Saturday, 24 January 2015 12:23

የታክስ ፖሊሲና ህጐች መሻሻል አለባቸው ተባለ

Written by 
Rate this item
(8 votes)

           በኢትዮጵያ ተግባራዊ በመደረግ ላይ የሚገኙት የታክስ ፖሊሲዎችና ህጎች ከወቅታዊ አለማቀፍና አገራዊ ሁኔታዎች ጋር ተገናዝበው መሻሻል እንደሚገባቸው የፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ (የማህበራዊ ጥናት መድረክ) ጥናት  አመለከተ፡፡በመድረኩ አዘጋጅነት “የኢትዮጵያ የታክስ ፖሊሲና ህጐች ቅኝት” በሚል ርዕስ መድረኩ ያቀረበው ጥናታዊ ፅሁፍ እንደጠቆመው፤ የአገሪቱ የገቢ ግብርና የቫት ህጎች ከአስር አመት በላይ ያስቆጠሩ ቢሆኑም ጉልህ የማሻሻያ ለውጥ አልተደረገባቸውም፡፡ ከወር ደሞዝ ታክስ የማይከፈልበት 150 ብር ወይም ከአመት ገቢ 1800 ብር እንዲሆን ከአመታት በፊት የወጣው ህግ ከብር የመግዛት አቅም መሸርሸርና ከዋጋ ንረት ጋር ተያይዞ ከመጡ ለውጦች ጋር ተገናዝቦ አልተሻሻለም፡፡ አላግባብ ከፍተኛ የታክስ ክፍያ የተጣለባቸው ድርጅቶች ጉዳያቸው እንዲመረመር አቤቱታ ማቅረብ ከፈለጉ፣ በቅድሚያ ግማሽ ያህሉን ክፍያ እንዲፈፅሙ እንደሚገደዱና ለአቤቱታቸው ምላሽ ለማግኘት ረጅም ጊዜ እንደሚንገላቱ የጠቆመው ጥናቱ፤ ብዙውን ጊዜም የሚያገኙት ውሳኔ ፍትሀዊ  እንዳልሆነ ይነገራል ብሏል፡፡ የታክስ ኦዲትን አስመልክቶም የታክስ ኦዲት የሚደረገው ከ4 እና ከ5 አመት በኋላ ስለሆነ የተጠራቀመ የታክስ እዳ እንዲከፍሉ የሚወሰንባቸው ድርጅቶች ከፍተኛ ወለድም ጭምር እንደሚጫንባቸው ጥናቱ ገልጿል፡፡የንግድ ድርጅቶች የ‹‹ሀ›› ምድብ፣ የ‹‹ለ›› ምድብ በሚል የሚፈረጁበት አመታዊ የሽያጭ ገቢ  በዋጋ ንረት ሳቢያ የብር የመግዛት አቅም ተሸርሽሮ ሽያጫቸው ላይ ጭማሪ ቢያሳይም ህጉ ግን እንዳልተሻሻለም በጥናቱ ተጠቅሷል፡፡የ‹‹ሐ›› ምድብ ተብለው በሚፈረጁትና አመታዊ ሽያጫቸው እስከ 100 ሺህ ብር  በሆኑ ድርጅቶች ላይ የሚደረገው የታክስ ክፍያ አወሳሰንም ውስብስብና በግምት ላይ የተመሰረተ ነው ብሏል፡፡
ብዛት ያላቸው መመሪያዎች በስራ ላይ መዋላቸው በታክስ ከፋዩና አንዳንድ ጊዜም በግብር ሰብሳቢ መስሪያ ቤቱ ባለሙያዎች ግራ አጋቢ እንደሚሆኑ ያመለከተው ጥናቱ፤ በተለያዩ የግብር መሰብሰቢያ ቢሮዎች ወጥ የሆነ መረጃ ያለመኖር እንዲሁም  ባለሙያዎችም መረጃዎቹን የሚረዱበት አግባብ ወጥ አለመሆኑ እንዲሁም በህጉ ላይ የተቀመጠውና በተግባር የሚታየው የተለያዩ መሆናቸው እንደችግር ተጠቅሰዋል፡፡ጥናቱ በታክስ ፖሊሲና ህጎች ዙሪያ መሻሻል ያለባቸውን ነገሮች ያስቀመጠ ሲሆን በአጠቃላይ ግን በአገር ውስጥና በአለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ለውጦችን ግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚኖርበት ተጠቁሟል፡፡
 “ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ” (የማህበራዊ ጥናት መድረክ) በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ጥናትና ምርምር እንዲሁም ሕዝባዊ ውይይቶችን የሚያካሂድ መንግስታዊ ያልሆነ አገር በቀል ድርጅት ነው፡፡

Read 2977 times Last modified on Saturday, 24 January 2015 15:20