Saturday, 24 January 2015 12:37

ኢትዮጵያ የነቃችና የበቃች ሉዓላዊት አገርም ጭምር ናት!

Written by  እስጢፋኖስ በፍቃዱ
Rate this item
(0 votes)

ጥንታዊውን ስልጣኔ ለማሻሻል በመጀመርያ ስልጣኔውን ማክበር፣ ማቆየት፣ መጠበቅና መጠቀም ያስፈልጋል፡፡

        ባለፈው ሳምንት አዲስ አድማስ ጋዜጣ በነፃ አስተያየት አምዱ፣ ዮሐንስ ሰ. በተባሉ ግለሰብ ፀሐፊነት “እውን ኢትዮጵያ ልዩና ድንቅ አገር ናት?” በሚል ርዕስ ያወጣውን ሸንቋጭ ጽሑፍ ካነበብኩ በኋላ፣ ከፀሐፊው ጋር ያለኝን የሃሳብ ልዩነት ለማስቀመጥ ወደድኩ፡፡
ፀሐፊው በሉዐላዊነትና በምዕራባውያን አስተምህሮ ሊያጠምቁን በሞከሩበት ፅሁፋቸው፣ ለገና በዓል በተዘጋጀው የቲቪ ፕሮግራም አቶ ዳንኤል ክብረትና አቶ ውብሸት ወርቃለማሁ፣ በምዕራባውያን ባህል መወረራችንንና የሀገራችን ባህል እየተሸረሸረ መሆኑ አሳስቧቸው ያደረጉትን በቁጭት የተሞላ ንግግር ነው መነሻ ያደረጉት፡፡
“…ሸማ፣ የሳር ጐጆ፣ የበሬ እርሻ፣ እንስራ የመሳሰሉ ከሺ ዘመናት በፊት በታላቅ የፈጠራ ባህል አማካኝነት የተፈለሰፉና ከትውልድ ወደ ትውልድ በልማድ የወረስናቸውን ነገሮች እንደታቀፍን ቆመን እንደቀረንና ደንዝዘን እንደተቀመጥን…” ፀሃፊው ይነግሩናል፡፡
ለማድረግ ያልቻልነውን ነገር ሲገልፁም፤ “ከሸክላ ቴክኖሎጂ በተጨማሪ የብረት፣ የፕላስቲክ ቴክኖሎጂ መፈልሰፍ፣ ከጠላና ጠጅ አልፈን የወይን ጠጅና የቢራ ፋብሪካ መፍጠር አልቻልንም” ይሉናል፡፡ ዮሐንስ ሰ. ባነሱት ሃሳብ ላይ ያለኝን የተቃውሞ ሀሳብ እንዲያንጸባርቅልኝ ሶስት ሃይለ ቃላትን በማስቀመጥ እነሱን እያብራራሁ ልቀጥል
1ኛ - ጥንታዊውን ስልጣኔ ለማሻሻል በመጀመርያ ስልጣኔውን ማክበር፣ ማቆየት፣ መጠበቅና መጠቀም ያስፈልጋል፡፡
ማለቴ … ከዘመናት በፊት በነበረው ስልጣኔ የተፈለሰፈውን ግኝት አክብረን ስናቆየውና ስንጠብቀው ነው ዛሬ ላይ ልንጠቀምበት የምንችለው፡፡ ያቆየነውን ደግሞ ስንጠቀምበት ነው ክፍተቶቹንና ችግሮቹን ልንለይ የምንችለው፡፡ ችግሮችን ከለየንና በጉድለቶቹ ምክንያት መጎዳታችን በግልጽ ሲታወቀን፣ ያኔ መፍትሄዎችን ወይም የተሻሻሉ ግኝቶችን እንፈጥራለን ማለት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር አክብሮ ማቆየት፣ መጠበቅና መጠቀምን፤ መጠቀም ደግሞ፤ ችግሮችን መለየትን፤ ከዚያም ችግር ብልሀትን ይወልዳል ማለት ነው፡፡
እዚህ ላይ እንኳን ልናሻሽላቸው በወጉ ከአባቶች ተቀብለን ልንጠቀምባቸውም ያልቻልናቸውን በባህል ወረራው የተነሳ እንደ ኪነ-ህንፃ፣ ስነ ክዋክብትና ህክምና ያሉ ጥንታዊ ኢትዮጵያዊ ጥበቦች ስናስብ፣ ሁለቱ ታዋቂ ኢትዮጵያውያን፤ ቀደምት ስልጣኔንና ባህልን የማቆየት የመጠበቁ ሃሳብ ላይ ሙጥኝ የማለታቸውን ተገቢነት እንረዳለን፡፡
2ኛ - ካላሻሻልነው አላስፈለገንም ማለት ነው፡
ዮሐንስ ሰ. በዚሁ ጋዜጣ ላይ ከዚህ ቀደም በታተመ ፅሁፋቸው፤ በንፋስ ሀይል የሚመነጭ የኤሌክትሪክ ኃይል ከውሃ አንፃር ውድ ስለሆነ ገና ለገና “የሰለጠኑት” አገሮች ስለተጠቀሙበት ብቻ በሚል ሀብት መባከን የለበትም፤ ቴክኖሎጂውም አያስፈልገንም እያሉ ሲሟገቱ ነበር፡፡ የዚህ ሙግታቸው አመክንዮ ‘ለአንድ ሀገር ስራ ላይ የሚውሉ ቴክኖሎጂዎች በሀገሪቱ ምድር ላይ ያሉ ሁኔታዎችን ያገናዘቡ ሊሆኑ ይገባል’ የሚል እንደሆነ አልጠራጠርም፡፡
 ታድያ ይሄንን ውሃ የሚያነሳ መከራከርያ ለሳምንቱ ጽሁፋቸው ማጠንጠኛ ለማድረግ ለምን አልፈለጉም ወይም አልቻሉም?
የአንድ ማህበረሰብ የስልጣኔ ወይም የለውጥ ፍላጎት ከራሱ ከማህበረሰቡ ነው የሚመነጨውና ሊመነጭም የሚችለው፡፡ የአንድ ማህበረሰብ ችግርም በራሱ በማህበረሰቡ አረዳድ የተወሰነ እንጂ እኔ አውቅልሃለሁ በሚል ሌላ አካል ሊወሰን አይገባም፡፡ ማህበረሰቡ ያሉበትን ችግሮች በመፍታት ሂደት አዳዲስ ግኝቶችን ሊፈጥር ወይም ያሉትን ሊያሻሽል የሚችለው ከችግሩ አስገዳጅነት በሚመጣ ተፈጥሯዊ ግፊት ነው፡፡
(“ችግር ብልሀትን ይወልዳል” እንደሚለው ነው ጥንታዊው ሀበሻ፡፡) ፈረንጆቹም “NECESSITY IS THE MOTHER OF INNOVATIONS” ይላሉ፡፡ /የእነሱ ነገር በአንድ በኩል የነፃ አስተሳሰብ አራማጅ ነን እያሉ፣ በሌላ በኩል የእኔ አውቅልሃለሁ አቀንቃኝ ሆነው ይገኛሉ እንጂ!
እኛ ኢትዮጵያውያን ከሺ ዓመታት በፊት የነበሩት አባቶቻችን የፈጠሩትን ጠቃሚ ነገሮች ጠብቀን አቆይተን እስከ ቅርብ ጊዜም (የባህል ወረራው በእጃችን ያለውን አጣጥሎብን የምዕራባውያንን ግሳንግስ ናፋቂ እስካደረገን ቀን ድረስ) ስንጠቀምባቸው ቆይተናል፡፡ ታድያ ከተጠቀምንባቸው ለምን አላሻሻልናቸውም? መልሱ በጣም ግልፅ እና አጭር ነው - ማሻሻል ስላላስፈለገን፡፡
እስቲ አስቡት … የሸማን ጥበብ ወዴት እናሳድገው? ወደ ሻማ? ከሸማ ወደ ሻማ? ቁልቁል ወደ ቴትሮን? ወደ ናይለን …ከዚያ ደግሞ 100% ጥጥ ፍለጋ መኳተን፡፡ እውነቴን እኮ ነው፡፡ እራሳችን ከአቅራቢያችን የተመረተውን ጥጥ በየቤታችን ፈትለን፣ ደውረንና ሸምነን ለሰውነት ተስማሚና ምቹ የሆነውን የጥበብ ልብስ መልበሱ ሳይጎረብጠንና ሳይረብሸን ሰው ስላደረገ ነው የምናሻሽለው ወይስ ለምን? ሌሎቹም ግኝቶች እንዲሁ ናቸው - አብዛኞቹ በቀላሉ በአቅራቢያችን የሚገኙ ወጪ ቆጣቢና ለከባቢ አየር ተስማሚ (friendly) ናቸው - ልክ እንደ የውሃ ግድብ ኃይል ማመንጫዎቹ፡፡ አቶ ዮሐንስ ሰ. በሸንቋጭ ፅሁፋቸው ጠላና ጠጅ ወደ ቢራ ፋብሪካ ማደግ እንደነበረባቸው ጠቁመውናል፡፡ ቢራ ፋብሪካ በቤት ውስጥ ከሚጠመቀው ጠላ ወይም ጠጅ የተሻሻለ መሆኑ ነው እንግዲህ እንደሳቸው አባባል፡፡ እንደመግዛትና እንደመጠጣት አቅማችን እያየን በየቤታችን ጠምቀንና ጥለን ከጉሽ እስከ ፊልተር፤ ከከረመ እስከ የተላሰ አማርጠን መጎንጨት እየቻልን ለምንድነው የተወሰኑ ካፒታሊስቶችን ብቻ ሊጠቅም የሚችል ፋብሪካ ከፍተን (ተከፍቶብን) ምላሳችን ካልለመደው ጎምዛዛ ቢራ ጋር በተፅዕኖ የምንጋተረው?
የገና ጨዋታንም መውሰድ ይቻላል፡፡ በነገራችን ላይ ዮሐንስ ሰ. አጣጥለው እንዳቀረቡት የገና ጨዋታ መሯሯጥ ብቻ አይመስለኝም፡፡
የማራኪ ስፖርታዊ ጨዋታ መለኪያ ብለው ያቀረቡትም ምንም እንኳን ከኛ አንፃር የወጣ መለኪያ መሆኑ ቢያጠራጥርም የገና ጨዋታ ግን ሁሉንም የሚያሟላ ነው፡፡ የስፖርተኛው የአካልና የአእምሮ ብቃት የእንጨት ኳሱን ይዞ እየተታለለ ለመሮጥ በሚያደርገው ጥረት የሚለካ ሲሆን ለተመልካች አመቺነት ለሚለው ደግሞ ጨዋታው ከጎልፍና በተለይም ከማራቶን በተሻለ ለተመልካች አመቺ መሆኑ እሙን ነው፡፡
አቶ ዳንኤል ክብረት እንዳሉትም፤ የገና ጨዋታን ከገና በዐል ቀደም ብለን ጀምረን ፍፃሜውን የበዐሉ እለት አድርገን ብንጫወትና ከጨዋታው ሊገኙ በሚችሉ ጥቅሞች ሁሉ ብንጠቀም ደግሞ ማለፊያ ነው የሚሆነው፡፡ ምክንያቱም ስንጠቀምበት ነውና ክፍተቶቹን አይተን ልናሻሽለው የምንችለው፡፡ ተጠቅመንበት ካላሻሻልነው በበቂ አዝናንቶናል ማለት ነው፡፡ አራት ነጥብ፡፡
3ኛ - ወገኛ ነገር - የዮሐንስ ሰ. ነገር ወይስ የእኛ ነገር?
“… በአዲስ አበባ የሚኖር ደራሲ፣ ዘፋኝ ሙዚቀኛ ወይም ጋዜጠኛ ወደ ቆላማው አካባቢ … የሀመር ተወላጆች ወደሚኖሩበት ሄዶ አኗኗራቸውን ሲያደንቅ፣ ከተሜነትን ሲያንቋሽሸው ይቆይና ወደየከተማ ኑሮ ለመመለስ ይሮጣል፡፡” ይላሉ ዮሐንስ ሰ. በዚሁ ጽሁፋቸው፡፡ አትፍረዱባቸው፡፡ እርሳቸው ይህን ፅሁፍ የጻፉት በስጋና በአእምሮ ሆነው፣ እንደ ጥበበኞቹ እንደ ፍቅረማርቆስ ደስታ ወይም የጎሳዬን ኢቫንጋዲ ዜማ እንደ ፃፈ ደራሲ አሊያም ደግሞ እንደ ጥልቅ አሳቢዋ ድምፃዊ እጅጋየሁ ሽባባው በነፍስ ሆነው አይደለም ጉዳዩን ያጤኑት፡፡
ዮሐንስ ሰ. የወገኛ ነገር ሆኖባቸው ስልጡንና ዘመናዊ ለመባል (ታድያ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?) ከላይ የቀነጨብኳትን አንቀፅ በፅሁፋቸው ከማካተታቸው በፊት የሚከተሉትን ጥያቄዎች እራሳቸውን ጠይቀው ቢሆን መልካም ነበር፡፡
ጠቢባኑ ለምን ይዋሻሉ? የዕለት እንጀራዋን ያሸነፈችውና ሙያዊ ነጻነቷን ያወጀችው ጂጂ፤ ናፈቀኝ እያለች የገጠሩን ህይወት ስታዳንቅና ‘ደህና ሁን ከተማ’ እያለች የከተሜን ህይወት ስታጣጥል ለነፍሷ የተገለጠላት አንዳች እውነት ከውስጧ ፈንቅሏት ካልሆነ በቀር ሌላ ምን ምክንያት ይኖራታል? እኛስ ታዳሚዎቹ እነኚህን የጥበብ ስራዎች ስንሰማ ወይ ስናነብ አንዳች ነገር ወደ ገጠሩ “ሂድ ሂድ/ ሂጂ ሂጂ” የሚለን ለነፍሳችን አንዳች የጥሪ ደወል ማቃጨል ቢችሉ እንጂ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? ታድያ ለምን ’ሂዱ ሂዱ’ የሚለንን ስሜት ተከትለን ወደ “አልሰለጠነው” ገጠር አልሄድንም? ካሉኝ ደግሞ ለዮሐንስ ሰ. አንድ ጥያቄ አለኝ፡- ገነት ለመግባት ሁሉም ይፈልጋል፤ ሁሉም ሊገባ ግን ይቻለዋል?
“ስልጡኑና ዘመናዊው” ዮሐንስ ሰ. እንዲህም ብለዋል፡፡ “… እንዴት ልብስ አለመልበስ እንደ ስልጣኔና እንደ ባህል ይቆጠራል? ባህል ማለት እኮ በሰፊው ስር ለመስደድ የበቃ የፈጠራ ውጤትና ስኬት ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ ልብስ መስራት እና መልበስ፡፡
እኔ ደግሞ እንዲህ እላቸዋለሁ …
ልብስ አለመልበስ እንደ ስልጣኔና እንደ ባህል ላይቆጠር ይችላል፤ ነገር ግን ምድር ካፈራቻቸው ልዩ ልዩ ተፈጥሯዊ ንጥረ ነገሮች የተቀመመ ሽቱ፣ እጣን፣ የጭቃ ቅባት ሰውነትን አስውቦ፣ በላዩ ላይ ደግሞ በልዩ እደ ጥበባዊ ክህሎት የተሰሩ የእግርና እጅ ጌጦች በራቁት ገላ ላይ ደርቦ ልብስ ሳይለብሱ፣ ልብስ ከለበሰው በላይ ውብና ጨዋ ሆኖ መታየት ባህልና ስልጣኔ ካልተባለ እራሱ ስልጣኔ ምንድነው?
ማጠቃለያ
የኢትዮጵያ ጥንታዊ ስልጣኔ ምሉዕ ነው፡፡ ከልዩ ልዩ ወረራዎችና ዝርፊያዎች ተከላክለንና ተንከባክበን ልናቆየው ብቻም ሳይሆን ልንጠቀምበትና ለልጅ ልጅም ልናስተላልፈው እንችላለን፡፡
ስልጣኔውና ባህሉ በራሱ አስገዳጅ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ የመለወጥና የመሻሻል ተፈጥሯዊ ባህሪ ስላለው ለመሻሻል ነጋሪ አይፈልግም፡፡ ካልተሻሻለ አላስፈለገውም ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ይህቺ ሀገር ልዩና ድንቅ ብቻ ሳትሆን የበቃችና የነቃች ሉዓላዊት ሀገር ነችና!

Read 2909 times