Saturday, 24 January 2015 12:55

በ60 ሚ. ብር የተገነባው ዘመናዊ የህክምና ማዕከል

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(1 Vote)

በ300 ሚ. ዶላር ኢትዮ አሜሪካን ዶክተርስ ስኩል ሊገነባ ነው

“ከአገሬ ወጥቼ ዘመኔን በስደት አሳልፋለሁ የሚል ምኞትና ህልም ፈፅሞ አልነበረኝም፡፡ የቀዶ ህክምና ትምህርቴን በ1976 ዓ.ም አጠናቅቄ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በሙያዬ እየሰራሁ ባለበት ወቅት አገሬን ጥዬ ለስደት እንድዳረግ የሚያስገድድ አጋጣሚ ደረሰብኝ፡፡ በቤተሰቦቼና በጓደኞቼ ላይ የደረሰው አደጋ አስደንግጦኝ ስደትን መረጥኩ፡፡ መጀመሪያ የሄድኩት ወደ አውስትራሊያ ነበር፡፡ ከዚያ ወደ አሜሪካ ቴክሳስ፣ በመቀጠልም ወደ ኒውዮርክ አምርቼ ኒውዮርክ ሜዲካል ኮሌጅ ውስጥ የውስጥ ደዌ ህክምና አጠናሁ፡፡ በዚሁ ኮሌጅ ለአምስት አመታት በአስተማሪነት አገልግያለሁ፡፡ ላለፉት ሰላሳ አመታት በህክምና ማማከር አገልግሎት፣ በማገገሚያ ማዕከላትና በበጎ ፍቃደኝነት ደግሞ በአልበርት አንስታይን ኮሌጅ ኦፍ ሜዲስን ስሰራ ቆይቻለሁ፡፡
“ወደ አገሬ ተመልሼ ለመግባትና በሙያዬ ወገኖቼን ለማገልገል እንድወስን ያደረገኝ ግን አሜሪካ አገር ከሚኖሩና እኔ ከምከታተላቸው ህመምተኞች የተሰጠኝ ምላሽ ነበር፡፡ በአሜሪካ አብዛኛዎቹ በእኛ ዘመን የተሰደዱ ሰዎች እድሜያቸው የገፋና ጡረታ የወጡ ናቸው፡፡ ለምን ወደ አገራችሁ አትገቡም? ስላቸው፣ ሐኪም ወደሌለበት ቦታ ሄደን ችግር ላይ እንወድቃለን ይሉኝ ነበር፡፡ እኔ ብሔድስ ስላቸው፣ ያኔማ እኛም እንገባለን… የሚል ምላሽ ይሰጡኛል፡፡ ይህ ነገር በውስጤ የሆነ ነገር እንዲጫርና ወደ አገሬ ለመግባት ልቤ እንዲነሳሳ ምክንያት ሆነኝ፡፡ እንደ እኔ ወደ አገራቸው ለመግባት ፍላጎቱ ካላቸው፣ ከህክምና ባለሙያ ጓደኞቼ ጋር በመሆን፣ ወደ አገራችን ገብተን በሙያችን ወገኖቻችንን ማገልገል እንዳለብን አሰብን፡፡ እናም ይህንን የጤና ማዕከል ልናቋቁም በቃን፡፡” ይህንን ያሉኝ ባለፈው ቅዳሜ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የዋሽንግተን ሜዲካል ሴንተር ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ፋሲል ተፈራ ናቸው፡፡ በአሜሪካ አገር ከሃያ አምስት ዓመታት በላይ በህክምና ሙያ ሲያገለግሉ በቆዩ የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ሀኪሞችና በሌሎች ኢትዮጵያውያን ሀኪሞች  ጥምረት የተቋቋመው ዋሽንግተን ሜዲካል ሴንተር፣ 60 ሚሊዮን ብር የፈጀ ሲሆን ዘመኑ ባፈራቸው ዘመናዊ የህክምና መስጫ መሳሪያዎች የተደራጀ መሆኑን የህክምና ማዕከሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ማርቆስ ፈለቀ ተናግረዋል፡፡ በውስጥ ደዌ ህክምና ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራው ማዕከሉ፤ በዘመናዊ የኤክስሬይ፣ አልትራ ሳውንድ፣ ኢኬጂና ላብራቶሪ ክፍሎች የተደራጀ ሲሆን ተቀማጭነታቸው በአዲስ አበባ ለሆኑ ዲፕሎማቶችና የውጪ አገር ሰዎች የህክምና አገልግሎት የሚሰጥ ደረጃውን የጠበቀ የህክምና ማዕከል መሆኑን ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል፡፡
“ማዕከሉ ዋሽንግተን ሜዲካል ሴንተር የሚል ስያሜ እንዲሰጠው የወሰንበት ዋንኛ ምክንያታችን በዚያ የስደት ዘመን መጠጊያና መሸሸጊያ አጥተን በነበረበት ወቅት በሯን ከፍታ የተቀበለችን ከተማ ዋሽንግተን በመሆኗ ለእሷ መታሰቢያ እንዲሆን በማሰብ ነው” ያሉት የማዕከሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ፋሲል ተፈራ፤ እንደ እኛ ሁሉ ወደ አገራቸው በመመለስ ወገኖቻቸውን ለማገልገል የሚፈልጉ በርካታ የጤና ባለሙያዎች እኛ የጀመርነውን ፈር በመከተል ወደ አገራቸው በቅርቡ እንደሚመለሱ ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል፡፡ አሜሪካንን ጨምሮ በተለያዩ የዓለም አገራት የሚገኙ የህክምና ባለሙያዎችን ያካተተውና ከ250 በላይ አባላት ያሉት በሐኪም ወርቅነህና በአቶ መላኩ በያን ስም የተቋቋመው ማህበር፤ ለዚህ ትልቅ አስተዋፅኦ ያደርጋል ብለው እንደሚያስቡም ተናግረዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሊሰራ ለታቀደውና እስከ 300 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ይደረግበታል ተብሎ የታሰበው ኢትዮ አሜሪካን ዶክተርስ ስኩል በርካታ በውጪ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የጤና ባለሙያዎችን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ያደርጋቸዋል የሚል እምነት እንዳላቸውም ገልፀዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሲኤምሲ አካባቢ ሊገነባ ለታቀደው ለዚህ ሆስፒታል ህንጻ ማሰሪያ የሚሆን ገንዘብ በማሰባሰብ ላይ እንደሚገኙና ቦታው እንደተሰጣቸው ግንባታውን በፍጥነት ለመጀመር መዘጋጀታቸውንም ዶ/ር ፋሲል በዚሁ ወቅት ገልፀዋል፡፡ “በተለያዩ የዓለም አገራት የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን የጤና ባለሙያዎች ወደ አገራቸው መምጣትና ወገኖቻቸውን በሙያቸው ማገልገል የሁልጊዜም ህልማቸው ቢሆንም በጤናው ዘርፍ ያለው አገልግሎት አስተማማኝ ባለመሆኑ ብንታመምስ፣ ችግር ቢፈጠርስ? የሚል ስጋት አላቸው፡፡ እኔ ወደ አገሬ ለመመለስ መወሰኔን የነገርኳቸው በርካታ ጓደኞቼ “አብደሀል እንዴ?” ሲሉ ጠይቀውኝ ነበር፡፡ “አላበድኩም፤ ያበድኩት እዚህ በመኖሬ ነው” የሚል ምላሽ ሰጠኋቸው፡፡ መጥተሸ እስከምታይው ድረስ ማመን አትችይም፤ ሁሉም ነገር ያስፈራሻል፡፡ እኔም ሁለት ሶስት ጊዜ ተመላልሼ ካየሁ በኋላ ነው የወሰንኩት፡፡ አሁን በቋሚነት ኑሮዬን በአገሬ አድርጌ፣ ወገኖቼን ለማገልገል ወደ ኢትዮጵያ ተመልሻለሁ፡፡ አንዳንድ ማጠናቀቅ የሚገቡኝ ጉዳዮች ስለአሉ ለትንሽ ጊዜ መመላለሴ አይቀርም፡፡ ግን ሙሉ ጊዜዬን በአገሬ እየሰራሁ ለማሳለፍ ወስኜ ተመልሻለሁ፡፡ አሁን እንደኔ በርካታ ኢትዮጵያውያን የጤና ባለሙያዎች ወደ አገራቸው በሚመለሱበት ጉዳይ ላይ የበኩሌን ጥረት አደርጋለሁ” ሲሉ ተናግረዋል - ዶ/ር ፋሲል፡፡ በንግድ ሚኒስትሩ አቶ አሊ ሲራጅ ተመርቆ የተከፈተው ዋሽንግተን ሜዲካል ሴንተር፤ በስፔሻላይዝድ ሐኪሞች የሃያ አራት ሰዓት የህክምና አገልግሎት  እንደሚሰጥም በምረቃው ስነስርዓት ላይ ተገልጿል፡፡ በዚሁ የህክምና ማዕከል ምረቃ ላይ የተገኙ እንግዶች በሰጡት አስተያየት፤ የማዕከሉ መከፈት በህክምናው ዘርፍ ተስፋ ሰጪ ጅማሮ ነው ብለዋል፡፡  

Read 3328 times