Saturday, 24 January 2015 12:46

የጉዞ ማስታወሻዬ

Written by  ነቢይ መኮንን-
Rate this item
(3 votes)

ከውሃ ወደ ውሃ - ከአሶሳ ወደ ካይሮ

         (ካለፈው የቀጠለ)
አሶሳ ስንደርስ እንዲህ ሆነላችሁ፡፡
አንድ ሆቴል ሄድን፡፡ ማረፊያችሁ እዚህ አደለም ተባለ፡፡ እርስ በርስ፤ የራስ ግምትም ተጨምሮበት፣ ስም ሊስት የያዙ ሁለት ሶስት ሰዎች ይታያሉ፤ እነሱን እየተከተሉ “ስሜ አለ ወይ?” እያሉ መጠየቅ ግድ ሆነ፡፡ ሁሉም የሚያውቀውንና አስተባባሪ ሊሆን ይችላል የሚለውን ሰው ይጠይቃል፡፡ ግራ ይገባል፡፡
ብቻ በመጨረሻ “ባምቡ ሆቴል ኑ ተብላችኋል” የሚለው ድምፅ በረከተና ወደ ባምቡ ሄድን፡፡ ደግነቱ አሶሳ ዐርበ - ጠባብ ናትና ከዚያች እዚያች እንደ መራመድ ነው ከሆቴል ሆቴል መሄድ፡፡ ባምቡ ሆቴል ደረስን፡፡ አስተባባሪው ልጅ ያውቀኛል፡፡ ከእኔ ጋር ያሉት እሱን ያውቁታል፡፡ “ሻንጣችሁን ሪሴፕሺን አስቀምጡና ምሳ ትበላላችሁ! ምሳው ላይ ስለመኝታችሁ እንነጋገራለን!” አለን፡፡ ቢያንስ መመሪያ ብጤ አግኝተናል አሁን፡፡ አበሻ ትንሽ እፎይ ሲል ብሶቱንም፣ ጨዋታውንም፣ ጉርምርምታውንም አንዴ ጠረጴዛው ላይ መዘርገፍ ይወዳል፡፡ ከምግቡ ጋር ነገር ማላመጥ ይቀናዋል፡፡  
“ይሄን ሁሉ ሰው ጠርተው ፕሮግራሙን ማሳወቅ እንኳ እንዴት ያቅታቸዋል?” አለ አንዱ፡፡ “ይሄ ሰው መናቅ ነው - የሰው ዋጋ አለማወቅ! ብቻ የጋበዘኝን ሰው ላግኘው!” አለ ሌላው፡፡ ብሶት ወዲያው ተቀጣጠለ፡፡
ቀጥሎ ያበሻ First Aid (የመጀመሪያ እርዳታ) ከንፈር እየመጠጡ “እምጥ… እምጥ” ማለት ነው፡፡ ትንሽ ሲሻሻል አስተያየት፣ አንዳንዴም ፍልስፍና ብጤ ይጨመርበታል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ሶስት ፈርጅ ያለው ነው ያበሻ አስተያየት፡-
“ዎ መንግስት ቤትኮ ይሄው ነው፡፡ ባለፈውም እንደዚሁ ተጫውተውብናል” አለ አንደኛው፡፡ ይሄንን “የትላንት ምሬት” በሉት፡፡ ቀጠለ ሌላኛው፡፡ “አሁንም‘ኮ ምንም ያሉን ነገር የለም፡፡ ብሉና እንወያያለን ነው የተባልነው!” አለ፡፡ የዛሬ ምሬት በሉት ይሄንን፡፡
ሦስተኛው ሰው፡- “ገና ምን አይታችሁ - ምስቅልቅላችንን ነው የሚያወጡት!” ይላል፡፡
ይሄ እንግዲህ የነገ ጉዳይ ነው፡፡ ትላንተኛነት…ዛሬኝነት…ነገኛነት! ትላንት፣ ዛሬና ነገን ምሬትና ብሶት ካፈሰሱባቸው በኋላ አንዱ ማስታመሚያ ሀሳብ ያቀርባል፡-
“ግን‘ኮ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ገና አዳጊ ክልል ነው - አትፈረዱበት”
ከአዲሳባው ዝግጅት ኮሚቴ ወደ ክልሉ መጣ ማለት ነው የቅንብር ችግሩ!
የጉዞ አስተባባሪው መጥቶ “እስቲ ትንሽ ቆዩ የናንተ አፍሪካ ሆቴል ሳይሆን አይቀርም” አለን፡፡ እንግዲህ ከቆየን ማወራረጃ ቢራ እንዘዝ ተባባልን፡፡ ከዩኒቨርሲቲው መምህር ወዳጄ ጋር ቢራ ልናዝ ተስማማን፡፡ አሁን እንግዲህ ወደ 10 ሰዓት ሆኗል - ከሰዓት፡፡ አስተናጋጇን “ቢራ እባክሽ” አልኳት
አስተናጋጇም “ቢራ በጀታችሁ ውስጥ አልተያዘም፡፡ ለስላሳና አምቦሃ ነው የሚቻለው” አለችን፡፡
“ይሁን እንከፍላለን - ብቻ ቶሎ አምጪው” አልናት፡፡
በዚህ ማህል ከእኛው ጋር ከመጡት ውስጥ አንዷ ታዋቂ ሴት መጣችና
“ነቢይ፤ የት ያዛችሁ አልጋ?” አለችን፡፡
“የትም” አልኳት፡፡
“እኔ እደዚህ ያለው የመንግስት ጉዞ ላይ እናቴ፣ ፊት የመቀመጫዬን ብዬ፤ ክፍሌን ይዤ መጣሁ” አለች፡፡
እኔ በሆዴ ትንሽ አማኋት፡-
“ይቺ ልዩ አስተያየት የሚደረግላት፣ ከመንግሥት ጉዞ ሁሌ አይቀሬ ከሚባሉት ተጓዦች ውስጥ ሳትሆን አትቀርም፡፡ እንጂ ከአገር ሰው ማህል ብቻዋን እንዴት አልጋ ይሰጣታል?” አልኩ፡፡
በመጨረሻ ከየት እንደተሰማ ባላውቅም አንድ መልዕክት በተደጋጋሚ ተነገረ፡-
“አርቲስቶች በሙሉ ሥራ አመራር ኢንስቲቲዩት ነው የምታርፉት”
“ስራ አመራር ኢንስቲትዩት ደሞ የት ነው?” አልን፡፡
“ከዚህ አንድ 10ኪ.ሜ ገደማ ነው!”
“ገጠር ሊወስዱን ነዋ! ገና ምን አይታችሁ እነዚህ ሰዎች …” አለ ሌላው የነገ ስጋት ያለው አርቲስት፡፡
ሁሌም የሚገርመኝ ክፉም ደግም ጎን ያለው አንድ ነገር፤ ይሄ ተጓዦችን ከከተማ ወጣ አድርጎ የማሸግ የአፍሪካ ፈሊጥ ነው፡፡ ደቡብ አፍሪካ አጋጥሞኛል፡፡ ዛምቢያ አጋጥሞኛል፡፡ ኬንያ አጋጥሞኛል .. ይገርመኛል! ፈረንጆች “a letter in a mail - box” የሚሉት አገላለፅ አላቸው፡፡ ከአንድ የፖስታ ሳጥን ወደ ባለቤቱ አንደሚወሰድ ደብዳቤ መሆን፤ ማለታቸው ነው፡፡ ፖስታው በገዛ ፈቃዱ ከሳጥኑ መውጣት እንደማይችል ሁሉ እኛም ያለፈቃዳችን ከከተማው ርቀን ልናድር ነው፡፡ ለጥናትና ምርምር አሊያም ለወርክሾፕ መጥተን ቢሆን እንኳ ጥናቱን ወይ ወርክሾፑን ስንወያይ ይመሻልና የበለጠ በትናንሽ ቡድን እናበስለዋለን - ይህ በጎ ጎኑ ነው፡፡
ለማንኛውም ወደ ስራ አመራር ኢንስቲትዩት ግቢ ገባን፡፡ ቡናና ፈንዲሻ የገቢ ተባልን፡፡ ቦታ ተደለደልን፡፡ እኔ መጀመሪያ የተመደብኩት 10 ሰው የሚይዝ ባለሁለት ድርብ አልጋ ያለው ክፍል ነበር፡፡ በኋላ ግን ዘነበ ኦላን አገኘሁትና “የእኛ ክፍል 4 ሰው የሚይዝ ቀለል ያለ ክፍል ነው፤ ለምን አትመጣም?” አለኝ፡፡ ሄጄ አየሁት፡፡ ዕውነትም ከባለ አስሩ ይሻለኛል፡፡ ክፍል ለወጥኩ፡፡ ተጣጠብንና ንፋስ ለመቀበል ስንወጣ፤ ዘነበ እዚህ አገር ወዳጆች አሉኝ - እነሱጋ ነገ መሄድ እንችላለን” አለኝ፡፡ “የአሶሳን ህይወት አጣጥሞ ለማወቅ ወደ  አገሬው ብቅ ማለትና ቤተሰብ ማየት ጥሩ ነው” አልኩኝ፡፡ ቀጥሎም “እዚህ አገር፤ ብርሃነ መስቀል ረዳ ያቋቋመው ላይብረሪ (መጽሐፍት ቤት) እንዳለ ታውቃለህ?” አለኝ፡፡ (ብርሃነ መስቀል እንግዲህ ኢህአፓን ከመሠረቱት ሰዎች አንዱ ነው፡፡)
“ኧረ ባክህ?”
“አዎ ሥዩም ወልዴ “ኩርፊያ የሸፈነው ፈገግታ” ብሎ በፃፈው መጽሐፉ ላይ የጠቀሰው‘ኮ ነው?” አለኝ አጠናክሮ፡፡ የሥዩምን መጽሐፍ በቅርብ ነው ያነበብኩት፡፡ ይሄን ጉዳይ በትናንሽ ቡድን ሌላ ጊዜ እናየዋለን፡፡
ከዘነበ ዎላ ጋር መጽሐፍት ቤቱን ሄደን ልንጐበኘው ዕቅድ አወጣን፡፡ ብርሃነ መስቀልን ደርግ ጽ/ቤት እሥር ቤት ውስጥ አግኝቼው ስለነበር የጓደኛዬን መጽሐፍት ቤት እንደማይ ሁሉ ህዋሴን ነዘረኝ፡፡ አንድም የዚያን ትውልድ ጥንካሬና ለአገር አሳቢነት ያሳያል የሚል ስሜት ተሰምቶኝ ሊሆን ይችላል - ለራስ ሲቆርሱ አያሣንሱ አደለ፡፡
በሥራ አመራር ኢንስቲቲዩት ግቢ እኛ የተመደብንበት ንፍቀ - ክበብ ዙሪያ ነው፡፡ ዙሪያውን ክፍሎች አሉ፡፡ መካከል ላይ ቅርንጫፉ የተንዘረፈፈ ዛፍ አለ፡፡ የዛፉ ጥላ አንዳች ቀዝቃዛ ድባብ ፈጥሯል፡፡ ጥላው ላይ ዙሪያውን ፍራሽ ተነጥፏል፡፡ ዋና ዋና ሰዎች ተቀምጠዋል:- ንዋይ ደበበ፣ አረጋኸኝ ወራሽ፣ ኪሮስ ሃ/ሥላሴ፣ ቢንያም ሃ/ሥላሴ፣ ኩራባቸው ደነቀ፣ ኃይሉ ፀጋዬ፣ እመቤት ወ/ገብርኤል፣ ቶማስ ቶራ፣ አስቴር ከበደ፣ ስማቸውን የማላስታውሳቸው ሁለት ሶማሌዎች አሉ፡፡ ጨዋታው ደርቷል…አርዕስት ይነሳል አርዕስት ይጣላል… ውይይቱ ሞቋል፡፡ ንዋይ በሰፊው ይጫወታል፡፡ በተለይ አንዱ አባል “ንዋይ አየር ወለድ ነበርክ የሚባለው ዕውነት ነወይ?” ሲል በድንገት ጠየቀው፡፡ ንዋይ ታሪኩን አስረዳን፡፡ ማብራራቱን የወደደው ይመስላል፡፡ አምስት ሆነው ከቀይ ሽብር ሽሽት ከሻሸመኔ መጥተው ደብረዘይት አየር ወለድ እንዴት እንደገቡ፣ በኋላ ግን እዚያም አሳሳቢ ሁኔታ በመፈጠሩ እንደገና መውጣታቸውንና ንዋይና አንዱ ጓደኛው ወደ አዋሳ እንደሄዱ፤ ሌሎቹ ሦስቱ ግን አዋሳ አንመለስም ብለው ወደ ናዝሬት/አዳማ እንደሄዱና እዚያው እንደሞቱ በሚያስደንቅ ስሜታዊነት ገለፀልን፡፡ ውይይቱ እንዳማረበት መሸ፡፡
አመሻሽ ላይ የተወሰንን ሰዎች አዋሳን በምሽት እንያት ብለን ከባኮው ወጥተን ወደ ከተማ ሄድን፡፡
በመጀመሪያ ባምቡ ሄድን፡፡ አዋሳ የቀርክሃ አገር ናት፡፡ ቀርክሃ ሆቴል እንዳይሉት ምን እንዳገዳቸው እንጃ፡፡ ቅንጭብ፣ ቃጫ፣ ቁርቁራ፣ ቆንጥር፣ ምናምን ሆቴል፤ አይበሉት እንጂ ቀርክሃ እኮ ቆንጆ ስም ነበረ አልኩኝ በሆዴ፡፡
ባምቡ ሆቴል ግቢ ዛፉ ስር አያሌ ሰው ታድሟል፡፡ አብዛኛው ባለሥልጣን እዚያው እንደሚያርፍም ጠርጥሬያለሁ፡፡ እኛ “ሥራ አመራር” ራት ቢኖረንም እዚህ ብንበላስ ብለን እንደዘበት ብንጠይቅ፤ ከቢፌው ምግብ አመጡልንና በላን፡፡ ከዚያ በየቡና ቤቶቹ ዘወር ዘወር አልን፡፡
ያየነው ቡና ቤት ሁሉ፤ እንደአብዛኛው የደቡብ ቡና ቤት ሁሉ፤ ከፊት ለፊት ዛፍ የከበበው፣ በረንዳውም ሆነ ግቢው ጨለምለም ያለ፣ ብዙ ሰው እጭለማው ጋ የሚስተናገድበት፣ ዋናው ውስጠኛው ቡና ቤት ግን ሰፊና ፏ ያለ መብራት ያለው ነው፡፡ በሁለት ሦስት ቀናት የበለጠ እናየዋለን ተባብለን ቢራ ቀማምሰን ወደማደሪያችን ሄድን፡፡
ነገ ወደግድቡ ጉዞ ነው፡፡ ፊታችንን ወደ ነገ አዙረን ተኛን!
መቼም መፃፍ ለምንጽፈው ነገር ፍቅርን መግለፅ ነው፡፡ ነጋና ከጠዋቱ 11፡30 ወደ ግድቡ ለመሄድ ተነሳን፡፡ ይመጣል የተባለው አውቶቡስ አልመጣም፡፡ አንድ ሌላ አውቶብስ ግን ግቢ ገብቷል፡፡ ስንጠይቅ “ይሄ የአርቲስቶች አይደለም የሥራ አመራሮች ነው” አለን ሹፌሩ፡፡ አልገባኝም፡፡ የጉዳዩ ባለቤት የሆነ ኃላፊ ስለሌለ ማንንም መጠየቅ ስለማልችል መጠርጠር ነው፡፡ “የአርቲስቶች ባስ” ባይገባኝም ተቀበልኩት፡፡
“ምናልባት እስክስታ እየወረደ የሚወስደን ይሆናል” ብዬ ጐኔ ላለ አንድ ሰው ነገርኩትና ተሳስቀን ጥበቃችንን ቀጠልን፡፡
ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን የዚያው አውቶብስ ተሳፊሪዎች “ባዶውን ከሚሄድ ለምን ከኛ ጋር አትሄዱም” አሉን፡፡ ሳስበው ካውቶብስ አውቶብስ የምናማርጥበት አይደለም - በተገኘው መሄድ ይሻላል አልኩኝ፡፡ ቅርቤ ያለውን ኃይሉ ፀጋዬን ጠራሁት፡፡ ኃይሉ ያገሬ የናዝሬት ልጅ ነው - አዲሳባም አትገናኙ ቢለን ነው እንጂ እንቀራረባለን፡፡
ፀሐፌ - ተውኔት መንግሥቱ ለማ እንዲህ ይሉናል “ባለ ካባ እና ባለደባ” ላይ፡፡
(በቴያትሩ ላይ ተዋናይ ስለነበርኩኝ አስታውሰዋለሁ)
አንዱ ገፀ - ባህሪ ሌላውን፤
“የት ነህ ያለኸው?” ይለዋል፡፡
“እዚሁ - አዲሳባ!” ይላል ያኛው፡፡
“ታዲያ እንዴት አንገናኝም?” ይለዋል፡፡
“አዲሳባ በመስፋፋቷ ሳይሆን ይቀራል? እኩሬ ውስጥ ያሉ አሣዎች በየጊዜው ስለሚተላለፉ ይተያያሉ፤ ይገናኛሉ፡፡ እባህር ውስጥ ሲገቡ ግን ያ ሁሉ ይቀራል” የእኔና የኃይሉም ነገር እንደዚያ ነው፡፡ ለማንኛውም ዛሬ ተገናኝተናል፡፡ አብረንም ተቀምጠናል፡፡
እንግዲህ ወደ ግድቡ አመራን፡፡ ትንሽ ትንሽ ሐሜታ አልጠፋንም፡፡ “አርቲስቱ አንድ ላይ ለመሆን ለምን ይፈልጋል? ሁሌም በየሥራ መስኩ ይገናኛል፡፡ ዛሬ እንኳ ነጠልጠል ቢል ምናለበት፡፡ ሌላ አመለካከት፣ ከሌላ ህይወት ጋር ቢቀላቀልኮ ቢያንስ ለውጥ ይሆንለት ነበር፡፡ Landscape ይፈጠርለታል - የተለየ አስተሳሰብ፣ የተለየ ንፍቀ - ክበብ! ሁሌ የሚገርመኝ የአበሻም የቤት ጣጣ ነው! አገር ውስጥም ሆነ ውጪ አገር ሰብሰብ የማለት ሁኔታ ሲገኝ እንደገና እኛው የምንተዋወቀው ሰዎች ተገናኝተን ጥግ መያዝ ነው ሥራችን! (ማሽሟቀቅ” ይለዋል ባሴ ሀብቴ ነብሱን ይማረውና!)
ወደ ግድቡ ስናመራ ከንጋቱ 11፡30 ግድም አንድ አስገራሚ ነገር አየን! ከእኛ በስተግራ ባለው የሰማይ አድማስ ጨረቃ የብርቱካን አሎሎ መስላ ቁልቁል ወደተራራዎቹ ትወርዳለች፡፡ በስተቀኝ ባለው የሰማይ አድማስ ደግሞ ሌላ ዱባ - አከል ፖም መስላ ፀሐይ ሽቅብ ወደ ላይ ትመጣለች፡፡ አንዷ ከኛ ዐይን ሽሽት ከተራራው ጀርባ በመሽቆልቆል ላይ ያለች፣ አንዷ ደሞ  ወደ እኛ ዐይን ለመግባት መሰላል እየወጣች ያለች ትመስላለች! እኔና ኃይሉ ዐይናችንን ማመን አቅቶናል፡፡ እኔ፤ አንድም በገጣሚ ዐይን፣ አንድም በሰዓሊ ዐይን አንድም እንዲያው በአዘቦት ዐይን ሳይ፤ እንዲህ ያለ ጨረቃና ፀሐይ ሲተያዩ ማየት አጋጥሞኝ አያውቅምና ነብሴን ሰርቆታል!
ወዴት ትወጫለሽ አለቻት ጨረቃ
እኔ ሰው አይቼ ታዝቤ ሳበቃ
ፀሐይም መለሰች፤ ትላንት ያየሽውስ  መቼ አለና ዛሬ
ኑሮ ተለዋዋጭ፤ ቶሎ እማይጨበጥ፤ ዛሬ ሰው ነገ አውሬ!
ያሰኘኝ ነው!!
ነብሳችን በተፈጥሮ እንደተሸነፈች ከወዲሁ ገብቶናል፡፡
ሰማይ ላይ አውሮፕላን ውስጥ ሆነን እኔና ኃይሉ ዐባይን ስናይ ያን የተልባ እባብ የመሰለ ጉዞውን አይተን ስለነበር እጅግ አድርገን አድንቀናል፡፡ አሁን በዐይናችን ልናየው በእጃችን ልንዳስሰው ነው፡፡ ዳቡስ የተባለው ወንዝ ዋናው የዐባይ መጋቢ ነው፡፡
ስለሌሎቹም ወንዞች አውቶብሱ ውስጥ የነበሩ ጐበዝ ጐበዝ የውሃ ሙያ ሰዎች ገለፃ ካረጉልን በኋላ የዐባይ ግጥሜን እንዳጠነክረው ሀሳብ ፈነጠቀብኝ:-
“…ዳቡስ የመጋቢ ንጉሥ
በጐርፍ እንዳትሌት ሲፈስስ
ላንተው ውሃ ዳስ ሲቀይስ፡፡
ግልገል ጐጆህን ሲቀልስ
ዴዴሣ ዳልጋው ሲያገሳ
ዲንደር ጅረቱን ሲያስነሳ
ባሮ - ውሃ አነባበሮ
መንፈሱን ላንተው ገብሮ
ፊንጫና የማዶ ጉደር
ኦሮሚያ ቤኒሻንጉል፣ ድግስ ጭነው ውሃ ግብር
ተስማምተው ላንተ ለማደር
ሸለቆ ግልገል ኮርማ ኃይል
አንድም ድፍርስ አንድም ጠለል
እንደ አገር ህብር የህዝብ ወኪል
እንደራሴ ሆነው በእኩል
አቢይ ዐባይ ነብሰ ጡር ማይ
የጥንተ - ታሪክ ውል አዋይ!
ተትረፍረፍ ፍሰስ እንደልብ፣ እንካ ኮርቻ ግድብ!
ሰው የሚያለማ እጅ ጥበብ
ዐባይ ዐቢይ ፍኖተ ማይ
ዛሬስ ፍሰስ እትብትህ ላይ!
በተርባይን ተርብ ጥንስስ
አገርክን ሻማ ሸማ አልብስ!!”
የትልቁ ዐባይ ግጥሜ አንድ አንጓ ነው፡፡
ግድቡ ግድም የደረስነው በርሃብ ተከበን ነው ለማለት ይቻላል፡፡
ግቢው ስንደርስ ማንም የመንገድ መሪ የለንም፡፡ ወዴት እንደምንሄድ የነገረን የለም፡፡
ቀጥሎ ምን እንደሚደረግ አናውቅም Disorganization ቅጥ የለሽ አመራር ዓይነት ነው የሚል ስሜት ሁላችንም ላይ ሰፍሯል፡፡ ከንጋቱ 11 ሰዓት ጀምሮ እህል ባልቀመሰ አንጀት ላይ ወዴት እንደምንሄድ አለማወቅ መራር ነው፡፡ አንድ አውቶብሱ ውስጥ ያለ ሰው፤
“ለ9ኛ ጊዜ የሚካሄድ የብሔር ብሔረሰብ በዓል የተሻለ አመራር እንዴት አይኖረውም?” አለ፡፡
አንድ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ መምህር ኢትዮጵያ ውስጥ ፒኤችዲውን ሊሠራ ከእንግሊዝ የመጣ “በእኛ ትምህርት አንድ ፖሊሲ አለ” አለና ጀመረ፡፡   
በግል እንተዋወቃለን!
“አንድ ተማሪ አንዴ ስህተት ሠርቶ 12 ከ20 ሊያገኝ ይችላል፡፡ ወይም ከ10 በታች አግኝቶ ይወድቃል፡፡ በሚቀጥለው ጊዜ ያነሰ ነው መውደቅ ያለበት 16 ከ20፤ 17 ከ20 እያለ ማሻሻል ይጠበቅበታል!”
ግድቡን አየነው!
ሰማይን ሊውጥ አፉን የከፈተ፣ ከፈፋ ፈፋ እያዛጋ የሚመስል ግዙፍ ጉድጓድ ነው፡፡ በቴሌቪዥን እንደምናየው ትንሽ አይደለም፡፡ ትልቅነቱና በውስጡ ያሉት ተርባይኖች (16) ጥርስና ላንቃው ይመስላሉ! ረሀባችንን ገዛው መሰለኝ - ለጥቂት ጊዜ ግድቡን ብቻ እንድናስብ ሆንን!
ዞሮ ዞሮ ወደምሣ መሄድ ነበረብን - ደክሞናል - ፀሐዩ በርትቷል!!
(ይቀጥላል)


Read 2959 times