሪካ ስራ ፈጣሪዎች በሚል ሰሞኑን ሮይተርስና ኤቢሲባዘጋጁት ፕሮግራም ላይ “Promissing African Entrepreuners Developed Unique Business Ideas In 2014” በሚል ከተመረጡ አራት የአፍሪካ ኩባንያ አንዱ ድርጅታቸው መሆኑን በዜና እንደሰሙ የተናገሩት ባለቤቱ፤ ሰሞኑን ሽልማታቸውን ለመቀበል ወደ ውጭ እንደሚሄዱም ተናግረዋል፡፡ በ60 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተመሰረተው ኩባንያ ለማስፋፊያ 40 ሚሊዮን ብር ተጨምሮበት ካፒታሉ ወደ መቶ ሚሊዮን ብር ማደጉን ባለቤቱ ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም ከቻይናና ከሳዑዲ ባለሀብቶች ጋር የስራ ስምምነት ተደርጐ፣ የወረቀት ፋብሪካ በመከፈት ላይ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ሚካኤል፤ የቀርከሃ ጉዳይ በመንግስት በኩልም ትኩረት አግኝቶ ገፈርሳ አካባቢ ባምቡ ኢንስቲትዩት ሊከፈት ዝግጅቶች ተጠናቀዋል ብለዋል፡፡ በቅርቡ ከ50-60 ሚሊዮን ብር ብድር ከልማት ባንክ ከተገኘ፣ ባምቡ ስታር ፎረስትሪ በሙሉ አቅሙ ለመስራትና እቅዱን ለማሳካት እንደሚጥርም የኩባንያው ባለቤት ተናግረዋል፡፡

Read 2590 times