Saturday, 07 February 2015 12:48

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ም/ቤት ፕሬዚዳንት፤ ከስልጣኔ አልወረድኩም አሉ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(8 votes)

የመፈንቅለ መጅሊስ ሙከራው ስርዓት አልበኝነት ነው ብለዋል
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ኪያር ሼህ መሃመድ አማን አህመድ፤ ከስልጣናቸው አለመውረዳቸውንና በቅርቡ በኦሮሚያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት የተሰጠውን መግለጫ በጥብቅ እንደሚቃወሙ ገለፁ፡፡ በቴሌቪዥን “የኦሮሚያ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ስራ አስፈፃሚዎች በህገ ወጥ መንገድ ስርዓት አልበኝነትን ተላብሰው፣ ‹እኛ የኢትዮጵያ ፌደራል መጅሊስ ፕሬዚዳንቶች ነን› በማለት በመንግስት ሚዲያዎች መግለጫ መስጠታቸው ህገወጥ ድርጊት ነው” ብለዋል-  ፕሬዚዳንቱ ሰሞኑን በፅ/ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፡፡ የአንድ ክልል ሥራ አስፈፃሚ በፌደራል ጉዳይ ጣልቃ ገብቶ እከሌን አባረናል፣ እከሌን አግደናል ማለቱ ከህግና መመሪያ ውጪ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በህገወጥነት ህጋዊ መሆን ስለማይቻል ግለሰቦቹ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አሳስበዋል፡፡
የህዝበ ሙስሊሙ ትልቅ ተቋም የሆነውን መጅሊስ ጥቂት ስርዓተ አልበኞች ሊያምሱትና ሊያተራምሱት እንደማይችሉ የተናገሩት የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት፤ “እኔ ለሥራ ጉዳይ ከአገር በወጣሁ ቁጥር መፈንቅለ መጅሊስ ለማድረግና በህገወጥ መንገድ ስልጣን ለመያዝ ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ቀርቷል” ብለዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ኦሮሚያን ጨምሮ ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ የስራ አስፈፃሚ አባላት ተመሳሳይ የመፈንቅለ መጅሊስ ሙከራ አድርገው ከሃላፊነታቸው መታገዳቸውን ፕሬዚዳንቱ ታውሰዋል፡፡
“ከሁለት ዓመት በፊት በህዝብ ተመርጠን፣ ህዝበ ሙስሊሙን ለማገልገልና መንግስትን ለመርዳት
ወደ ስልጣን መጥተናል” ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ይህንን ህጋዊ አሰራር ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆኑ ጥቂት
ህገወጥ ግለሰቦች የሚፈፅሙት ስርዓተ አልበኝነት መቀጠል እንደማይችል ተናግረዋል፡፡ በሌላ በኩል በየዓመቱ በየካቲት ወር የሚካሄደውን ጠቅላላ ጉባኤ ለማድረግ በዝግጅት ላይ እንደሚገኙ የገለፁት ፕሬዚዳንቱ፤ በጉባኤው ላይ አሉ የተባሉ ችግሮችን በማንሳት ውይይት ተደርጐበት ውሳኔ እንደሚተላለፍ ተናግረዋል፡፡ በህገወጥነት ታግደው የቆዩት ሥራ አስፈፃሚዎች ጉባኤው ከፈቀደላቸው ብቻ በጠቅላላ ጉባኤው እንደሚሳተፉ ተናግረዋል፡፡ ኦሮሚያ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት በቅርቡ ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በሰጠው መግለጫ፤ የፌደራሉ መጅሊስ ፕሬዚዳንት፤ ያለአግባብ የስራ ኃላፊዎችን በማገዳቸውና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው ከስልጣናቸው መውረዳቸውንና ክልሉም ውክልናውን ማንሳቱን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡  


Read 4026 times