Saturday, 24 January 2015 14:27

የእርስ በእርስ ግጭትና የውሃ ቀውስ ቀጣዮቹ የአለማችን ስጋቶች ናቸው ተባሉ

Written by 
Rate this item
(6 votes)

አለማችን በመጪዎቹ 10 አመታት 28 ስጋቶች ይጠብቋታል

በመጪዎቹ አስር አመታት አለማችንን ይፈታተኗታል ተብለው ከሚጠበቁ ስጋቶች መካከል አለማቀፍ የእርስ በእርስ ግጭቶችና ከውሃ ጋር ተያያዥ የሆኑ ቀውሶች ቀዳሚውን ስፍራ እንደሚይዙ በመካሄድ ላይ በሚገኘው የ2015 የአለም የኢኮኖሚ ፎረም አመታዊ ጉባኤ ላይ ተገለጸ፡፡የአለም የኢኮኖሚ ፎረም አመታዊ ሪፖርት እንደሚለው፣ አለማቀፍ ግጭቶች የመከሰት ዕድላቸው ከአየር ንብረት ጋር ተያያዥ ከሆኑ የተፈጥሮ አደጋዎች፣ ከአገራት የአስተዳደር ችግሮች፣ ከመንግስታት ቀውሶችና ከስራ አጥነት የበለጠ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡የህዝቦችን ህልውና አደጋ ላይ በመጣልና ጉዳት በማድረስ ረገድም፣ ከሌሎች አደጋዎች የበለጠ ተጽዕኖ ይፈጥራል ተብሎ የሚሰጋው የውሃ እጥረት እንደሆነ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡ በአገራት ውስጥ የሚፈጠሩ የእርስ በእርስ ግጭቶች፣ የተላላፊ በሽታዎች መዛመት፣ አውዳሚ የጦር መሳሪያዎችና ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያያዥ የሆኑ ቀውሶችም ጉዳት ያደርሳሉ ተብለው የሚጠበቁ ሌሎች የአለማችን ቀዳሚ ስጋቶች ናቸው፡፡
በዘንድሮው የአለም የኢኮኖሚ ፎረም በመጪዎቹ አስር አመታት አለማችንን ይገጥሟታል በሚል ያስቀመጣቸው ስጋቶች 28 ያህል ሲሆኑ፣ ስጋቶቹም ኢኮኖሚያዊ፣ አካባቢያዊ፣ ጂኦፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ከቴክኖሎጂ ጋር ተያያዥ ናቸው፡፡
በያዝነው የፈረንጆች አመት 2015 አለማችንን በከፋ ሁኔታ ያሰጓታል ተብለው የተቀመጡት ስጋቶች ጂኦፖለቲካዊ እንደሆኑ የጠቀሰው ሪፖርቱ፣ እነዚህ ስጋቶች በአገራት ውስጥ የሚከሰቱና ክልላዊ ተጽዕኖ የሚያደርሱ የእርስ በእርስ ግጭቶችን ያጠቃልላሉ ብሏል፡፡
በስዊዘርላንድ ዴቮስ በመካሄድ ላይ በሚገኘውና ዛሬ በሚጠናቀቀው 45ኛው የ2015 የአለም የኢኮኖሚ ፎረም አመታዊ ጉባኤ ላይ ከ100 የአለማችን አገራት የተወከሉ ከ2ሺህ በላይ የአገር መሪዎች፣ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች፣ የኩባንያ ሃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈውበታል፡፡
በተያያዘ ዜና ኦክስፋም ኢንተርናሽናል በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ያወጣው የጥናት ውጤት፣ ካለፉት ስድስት አመታት ወዲህ በአለማችን የሃብት ክፍፍል ኢ -ፍትሃዊነት እየጨመረ መምጣቱን ይጠቁማል፡፡
በመጪው አመት ከአለማችን አጠቃላይ ህዝብ 1 በመቶ የሚሆነው፣ ቀሪው 99 በመቶ ህዝብ ከሚኖረው ድምር የሃብት መጠን የሚበልጥ ሃብት ይኖረዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ይህ 1 በመቶ ህዝብ በመጪው አመት የዓለማችንን ሃብት ከግማሽ በላይ ጠቅልሎ ይይዛል ተብሎ እንደሚገመት ገልጿል፡፡

Read 2457 times