Saturday, 24 January 2015 13:31

ሮሚዮዘ ጁሊየት እና ኢያጎ

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(5 votes)

12፡ July Face book
ፎቶ …፡- ወጣት ልጃገረድ ሚኒ እስከርት ቀሚስ አድርጋ ትልቅ ሶፋ ላይ እግሯን አጣምራ ትታያለች፡፡
ጓደኞቿ ወዲያው በ Like መዓት አጀቡዋት፡፡
150 Like – 70 Comments
Leul and 69 others have commented
ኮሜንት ሲከፈት፡-
Abebe:- Wow! መቲ እንደዚህ የተሽቀረቀርሽው የት ለመሄድ ነው?
Sol:- እቺ ልጅ የሆነ ሰው cook ሳታደርግ አልቀረችም
Leul:- የጠበስሽውን ቶሎ አግቢውና ጥሬውን እንደኔ ቀቅለሽ አብስይው!...
መቲ:- How dare you insult me on face book ቀንተህ ነው አይደል…እርር ድብን በል!
 Leul:- ቅናት?! Hahaha….ቅናት ፍቅር በተቀናበት ቀናት ነው ባክሽ…እኔ ረስቼሻለሁ! አርፈሽ ጠበሳሽን አጧጡፊ!!!
አበበ :- ሁለታችሁም እረፉ…መነጋገር ካለባችሁ ከ face book ውጭ ተገናኙና አውሩ፡፡ አንተ ልዑል ደግሞ የፈለገ ቢሆን ምናለ…ዝም ብለህ አምሮብሻል ብትላት…ምን ይጐዳሀል?
ልዑል :- ስልኬን አላነሳም ማለቷን እንጂ ታውቃለህ፤ ፌስቡክ ላይ አተካሮ አይመቸኝም፡፡ በአንተ ፊት አሁኑኑ ትንገረኝ Is she seeing somebody?
መቲ:- ከሌላ ሰው ጋር ብሆንስ…ምን ልታደርግ ነው? በአለፈው እንደፈጠርከው አይነት የዱርዬ አንባጓሮ ልትፈጥር ነው? አልፈልግህም ተወኝ!!
አበበ :- ልዑል በእናትህ ተረጋጋ…ነገ እኔ እና አንተ ተገናኝተን እናወራለን፤ አሁን ዝም ብለህ ለመተኛት ሞክር… ከቤት የትም እንዳትሄድ Please
መቲ:- አቤ: በአለፈው ያደረገውን ነግሬሀለሁ አይደል…
አበበ:- አይ ከሰው ሰምቼአለሁ…በቃ አሁን ተረጋጊ I will talk to him tomorrow…sleep tight
(በቴክስት መልዕክት አበበ ለመታሰቢያ:- ግን “Are you seeing somebody else?” ብሎ ላከላት፡፡ መልስ ሳትሰጠው ቀረች፡፡)
“የሆነ ልጥጥ ሰው cook አደረግሽ እንዴ?” ብሎ ደገመላት
መቲ :- አንተም እንደ ሌላው ሰው ወሬ መፍተል ጀመርክ (መለሰችለት)
2፡00 PM Dec 21
 ፎቶ :-
ወጣት፤ ሸበላ…ጠይም መቲን እቅፍ አድርጐ ሲስማት ይታያል፡፡ መቲ እየተሳመች በአንድ አይኗ ወደ ካሜራው እየተመለከተች፣ ግራ እጇን ወደ ፊት ወጣ አድርጋ እየሳየች ነው፡፡ በጣቷ ላይ የጋብቻ ቀለበት ጠልቋል፡፡
ከፎቶው በላይ የሰፈረ መልዕክት :- It is official!
Like – 665  Comment – 50
Comments
ሜሮን - ስለ ሰውዬሽ ሰምቻለሁ…ቀናሁብሽ
ተረፈ :- ሜሪ ከመቅናት …ቀልጠፍ ብለሽ እኔን ማግባት [p]
ሰላም:-   አንተን ማን ያበስላል…አንተ ምግብ አብሳይ (LoL)
መቲ፡- የኔ ቆንጆ ኮንግራ
አበበ “Chat” ላይ መቲን አግኝቶ ስለ ፎቶው አወራት፡፡
አበበ :- አቤት ደስ የሚል ነገር ነው፡፡ አቤት ሰው ሲጠፋ አለመጠየቅ… አቤት እንዴት ያምርባችኋል! አቤት የLike ሽ መብዛት…
እኔ ላይክ ስልሽ ስድስት መቶ ስልሳ ስድስተኛ መሆኔ የታወቀኝ ከተጫንኩት በኋላ ነው፡፡ I hope you will not consider it as a bad omen (p) መቼ ነው ሰርጉ? አንጠራም እንዴ?
መቲ:- ጥር ላይ ነው ብለን እያሰብን ነው ከአቢ ጋር፤ ወደዚህም ቀረብ ሊል ይችላል፡፡
…እ…You know what I want to ask you…ስለዚህ ለምን አንተ ሳልጠይቅህ በፊት አትነግረኝም (በናትህ ስለምን ልትጠይቂኝ ፈለግሽ ብለህ እንዳትለኝ!)
አበበ:- I think you mean about leul (I know) ልዑል ደህና ነው፡፡ በፊት…ከነበረበት ሁኔታ በጣም ይሻላል…Don’t worry ሜዲኬሽኑን እየተከታተለ ነው፡፡
መቲ:- ቤት ሄጄ ልጠይቀው ፈልጌ ነበር…ግን የተወሳሰበ ነገር ሆነብኝ…ቤተሰቦቹ እኔን ምን አድርገው እንደሚያስቡኝ ታውቃለህ አይደል? በኔ ምክንያት የታመመ ነው የሚመስላቸው፡፡ ማንም የእኔን እውነት አይረዳም…Its sad
አበበ:- I think he knows it too…I am sure he doesn’t hate you…
መቲ:- (እያለቀሰች ነው ሞባይሏ ላይ የምትፅፈው) በናትህ እኔ ራሴ ግራ ግብት ብሎኛል፡፡
አበበ:- አንቺ አትጨነቂ…እሱ ምንም አይሆንም…በቃ ፍቅር ይሰምራል ወይ አይሰምርም፡፡ የአንቺና የልዑልን ፍቅር ፈጣሪ አልፈቀደውም፡፡ አሁን ተረጋግተሽ ህይወትሽን በሙሉ መንፈስ ጀምሪ ወይንም ቀጥይ
መቲ:- Is he with his mom and dad
አበበ:- ብዙ ነው ታሪኩ፤ አሁን ግን ሆስፒታል ገብቷል፤ ዛሬ ሄጄ አይቼው ነበር፡፡ አትጨነቂ በጣም ተሽሎታል…እንዲያውም በሌሎቹ በሽተኞች ላይ ሙድ እየያዘ ሲያስቀኝ ነበር…you can’t begin to imagine the Varity of… (ጠሾች) In that አማኑኤል place…በጣም ያሳዝኑሻል…ልብሽ ያነባል፤ ከዛ ደግሞ የሚያደርጉት ነገር ስታስቢው ያስቅሻል፡፡
መቲ:- በናትህ አትንገረኝ…እኔ ራሴ አቢ ከጐኔ ባይኖር…በእነዛ የመጀመሪያዎቹ ወራት አብጄ እዛው መግባቴ አይቀርም ነበር፡፡
አበበ :- አቢ?!...Is that your new man…your husband?
መቲ:- እሱ ባይኖር ከዛ አይነት ስብራት አላገግምም ነበር
አበበ :- (ሊፅፍ የቃጣውን ገታው “I heard your man is stinking rich” ሊላት ነበር፡፡  “I think you deserve a painless life` ብሎ ለውጠው)   
መቲ:- Yes I think so too…የልዑል ፍቅር ህመሙ አይቻልም፡፡ ህመሙ ብሶ ሊያጠፋፋን ሆነ I had to move away
አበበ፡- Any way let me know about the “big day”
መቲ፡- I will … ደውልልኝ … ቢያንስ የልዑልን ሁኔታ ማወቅ አለብኝ  
አበበ፡- He will pull through, ልዑል “ሰርቫይቨር” መሆኑን መቼም እኔ ላንቺ አልነግርሽም
መቲ፡- I blame myself
አበበ፡- ምን ማለትሽ ነው? ኧረ በፈጠራችሁ ሮሚዮ እና ጁሊየትን አትሁኑብኝ … ልዑል ራሱን በመኮነን ነው ለዚህ አሳዛኝ ደረጃ የበቃው … አንቺ ይሄንን ሀሳብ ከጭንቅላትሽ አውጭው
መቲ ፡- እንደማይሆን ስለሆነብኝ እንጂ እንደምወደው ታውቃለህ .. ክጄው አይደለም
አበበ ፡- አቦ ጠንከር በይ … ከፊት ለፊትሽ ያለውን ህይወት ተመልከቺያ… እንዴ!!! በተረፈ ስራ አሸወይና ነው አይደል? አዎ እንደምትይኝ ስለማውቅ በዚሁ ልቀንጠስ cheers!
04፡00 Nov – face book
ፎቶ:-
ሙሽሮች እጅ ለእጅ ተያይዘው በሜዳ ላይ እየሮጡ፡፡ ሴቷ (መቲ) ቀሚሷ እንዳያደናቅፋት ሰብስባዋለች፡፡
Just married!
Like - 830 comments – 100
አበበ ፎቶውን እየተመለከተ እንባ ተናነቀው፡፡ በስንት ቀኑ ነው የፌስ ቡክ ገፁን የከፈተው፡፡ ያመለጡትን የወሬ ቀናት ያህል ወደ ኋላ ተመልሶ የመቲን መልዕክቶች ተመለከተ፡፡ ስታፈላልገው ከርማለች፡፡ ወደሱ መልዕክት ሳጥን ብዙ አረፍተ ነገሮች ሰዳለች፡፡
ልዑል መሞቱን ከሰማበት ቅፅበት ጀምሮ ስልኩን በጥንታዊ አገልግሎቱ እንጂ በፌስቡክ የወሬ ፋሲካነቱ ስለጠላው ፆመው፡፡ የማንንም ትርኪ ምርኪ ወሬ ሲለቃቅም … አብሮ አደግ ጓደኛው ራሱን አንጠልጥሎ ሞቶ ጠበቀው፡፡ ፌስ ቡክን ጠላው፡፡ ፌስ ቡክ ውስጥ ስሜት የለም … ፡፡ ወሬ እና ማስታወቂያ በእያይነቱ ብቻ፡፡ ሞትም ማስታወቂያ ነው ለፌስ ቡክ፡፡
ከቀናት በኋላ አላስችል አለው፡፡ ፌስ ቡክ አካውንቱን በሚንቀጠቀጥ እጁ ከፈተው፡፡ በሞባይሉ ካሜራ ከዚህ ቀደም አጥምዷቸው ከነበሩት የልዑል ፎቶዎች መሀል የሱን ማንነት እንደ ቀድሞው የጉብዝና ዘመኑ … አንገቱን ሳይደፋ በፊት እንደነበረው ይገልፀዋል ብሎ ያሰበውን በገፁ ላይ አኖረ፡፡
“ልዑል … እግዜር በገነት ነብስህን ያኑራት”
Post
የከፈተውን በፍጥነት ዘጋ፡፡
ፌስ ቡኩ ተዘግቶም … መልዕክቶች … likeዎች R.I.Pዎች እየተከታተሉ ሲገቡ በምናቡ ተሰማው፡፡ ተጋድሞ ለተወሰነ ጊዜ ታገሰ፡፡
መቲ የልዑልን ፎቶ ተለጥፎ አይታ ምን ልትል እንደምትችል ለመገመት አልፈለገም፡፡ አይታ ልታደርግ የምትችለው ምን እንደሆነ ማሰብ ከአቅሙ በላይ ነው፡፡ ልቡ ያውቀዋል፤ እውነተኛ ፍላጐቱን፡፡ የፈለገው የማህበረሰቡን ሀዘን (የፌስ ቡክ ሀዘን) በLike ደረሰኝ መልክ መልቀም ብቻ ነው፡፡
መቲ ምናልባት የጫጉላ ሽርሽር ላይ ልትሆን ትችላለች፡፡ ሽርሽር ላይ ያሉ ሙሽሮች ፌስ ቡክ እንዳይጠቀሙ የሚከለክል ኮስታራ ባህል ቢኖር ምናለበት ብሎ ተመኘ፡፡ ግን በቤተመቅደስ ውስጥም በቅዳሴ መሀል ፀሎታቸውን ከፌስቡክ ጋር አጣምረው Post ሲያደርጉ የታዘባቸው ምዕመናን ትዝ አሉት፡፡
ለምን የልዑልን ሞት ለፌስቡክ ማህበረሰብ ማወጅ እንዳስፈለገው ለራሱም አልገባውም፡፡ መሞቱ በማህበረሰቡ ላይ የሚያመጣው አንዳችም ለውጥ የለም፡፡ ለአንዲት የማህበረሰቡ አባል ብቻ ግን ትልቅ ጉዳት ያደርሳል፡፡ በብዙ ሰው የማይጠቀም አንዲቷን ሙሽራ ግን መስበር የሚችል ዜና … Like ለመቁጠር ሲል ሞባይሉ ላይ ለጠፈ፡፡
ምናልባት በፊት፣ በዛ ምሽት ለመቲ .. የላከው ስድስት መቶ ስልሳ ስድስተኛ ውዴታ (Like) ትሆናለች መጥፎ እርግማን ሆና ተመልሳ የመጣችው፡፡ ግን እንደዛ እንዳልሆነም እርግጠኛ ነው፡፡ እንደው ራስህን ርገም ሲለው እንጂ፡፡
ከራሱ ማንነት ውጭ የወሬ አመላላሽ ባህሪን በቅልጥፍና እንዲወጣ ያስቻለው ቴክኖሎጂ በእጁ ላይ አለ፡፡ ፌስ ቡክ ሮሚዮ እና ጁሊየትን ከማገናኘት አገዳድሎ ለማለያየት የበለጠ የሚጠቅም ፈጠራ መሆኑን አመነበት፡፡
አምኖም ስም አወጣለት፡፡ “እያጎ” ብሎ መሰለው፡፡ እያጎ፤ ከኦቴሎ የድራማ ገፀ ባህሪነት ወጥቶ ሮሚዮ እና ጁሊየት መሀል በምን ምትሀት እንደገባ ለመተንተን ግን አቅም አጣ፡፡
እያጎ ግን እኩይ ባህሪውን የሚወተው በሰዎች እጅ ከተገፋ ነው፡፡ Like, Share, Comment .. ብለው ካልነኩት እያጎ ተግባሩን ብቻውን ማከናወን አይችልም፡፡ መሳሪያ ነው፡፡
አበበ ፌስ ቡክን እርም ብሎ ሊተው እንደማይችል ጠንቅቆ አውቋል፡፡ እያጎነትን ለምዷል፡፡ “የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም” አለ ለራሱ፡፡ ስልኩን መልሶ አበራ፤ ጥይት መኖሩን አረጋገጠ፡፡ ጥይት የለም፤ ካርድ ገዝቶ ሞላ፡፡
ገፁን ከፍቶ የሚከተለውን ላከ፡፡
2፡00 Dec
አበበ ዘሩ
“ሮሚዮ እና ጁሊየት የሞቱት እጣፈንታቸው ጠማማ ስለሆነ ሳይሆን፣ እያጎ መንገድ አቋርጦ መሀላቸው ገብቶ ነው፡፡ የዘመናችን ምርጥ ወሬ አመላላሽ እያጓችን Face book ተብሎ ይጠራል፡፡ Post!
Like – 10 comment – 1
ብዙም ምላሽ አላገኘም፤ የተወሰኑ “ውዴታዎች” ቆጠረ፡፡ ግን ከሰጪዎቹ ልብ ተፈንቅለው የወጡ እንዳልሆኑ ያስታውቃሉ፡፡ አስር ውዴታዎች .. እየተንጠባጠቡ በእሱ ገፅ ላይ ተጠራቀሙ፡፡ አላረኩትም፡፡ የሳይበሩ ሰማይ ተበስቶ በLike መአበል ተጠርጎ ሲወሰድ ለማየት ጓጉቷል፡፡
እንደገና ገፁን ከፈተ፡፡ እንደገና ፃፈ፡፡
2፡10 Dec
አበበ ዘሩ
ልዑል እና መቲን የገደልኩት እያጎ እኔ ነኝ፡፡ ለመግደል የተጠቀምኩበት መሳሪያ ደግሞ ይኼ ፌስ ቡክ የተባለ ፈጠራ ነው፡፡
Like – 100 comment 28
መቲ ሰምታ ምን ታደርግ ይሆን እያለ እያሰበ … ስልክ ደወለችለት፡፡ የለጠፈውን አንብባለች፣ የልዑልንም ሞት ተረድታለች፡፡ የልዑልን ሞት በለዘብታ አስተዛዘነች፡፡ አሁን መጨረሻ ላይ የላከው መልዕክት ግን አልገባትም፡፡ ከዚህ በተረፈ ያወራችለት ከራሷ ሰርግ ጋር ስለተያያዙ ነገሮች ብቻ ነው፡፡ ብዙም አላካበደችም፡፡ ሮሚዮ እና ጁልየት በፌስቡክ ዘመን ያን ያህል ትራጀዲ አይፈጥሩም፡፡ የፍቅረኛሞች መለያየት…የአፍቃሪ ማበድ…አብዶም መሞት…ለፌስ ቡክ ትውልድ ቀለል ብሎ የሚታይ ነው፡፡ ሁሉም እለታዊ … ወረታዊ ወሬዎች ናቸው፡፡
እያጐም የሚፈጥረው አሻጥር በተወሰኑ “ላይክ” እና “ኮሜንቶች” ውስጥ ተድበስብሶ ይመክናል፡፡
በአንዱ ስቃይ ላይ ሌላው ልደቱን ያውጃል፡፡ ሞቱም ውልደቱም ሰርጉም ሀዘኑም ስድቡም ሙገሳውም እንደ ቀላል በአዲስ ወሬ ታጥበው ያልፋሉ፡፡ አዲስ ወሬ ይመጣል፣ አዲስ ቁጣ፣ አዲስ ግጥም፣ አዲስ ፎቶ፣ አዲስ ቀልድ…ለእያንዳንዱ አዲስ ገፅ የሚሰጡ ውዴታዎችም ሆነ አስተያየቶች አያልቁም…፡፡
ለፌስ ቡክ ማህበረሰብ ነገም ሌላ ቀን ነው፡፡
Like   Comment   Share
ለፌስቡክ ማህበረሰብ ነገም ሌላ ቀን ነው፡፡

Read 7073 times