Saturday, 07 February 2015 12:34

የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት ከ90 ሚሊዮን አላለፈም ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(19 votes)

አለማቀፍ ተቋማት ወደ 100ሚ. ይጠጋል ይላሉ

   የተለያዩ አለማቀፍ ተቋማት ሪፖርቶች የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት ወደ 100 ሚሊዮን ተጠግቷል ቢሉም የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የሃገሪቱ ህዝብ ከ90 ሚሊዮን አላለፈም ብሏል፡፡ ኤጀንሲው ትናንት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ከህዝብ ቆጠራ የተገኘ መነሻ የህዝብ ብዛት፣ ከስነ ህዝብና ጤና ጥናቶች የተገኙ የውልደትና የሞት መጠን፣ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎትና የፍልሰት መጠን ስሌትን ጨምሮ የተባበሩት መንግስታት ስነ ህዝብ ተቋም የህዝብ ትንበያ አሰራርን በመከተል በተዘጋጀው ስሌት የዚህ ዓመት የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት 90 ሚሊዮን ነው ብሏል፡፡ ከጠቅላላው የህዝብ ብዛት ውስጥ 45 ሚ. 250 ሺ ወንዶች ሲሆኑ 44 ሚ. 825 ሴቶች መሆናቸውን የኤጀንሲው ትንበያ ያስረዳል፡፡ በኢትዮጵያ በአሁን ሰዓት አንድ እናት በአማካይ 4 ልጆች ትወልዳለች ተብሎ እንደሚገመትም ሪፖርቱ ይፋ ያደረገ ሲሆን የህዝብ ብዛቱ ከቁጥጥር ውጪ እንዳይሆን ዘመናዊ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ግንዛቤን በመፍጠር ለህብረተሰቡ ተደራሽ እየተደረገ ነው ተብሏል፡፡ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ሽፋኑም ወደ 40 በመቶ መድረሱን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
የሃገሪቱ የህዝብ ብዛት ከክልሎች አንፃር በተቀመጠው መረጃ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ፣ ሶማሌ እና ትግራይ በቅደም ተከተላቸው ከ1-5 ያለውን ደረጃ የያዙ ሲሆን በ1999 ዓ.ም በተደረገው የቤትና የህዝብ ቆጠራ 2.7 ሚሊዮን እንደነበር የተገለጸው የአዲስ አበባ የህዝብ ብዛት ወደ 3.2 ሚሊዮን ከፍ ማለቱ በሪፖርቱ ልክቷል፡፡ ኢትዮጵያ በህዝብ ቁጥሯ ከአፍሪካ ሃገሮች ከናይጄሪያ ቀጥላ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ ከ50 ዓመት በኋላ ከአፍሪካ 1ኛ ትሆናለች የሚለው የተለያዩ ተቋማት ትንበያ ትክክል እንዳልሆነና
የስታትስቲክስ ኤጀንሲው የትንበያ ቀመር፣ የህዝብ ቁጥር እድገት አማካይ መጠኑ እየቀነሰ እንደሚሄድ የኤጀንሲው የስራ አመራሮች ገልፀዋል፡፡ ኤጀንሲው የመረጃ ክፍተቶችን ያስወግዳል ያለውን 4ኛውን የህዝብና ቤት ቆጠራ ከ3 ዓመት በኋላ በ2010 ዓ.ም ለማካሄድ የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶችን እያደረገ መሆኑም ተመልክቷል፡፡ የሃገሪቱ የህዝብ ብዛት ከ5 ዓመት በኋላ 100 ሚሊዮን እንደሚደርስና ከ20 ዓመት በኋላ ወደ 136 ሚሊዮን እንደሚጠጋ የኤጀንሲው የህዝብ ብዛት ትንበያ ያመላክታል፡፡ በሌላ በኩል የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት በዘንድሮው ዓመት ከ98 ሚሊዮን ልቋል የሚል ሪፖርት ያወጣ ሲሆን ከ150 በላይ የሚሆኑ የዊኪፒዲያ ተቋማት እንደመረጃ ምንጭ የሚጠቀሙትና አለማቀፍ አጥኚዎችን በስሩ ያሰባሰበው “ዎርልድ ሜትር” በበኩሉ፤ የህዝብ ብዛቱ 98 ሚሊዮን 942 ሺህ መድረሱን ይፋ አድርጓል፡፡ የተባበሩት መንግስታት ሪፖርት ደግሞ የህዝብ ብዛቱ 92 ሚሊዮን ደርሷል ብሏል፡፡

Read 18281 times