Saturday, 07 February 2015 12:22

የጦማሪያኑንና የጋዜጠኞቹን ጉዳይ የሚያዩት ዳኛ ከሰብሳቢነታቸው በፈቃዳቸው ለመነሳት ወሰኑ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

የይነሱልን ጥያቄው በግራና ቀኝ ዳኞች ውድቅ ተደርጓል

   በሽብርተኝነት ወንጀል ክስ ቀርቦባቸው ከዘጠኝ ወራት በላይ በእስር ላይ የሚገኙት ሶስቱ ጋዜጠኞችና ስድስት ጦማሪያን የመሃል ዳኛው እንዲነሱላቸው ያቀረቡትን አቤቱታ የግራና ቀኝ ዳኞች ልተቀበልነውም ቢሉም የመሃል ዳኛው፣ “ከዚህ በኋላ ጉዳዩን በነፃነት አየዋለሁ ብዬ ስለማላምን ከሰብሳቢነቴ ለመነሳት ለፍ/ቤቱ አስተዳደር ማመልከቻ አስገብቻለሁ” ሲሉ ከትላንት በስቲያ ገለፁ፡፡ ፍ/ቤቱ የተከሳሾቹን የእምነት ክህደት ቃል ለመቀበል ላለፈው ማክሰኞ ቀጠሮ መያዙ የሚታወስ ሲሆን በዕለቱ ውድቅ ያደረጉት ተከሳሾቹ የእምነት ክህደት ቃል መስጠት ይችሉ እንደሆነ ሲጠየቁ የመሃል ዳኛው እንዲነሱላቸው ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡ በጉዳዩ ላይ ብይን ለመስጠት ፍ/ቤት ለረቡዕ ቀጠሮ ቢይዝም የግራ ዳኛው በጉዳዩ ላይ
ስላልተነጋገሩ ብይን ለመስጠት እንደማይችል ፍ/ቤቱ ገልፆ ለሐሙስ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ፡፡ በሃሙስ እለቱ ችሎት የግራና ቀኝ ዳኞች የተከሳሾቹን “የመሃል ዳኛው ይነሱልን” ጥያቄ አልተቀበልነውም በሚል ውድቅ ያደረጉት ሲሆን የመሃል ዳኛው ግን “ከዚህ በኋላ ይህን ጉዳይ ነፃ ሆኜ ለማየት ስለምቸገር ከዛሬ ጀምሮ ጉዳዩን  እኔ አልከታተልም፤ ይህንም ለፍ/ቤቱ አስተዳደር በማመልከቻ ጠይቄያለሁ” ብለዋል፡፡
ጦማሪያኑና ጋዜጠኞቹ$ ሰብሳቢ ዳኛው በተለያየ ጊዜ ሃሳባችንን እንዳንገልፅ ተፅዕኖ አሳድረውብናል፣ ክርክሩ ሂደት የተፋጠነ ፍትህ እንዳናገኝ  የሚመሩትን ችሎት በቸልተኝነት ተመልክተዋል፣ አቃቤ ህግ ክስ አሻሽል ተብሎ የተሰጠውን ጊዜ ሳይጠቀም ሲቀር እንደማስቆም የተለያየ እድል እየሰጡ=@ የእኛ የመቃወሚያ ክስ ውድቅ እንዲሆን አድርገዋል፣ አቃቤ ህግ አሻሽል የተባለውን ክስ እንዳላሻሻለ እያወቁ የተሻሻለ በማስመሰል በክስ ውስጥ አካተተዋል፣ እኛ ያቀረብናቸውን በርካታ የመቃወሚያ ክሶች በአግባቡ ሳያዩ ውድቅ አድርገዋል… የሚሉ አቤቱታዎችን በማቅረብ ነበር እንዲነሱላቸው ፍ/ቤቱን የጠየቁት፡፡
የተከሳሾቹ ጉዳይ በአዲስ ሰብሳቢ ዳኛ መታየት ይጀምራል አይጀምርም በሚል ያነጋገርናቸው የተከሳሾቹ ጠበቃ አቶ አመሃ መኮንን፤ “በእርግጥ የመሃል ዳኛው ከዚህ በኋላ የተከሳሾቹን ጉዳይ አላይም ብለዋል፤ እርሳቸው ለዳኞች አስተዳደር ማመልከቻ ያስገቡ በመሆኑ ከችሎቱ ይነሱ ወይም ይቀጥሉ የሚለውን የሚወስኑት አለቆቻቸው ናቸው” ሲሉ  አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡በተያያዘ ዜና ሰባተኛ ተከሳሽ አቤል ዋበላ፤ በሀሙሱ ችሎት ለፍ/ቤቱ አቤቱታ ያቀረበ ሲሆን ማክሰኞ እለት ከችሎት በኋላ ወደማረሚያ ቤት ሲመለስ “እጅህ ላይ ለምን ካቴና አላደረግህም” በሚል በአጃቢው ፖሊስ መኪና ውስጥ እያለ አፀያፊ ስድብና ዛቻ እንደደረሰበትና ማረሚያ ቤት እንደደረሰም በትልቅ ሰንሰለት እጁ ታስሮ ማደሩን ለፍ/ቤቱ ተናግሯል፡፡ “ከዚህ ቀደም ማዕከላዊ እስር ቤት እያለሁ በደረሰብኝ ድብደባ አንድ ጆሮዬ ከጥቅም ውጭ በመሆኑ ለመስማት የሚያግዝ መሳሪያ በጆሮዬ አደርግ ነበር” ያለው ተከሳሹ፤ የማዳመጫ መሳሪያውን እንደተቀማና “አኮላሽሃለሁ፤ ሬሳህ ከዚህ ማረሚያ ቤት ይወጣል” የሚል ዛቻ እንደደረሰበት ለፍ/ቤቱ አቤቱታውን አቅርቧል፡፡ ፍ/ቤቱ የእለቱን የማረሚያ ቤት ተወካይ ስለጉዳዩ ቢጠይቅም፤ ተወካዩ ስለ ጉዳዩ ምንም የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ገልጿል፡፡ ተወካዩ ጉዳዩን አጣርቶ ምላሽ እንዲሰጥ፣ አቤቱታ

አቅራቢው ተከሳሽም አቤቱታውን በፅሁፍ እንዲልክ ትዕዛዝ የሰጠው ፍ/ቤቱ፤ የተከሳሾቹን የእምነት

ክህደት ቃል ለመስማት ለየካቲት 11 ቀን 2007 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡  

Read 1491 times