Saturday, 31 January 2015 12:48

ዝብርቅርቅ ጥያቄ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

….. (እኔ ላንቺ ማሬ)
አበባ ሞልቶልኝ - ዕድሜዬን ቀጥፌ
ቄጤማ እያለ - እኔኑ አንጥፌ
ወፎች ስላልበቁኝ - ጥርሶቼን አርግፌ .....
እኔ ቀልጬልሽ -
ሜዳ ላይ ፈስሼ - ለፍቅሬ ሳበራ
በገዛ መብራቴ -
ልብሽ ሌላ ‘ያየ - ለግብዣ ከጠራ .....”
.
አይጣልብሽ አንቺው - ያ’ይምሮዬ ነገር
አንቺን እያሰብኩኝ - ትዝ የሚለኝ ሀገር
አሁን የኔን ነገር - ምን ይሉታል ማሬ?
ምን ያገናኝሻል - እስቲ አንቺን ካ’ገሬ?
“…..(እኔማ ላ’ገሬ - )
.
“ሀገሬ ተራራሽ” - እያልኩኝ ዘፍኜ
ያ ቀዳዳነቷን - በአፌ ደፍኜ
እየፆምኩ ስጸልይ - ለሀገሩ ጌታ
ሁሌ እያሰርኩኝ - ሁል ጊዜ ስፈታ ..... ”
.
ግድ የለሽም በቃ -
የምር አብጃለሁ - ሙች ለይቶልኛል
እንዴት “ሀገር” ሳስብ -
እግዜር ከነግርማው - ይደቀንብኛል?
.
“ ….(እግዜር ደ’ሞ እኔን - )
ደካማዋ ነፍሴ - ከእቅፉ ርቃ
ነገር ሲጋጭባት - ሺህ ጊዜ ጠይቃ
እሱ እንደሩቅ ሰው - ዝም - ጭጭ - በቃ
ይህን ጊዜ ነፍሴ - በሃሳቧ ደርቃ ....”
.
ገላጋይ እንቅልፌ - አፋፍሶኝ ይነጉዳል
ያ ባካኙ ልቤም - እንቅልፉን ይወዳል!
.
ማሬ
እኔና እግዜሩ - አንቺና ሀገሬ
ጥያቄዎች ነን - በልቤ ‘ስከዛሬ
ስላ’ንዳችን ሳስብ -
ሌላው ብቅ እያለ - እዛው ላይ ነኝ ዞሬ!!

Read 3849 times