Saturday, 07 February 2015 12:27

የለቡ አካባቢ ነዋሪዎች የተጣለባቸውን የመሬት ግብር ተቃወሙ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

“ክፍያውን በቀድሞ ታሪፍ መቀጠል ይችላሉ፤ ቤታቸው ግን መለካት አለበት” - የወረዳው አስተዳደር

   በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1፣ በተለምዶ ለቡ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የሚገኙ ከ25 ሺህ በላይ ነዋሪዎች በካሬ ሜትር 0.50 ሳንቲም ሲከፍሉ የቆዩት የመሬት ግብር ወደ 3 ብር ማደጉ አግባብ አይደለም ሲሉ ተቃወሙ፡፡ ከ1990 ዓ.ም  አንስቶ የመኖሪያ ቤት በማህበር ለመስራት ከመንግስት በሊዝ ቦታ መመራታቸውን ያስታወሱት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ቦታውን ሲወስዱ በካሬ ሜትር 0.50 ሳንቲም ሊከፍሉ መስማማታቸውንና እስከ 2005 ድረስ በተመሳሳይ ክፍያ መቀጠላቸውን ጠቁመው ከዚያ በኋላ በካሬ ሜትር ሶስት ብር እንዲከፍሉ መደረጋቸውን ይናገራሉ፡፡“ይህን ክፍያ የከፈልነው በአስሩም ክፍለ ከተማ መመሪያ የወጣ መስሎን ነበር” ያሉት የቅሬታ አቅራቢዎቹ ተወካይ፤ በኋላ ጉዳዩን ሲያጣሩ ግን ከ1996 ዓ.ም በፊት ቦታ የተመሩትን የሶስት ብሩ ክፍያ እንደማይመለከታቸው ማወቃቸውን ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ ላለፉት ሁለት ዓመታት ያላግባብ የከፈሉት ክፍያ እንዲመለስላቸውና በ0.50 ሳንቲም ክፍያቸውን እንዲቀጥሉ በየተዋረዱ ላሉ የመንግስት መስሪያ ቤቶች አቤት ቢሉም ምላሽ ማጣታቸውን የተናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ከጥቂት ወራት በፊት ችግራቸውን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት መናገራቸውንም አስታውሰዋል፡፡ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት ኃላፊዎችም በሬዲዮ ፋና ቀርበው፣ ከ1996 በፊት በሊዝ ቦታ የወሰዱትን በካሬ ሜትር 3 ብር ክፍያ እንደማይመለከታቸው ማረጋገጣቸውን ጠቅሰው፤ እነዚሁ ኃላፊዎች ወረዳው በአስቸኳይ መፍትሄ ሊሰጣቸው እንደሚገባ መግለፃቸውንና ለወረዳው መሬት አስተዳደር የትዕዛዝ ደብዳቤ መፃፉን ነገር ግን እስካሁን ምላሽ አለማግኘታቸውን ይናገራሉ፡፡ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን በሌሎች ክፍለ ከተሞች ተመሳሳይ ስህተት ተፈፅሞ ከሆነ እንዲታረም በፃፈው ደብዳቤ፤ ከ1996 ዓ.ም በፊት በእጣና በምደባ ቦታ ተሰጥቷቸው በሊዝ ውል የገቡ ነዋሪዎች አዲሱ ታሪፍ እንደማይመለከታቸው መግለፁንም ጠቅሰዋል፡፡
“እኛ ቤቱን የሰራነው መንግስት በሰጠን ፕላንና መመሪያ ነው፤ ከአፈር ግብር በተጨማሪም ጣሪያና ግድግዳ አስለክተን የከፈልንበት ደረሰኝ አለን” ያሉት ተወካዮቹ፤ የፕላንና የካርታ ለውጥ ሳያደርጉና ቤት በፎቅ መልክ ሳይቀጥሉ ይለካ መባሉ ግራ እንዳጋባቸው ነዋሪዎቹ ገልጸዋል፡፡ መንግስት አስለካሁ ካለ ማስለካት እንደሚችል፤ ነገር ግን ለመሃንዲስ 500 ብርና ለታክሲ 300 ብር ክፈሉ መባላቸውን እንደማይቀበሉት ነዋሪዎቹ በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡ ጉዳዩን በተመለከተ ያነጋገርናቸው የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ፣ የወረዳ አንድ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ታሪክ ፍቅሬ፤ የነዋሪዎቹ ቅሬታ ተገቢነት እንዳለው አልካዱም፡፡ ወደ ኃላፊነቱ ከመጡ ገና 15 ቀናት ብቻ እንዳስቆጠሩ የጠቆሙት ዋና ስራ አስፈፃሚው፤ 0.50 ሳንቲም መክፈል እያለባቸው በካሬ ሶስት ብር መክፈላቸው ስህተት መሆኑን አምነው፣ እስከዛሬ የከፈሉት እላፊ ሂሳብ በወደፊት ክፍያቸው ላይ ይታሰብ ወይስ ይመለስላቸው በሚለው ላይ ከሌሎች ኃላፊዎች ጋር ተነጋግረው ምላሽ ለመስጠት ለፊታችን ረቡዕ ቀጠሮ መያዙን ገልፀዋል፡፡ ከአሁን ጀምሮ ነዋሪዎቹ ክፍያቸውን በ0.50 ሳንቲም መቀጠል እንደሚችሉ የተናገሩት አቶ ታሪክ፤ ነገር ግን የቤቱን ግድግዳና ጣሪያ የማስለካት ግዴታ እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡ ቅሬታ አቅራቢዎቹ በበኩላቸው፤ አሁን ክፍያ እንድንፈፅም ጠይቀን ካላስለካችሁ መክፈል አትችሉም ስለተባልን ግራ ገብቶናል፤ ለቅጣትም ልንዳረግ ነው ብለዋል፡፡ አቤቱታቸውን ለወረዳው ገቢዎች ፅ/ቤት ሊያቀርቡ ገብተው በጽ/ቤቱ ኃላፊ ዘለፋና ስድብ እንደደረሰባቸው የገለፁት ተወካዮቹ፤ ህዝብን ሊያገለግሉ የተቀመጡ ሰዎች አያቶቻቸው የሚሆኑ ሰዎችን መሳደብና ማዋረዳቸው አግባብ አይደለም ሲሉ ነቅፈዋል፡፡ የወረዳው ዋና ስራ አስፈፃሚ፤ የቤት ማስለካቱ ጉዳይ ተገቢ ነው አይደለም፣ በሶስት ብር ሂሳብ የከፈሉት ክፍያ ልዩነቱ ታስቦ ይመለስ ወይስ በወደፊት ክፍያቸው ላይ ታሳቢ ይሁን፣ ለመሃንዲስና ለታክሲ ይከፈል የተባለው 800 ብር ተገቢ ነው አይደለም የሚለውንና ተያያዥ ጉዳዮችን ከሌሎች የስራ ኃላፊዎች ጋር መክረው የፊታችን ረቡዕ ምላሽ እንደሚሰጡ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡     

Read 2284 times