Saturday, 24 January 2015 12:38

“ዋና የማይችል ባህር አይግባ፤ ትግል የማይችል ልፊያ አይውደድ”

Written by 
Rate this item
(15 votes)

አንድ አፈ-ታሪክ እንዲህ ይላል፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት ውብ ልዕልት ነበረች አሉ - ሁሉም የሚያደንቃት ናት፡፡ ግን ማንም ላግባሽ ያላት የለም፡፡ ንጉሡ አባቷ ተስፋ በመቁረጥ አፖሎ የተባለው አምላክ ዘንድ ሄደና አማከረው፡፡ አፖሎም፤ ሳይክ (Psyche) ልዕልቲቱ ወደ ተራራ መውጣት አለባት፡፡ የሐዘን ልብስም ትልበስ፡፡ እዚያም ብቻዋን ትተው፡፡ ቀኑ ከመንጋቱ በፊት አንድ እባብ ይመጣል፡፡ ያገኛታል፡፡ ያገባታልም፡፡”
ንጉሱ ታዘዘው፡፡ ሌሊቱን ሙሉ ልዕልቲቱ ባሏን ልታይ ስትጠብቅ ቆየች፡፡
የሞት ያህል በሚያስፈራ ሁኔታ ውስጥ በአሰቃቂ ቅዝቃዜ በድና መጠበቋን ቀጠለች! በመጨረሻ እንቅልፍ ወሰዳት፡፡
ስትነቃ በአንዳች ቆንጆ ቤተ መንግስት ውስጥ ንግሥት ሆና ራሷን አገኘች! በየማታው ባሏ ይመጣል፡፡ ኢሮስ ይባላል፡፡ ይገናኛታል (ፍቅር ይሰራሉ)፡፡ ግን አንድ ቃል ኪዳን አስገብቷታል፡- “ሳይክ፤ የምትፈልጊውን ሁሉ አደርግልሻለሁ፡፡ ግን ፊቴን መልኬን አታይም፡፡ ሳታይኝ ሙሉ በሙሉ ልታምኚኝ! ይገባል፡፡” ወጣቷ ያላትን ፈፅማ ለረዥም ጊዜ በደስታ ኖረች፡፡
ምቾት አላት፡፡ መወደድ አላት፡፡ ደስተኛ ናት፡፡ በየማታው ከሚጎበኛት ሰው ጋር ፍቅር ይዟታል! ግን አንዳንዴ ከእባብ ጋር የተጋባች የተጋባች ይመስላታል! አንድ ጧት ማለዳ ላይ፤ ባሏ ተኝቶ ሳለ ፋኖሱን ለኮሰችና ባሏን ኢሮስን መልኩን አየችው፡፡ ወደር የሌለው ቁንጅና ያለው ወንድ ነው፡፡ ከጎና ተኝቷል፡፡ የፋኖሱ ብርሃን ቀሰቀሰው፡፡
ያፈቀራት ሴት፤ አንድዬ አደራውን አለማክበሯን አይቶ ኢሮስ ላንዴም ለሁሌም ተሰወረ፡፡ ልዕልቲቱ ባለ በሌለ ኃይሏ ፍቅረኛዋን ዳግም ለመመለስ ስትፍረመረም አፍሮዳይት የተባለች የባሏን እናት አግኝታ ጥፋቷን አምና ለመነቻት፡፡ ከእንግዲህ ብዙ ልትፈፅማቸው የሚገቡ ነገሮች እንዳሉ አውቃ፣ ተቀብላ ልትኖር ቃል ገባች፡፡
ምራቷ ግን በልዕልት ውበት ቅናት ይዟት ኖሮ፤ የሁለቱን ፍቅረኞች ዳግም መገናኘት ለመቀልበስ/ ለማነቀፍ ያልፈነቀለችው ድንጋይ አልነበረም፡፡ ልዕልት ሳይክ፤ በተቀበለችው የቤት ስራ መሰረት አንድ ሳጥን ከፈተች፡፡ ለካ ያ ሳጥን ከባድ እንቅልፍ የሚያስወስድ አስማታዊ ሚስጥር ኖሮታል፡፡ ድብን አድርጎ እንቅልፍ ወሰዳት፡፡
መቼም ሳይደግስ አይጣላምና ኢሮስ ደግሞ ከባድ ፍቅር ይዞት ኖሮ እጅግ አድርጐ ተፀፅቷል፡፡ እንደምንም ብሎ ወደ ቤተመንግስቱ ህንፃ ገብቶ ሚስቱን በቀስቱ ጫፍ ጭሮ ቀሰቀሳት፡፡ “በማወቅ ጉጉትሽ ምክንያት ሞት አፋፍ ደርሰሽ ተመለስሽ” አላት፡፡ ዕውቀት ስር መጠለል ሽተሽ ግንኙነታችንን ገሥሠሽ አጠፋሽ! ቃልኪዳንሽን ሰበርሽ! ሆኖም በፍቅር ዓለም ምንም ነገር ለዘለዓለም አይጠፋም፡፡
ባልና ሚስቱ በዚህ ዕምነት ተይዘው/ተጠርንፈው ወደ ዚዑስ ሄዱ፡፡ ፍቅራቸው ከእንግዲህ እንዳይጠፋ ለመኑ፡፡ ዚዑስ ከብዙ ክርክርና ሙግት በኋላ የአፍሮዳይትን ምክር አገኘ፡፡ ከዚያን ቀን ወዲህ ሳይክ (የአንጎላችን አላዋቂ (unconscious) ግን አመክኖአዊ ወገን) እና ኢሮስ (ፍቅር) በደስታና በተድላ ለዘለዓለም ኖሩ!”
በዚህ ታሪክ መሰረት፤ “ይህንን የማይቀበሉና አስማታዊና ሚስጥራዊ ለሆነው የሰው - ልጅ ግንኙነት ማብራሪያ ለማግኘት የሚሹ ሁሉ፤ እንደሳይክ የህይወትን ምርጥ ክፍል ያጣሉ!” የሚባለው ለዚህ ነው፡፡
ሳይክ፤ በሆዷ እንዲህ አለች፡-
“አንድ ቀን ቤተ መንግሥት ውስጥ እነቃለሁ! የምፈልገው አንድ ነገር፤ ጊዜ ብቻ ነው!”
*          *          *
በዓለማዊው ህይወታችን ሳያዩ ማመን ከባድ ነው፡፡ ባሌ እባብ ሊሆን ይችላል ብሎ መኖርም ከባድ ነው! እርግጥ፤ “አንድ ቀን ቤተ መንግሥት ውስጥ እነቃለሁ” ብሎ ማሰብ ይቻላል፡፡ ግን ድካም አለበት፡፡ በቀስት ተጭሮ እንደመንቃት ቀላል አይደለም፡፡ ቃልኪዳንን መጠበቁን ይጠይቃል፡፡ ለማወቅ ጉጉት ለከት ማበጀትም ይፈታተናል፡፡ በልጦ መገኘትን ጠንቅቆ መቻል እንደው ያለጥረት የሚገኝ፣ ክብሪት እንደመጫርም የቀለለ፣ የዘፈቀደ ነገር አይደለም፡፡ በሀገራችን ተፎካካሪን በልጦ መገኘት እጅግ አዳጋች፣ የቋጥኛማ ተራራ ያህል የማይዘለቅ ችግር ሆኖ ከቆየ ሰነባብቷል፡፡ አንድ ፀሃፊ እንዳለው፤ “እያንዳንዱ ሰው ትንሽ ትንሽ ዘውድ በኪሱ ይዞ ስለሚዞር “ውይይቱም፣ ድርድሩም፣ ፉክክሩም ሌላውን በማጥፋት ወይም በመጥለፍ ላይ የተመሰረተ ይሆንና ጤናማ ጉዞ አይሆንም፡፡ ጥንትም እንደዚያው ነበር፤ አሁንም ቅኝቱን አልቀየረም፡፡ በዚህ ቅኝት ላይ የመከፋፈል ዜማ ሲጨመርበት ለባላንጣ ሲሳይ የመሆን አባዜ ይከተላል፡፡ ማ ለምን ይህን አደረገ? ምን እየተጠቀመብኝ ነው? ብሎ ማሰብ ያባት ነው!
ተፈጥሮውን ማሳየት የሚበጀው / የሚያዋጣው አንዳንዴ ብቻ ነው፡፡ ከተቻለ ቃናውን ዝቅ ማድረግ መማር አለብህ… ስትጀምር ብዙ ሳትጮህ መጀመር ነው፤ አዋጪው፡፡ የውድድር ዘዴ! “ከጥበብ ሁሉ ከባዱ ደደብነትህን መቼ እንደምትጠቀምበት ማወቅ ነው!” ይላሉ አዋቂ ፀሀፍት፡፡ ብዙ ከመንጫጫት፣ ሰብሰብ ብሎ የማሰብ፣ የማስተዋል ክህሎት ሊኖር ይገባል፡፡ ከተመክሮ ሁሉ ጥንቃቄን የሚፈልግ ተመክሮ የትግል ተመክሮ ነው፡፡ አምስት ዓመት ሙሉ ጊዜ ኖሮ በቂ ዝግጅት ማጣት አንድም ንዝህላልነት፣ አንድም አቅለ-ቢስ መሆን ነው ከማለት በስተቀር ምን ትርጓሜ ይኖረዋል? ራስን ለክፍፍል ማጋለጥ፣ የራስን ችግር ራስ አለመፍታት፣ የተፎካካሪን ስልትና ስትራቴጂ አለማስላት፣ የህዝብንና የሀገርን ፍላጐት አለማስቀደም፣ የመንገዶችን ኮረኮንችና ሊሾነት አለመለየት አባዜዎች ሁሌ እንደተፈታተኑን አሉ፡፡ ጠንካራነትን ብቻ ሳይሆን ደካማነትንም መገንዘብ ብልህነት ነው፡፡
”ደካማ ከሆንክ በማታሸንፈው ጦርነት ውስጥ ለክብርህ ብለህ አትዋጋ፡፡ ይልቁንም ማፈግፈግን እወቅ፡፡ ማፈግፈግ ጊዜ መግዛት ነው፡፡ ማገገሚያ ነው፡፡ ቁስልህን ማከሚያና ባላንጣህን ማዳከሚያ ነው፡፡ ቁልፉ ነገር ማፈግፈግን የኅይል ማፍሪያ መሳሪያ ማድረጉ ነው!”
ጉዞን በረዥሙ ማቀድ ሌላው የብልህነት ስልት ነው፡፡ “ዛሬ ካልተሳካ ሞቼ እገኛለሁ” ማለት ቢያንስ የዋህነት ነው! አጓጉል ፍዘትም ስስ ብልት መስጠት ነው፡፡ ፖለቲካ ማመዛዘንን፣ ጊዜ-መግዛትንና ፍጥነትን መሰረት የሚያደርግ “ሸቃባ ሚዛን” ነው ይባላል፡፡ ይሄን ልብ ማለት ግድ ነው፡፡ “ታሪክ ባሸናፊዎች የሚፃፍ ተረት ነው!” የሚባለውንም አለመርሳት ነው፡፡
ታዲያ ፀጋዬ ገ/መድህን በሼክስፒሩ ሐምሌት እንደሚለን፡-
“…ፈጥነህ ጠብ ውስጥ አትስጠም
አንዴ ከገባህበት ግን እጅህ ከባላንጣህ ይቅደም”
የሚለውን ሳንዘነጋ ነው፡፡ ሁሉም መስዋእትነት ይጠይቃል፡፡ መስዋእትነት እንደ ዴሞክራሲ ሁሉ ገጠመኝ አይደለም፡፡ ቀድመው መሰረትና እሳቤ የሚያበጁለት ነው፡፡
“አንተኛም ካላችሁ እንገንድሰው
መኝታ እንደሆነ ቀርቷል ካንድ ሰው!” እያልን የምናላዝንበትም ከቶ አይደለም፡፡ ሂደት ነው፡፡ መቀጠል አለበት፡፡ ዝምታ እንኳ መስዋእትነት የሚጠይቅበት ጊዜ አለ፡፡ ትግል በጥበብ የተሞላ መንገድ ነው! ካልበሰሉ በድፍረት ብቻ የሚወጡት የወጣት ስሜታዊነት ዘመቻ መሆኑ ቀርቷል፡፡ እንደ ፋሽን በወረት የሚያሸበርቁበት የገና ዛፍም አይደለም፡፡ ከጀመሩ በኋላ “ፉርሽ ባትሉኝ!” የሚባልበት ጨዋታም አይደለም! “ሰይ ብል ባንከረባብት” እያሉ ያሹትን የሚያጭዱበት ቁማርም መሆን የለበትም! “አርፋ ስጠኝ”፣ “አቫንስ ስጠኝ” እያሉ የሚጠባበቁበት አይደለም፡፡ ትግል መሰረቱ የፖለቲካ ክህሎት ነው፡፡ ያልተነገረ ያልተሰማ ነገር የለም፡፡ ከአንጃ እስከ ዋና መስመር፣ ከቀኝና ግራ መንገደኛ እስከ አምስተኛ-ረድፈኛ፣ ከውጪ ወራሪ እስከ ውስጥ ቦርቧሪ፣ ከአናርኪስት እስከ ዘውድ-ናፋቂ፣ ከገንጣይ-አስገንጣይ እስከ በታኝ-ከፋፋይ፣ ከጠባብ እስከ ትምክህተኛ፣ ከአኢወማ እስከ ሊግ፣ ከአንጋፋው ፎረም እስከ ብላቴናው ፎረም…” ስርዝ የኔ ድልዝ ያንተ፣ እመጫት የሷ፣ ሆያ-ሆዬ የሰፊው ህዝብ ስንባባል በኖርንበት አገር ትግል “ሁለት አንድ ዐይናዎች ተጋብተው ሁለት ዐይን ያለው ልጅ ወለዱ፡፡ ምነው ቢሉ፣ አንዱን ከእናቱ አንዱን ከአባቱ!” ብለው የሚገላገሉት አይደለም!? “ዋና የማይችል ባህር አይግባ፤ ትግል የማይችል ልፊያ አይውደድ” የሚባለው ተወዶ አይደለም፡፡ እሙናዊውን ዓለም እናጢን! ሁሌ ልጅ አንሁት - ልብ-እንግዛ!!


Read 7661 times