Saturday, 24 January 2015 14:16

የአውሮፓ አናሳ ሙስሊሞች በቁጥር

Written by 
Rate this item
(5 votes)

በቅርቡ በሁለት ፈረንሳውያን ሙስሊም ወንድማማቾች ፓሪስ ውስጥ የተፈፀመውን የሽብር ጥቃት ተከትሎ በአውሮፓ በተለይም በፈረንሳይና በጀርመን የሚኖሩ አናሳ ሙስሊሞች ጫና በርክቶባቸው ውጥረት ውስጥ ገብተዋል፡፡
ከትላንት በስቲያ በሺዎች የሚቆጠሩ ጀርመናውያን የምዕራቡን አለም “እስላማዊነት” በመቃወም አደባባይ ወጥተው ድምፃቸውን አሰምተዋል፡፡ የነገርየው አያያዝ አላምራቸው ያለ ሙስሊሞችም የገባቸውን ስጋት ለመግለጽ በፊናቸው አደባባይ በመውጣት አቤት ብለዋል፡
ጉዳዩ መገረምን የፈጠረባቸው እጅግ በርካታ ሰዎች ታዲያ አውሮፓውያን አብረዋቸው በሚኖሩት ሙስሊሞች ይህን ያህል ስጋት የገባቸው ቁጥራቸው ምን ያህል ቢሆን ነው የሚል ጥያቄ ማንሳታቸው አልቀረም፡፡
በአውሮፓ የሚገኙ ሙስሊሞች ቁጥር ከተቀሩት ጋር ሲወዳደር አናሳ መሆኑ እርግጥ ነው፡፡ በፈረንሳይና በጀርመን አተካራው ያየለበት ዋነኛው ምክንያት ሌላ ሳይሆን በምዕራብ አውሮፓ ከሚገኙት ሙስሊሞች አብዛኞቹ የሚገኙት በሁለቱ አገራት በመሆኑ ነው፡፡ በሁለቱ ሀገራት ብቻ 4.7 ሚሊዮን ሙስሊሞች ይኖራሉ፡፡
63 ሚሊዮን ከሚሆኑት ፈረንሳውያን ውስጥ 7.5 በመቶ የሚሆኑት ሙስሊም ናቸው፡፡ ይህ ቁጥር ደግሞ በምዕራብ አውሮፓ ከፍተኛው ነው፡፡ 82 ሚሊዮን ከሚሆኑት ጀርመናውያን መካከል ደግሞ የሙስሊሞቹ ቁጥር 5.8 በመቶ ነው፡፡ በፈረንሳይ ከሚኖሩት ሙስሊሞች እጅግ አብዛኞቹ የሰሜን አፍሪካ ተወላጆች ሲሆኑ በጀርመን ከሚገኙት ሙስሊሞች ውስጥ ደግሞ እጅግ የሚበዙት ትውልዳቸውን ከቱርክ የሚቆጥሩ ናቸው፡፡
በእንግሊዝ 2.7 ሚሊዮን ሙስሊሞች ይኖራሉ፡፡ ይህም ከጠቅላላው የእንግሊዝ ህዝብ 4.8 በመቶ የሚሆነውን ይወክላል፡፡ ከነዚህ ሙስሊሞች ውስጥ በጣም የሚበዙት የዘር ሀረጋቸውን የሚመዙት የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ከነበሩት ፓኪስታንና ናይጄሪያ ነው፡፡
በምዕራብ አውሮፓ ከሚኖሩት ሙስሊሞች ውስጥ በብዛት አራተኛ ደረጃ የያዙት መኖሪያቸውን ያደረጉት ጣሊያን ነው፡፡ 2.2 ሚሊዮን የሚሆኑት ሙስሊሞች ከጠቅላላው የጣሊያን ህዝብ ብዛት 3.7 በመቶ የሚሆነውን ይወክላሉ፡፡

Read 2183 times