Saturday, 07 February 2015 13:43

ልቻል ወይስ ልድፈር?

Written by  ረጀ ይመር
Rate this item
(15 votes)

          ጉሮሮዬን በቀዝቃዛ ቢራ ለማርጠብ ወደ አንድ ምሽት ክበብ ደጃፍ ስደርስ አፍታም አልፈጀብኝም። ደጃፉን አልፌ ወደ ውስጥ እንደዘለቅሁ አንዲት እንስት አቀንቃኝ በታዳሚው የጋለ ጭብጨባ ታጅባ ወደ መድረኩ እየተውረገረገች ስትወጣ ተመለከትኩ። የቤቱ ኮከብ ዘፋኝ ትመስላለች። በእርግጥም ኮከብ ነች፡፡ ማይኩን ጨብጣ ተስረቅራቂ ድምጿን ስትለቀው አጃኢብ ነው። ድምጿን ስታወጣ ግብግብ የለም፡፡ ዝም ብሎ መስረቅረቅ ብቻ …
ተሰጥዖን ሲያገኙ እንዲህ ነው፡፡ ተሰጥኦ ባለበት የትግል ዱካ ይሸሸጋል፡፡ ዶልፊን ውሃ ላይ ለመሰልጠን ክንፎቹን እና ጭራውን ዝግጁ ማድረግ ብቻ ነው የሚጠበቅበት፡፡ ዝግጁ ሲሆን ይከናወንለታል፡፡ ልክ እንደ መተንፈስ፡፡ ጥረት እና ትግል ለተሰጥኦ ምኑም አይደሉም፡፡ እንስቷ ማቀንቀንን ስለወደደች ብቻ ሁሉም ነገር በቀና እየሄደላት ነው፡፡
አቀንቃኟን ትክ ብዬ ሳስተውላት ግን ግራ ሆነችብኝ፡፡ ድምጿ ወዲህ፣ ስሜቷ ወዲያ ሆኖ አጥበረበረኝ፡፡ ከፊቷ የሚነበበው ስሜት ድንዛዜ ነው፡፡ በስጋዋ ልግምና ላይ ተሰጥኦዋ ቢታከልበት ኖሮ መስረቅረቁን ውሃ በበላው ነበር፡፡ ግን አልሆነም፡፡ ከተራበ ጆሮ አንጀት የሚጠጋ ውብ ዜማ ከለገመው ገላዋ ላይ ማስወንጨፏን ቀጥላለች።
ከየማዕዘናቱ የሚያስተጋባ፣ ባዶነትን ያረገዘ ቅላጼ አሁንም አሁንም እየወተወኝ ነው፤ ውትወታውን በጄ ማለት እንዳለብኝ ወሰንኩ፤ ስለ ውብ ቅላጼ …ስለ ለገመ ገላ … ስለ ዜመኛዋ ውስጠ ወይራነት … ላወጣ ላወርድ … ተነሳሳሁ፡
በእርግጥም ይህቺን ውብ ዜመኛ ከተጣባት ልግምና በስተጀርባ አንድ ጥላ አጥልቷል፡፡ ጥላው  ለመኖር መታዘዝ ነው፡፡ የታዘዘችውን ካልከወነች እህል ውሃ ያከትማል፡፡ ተሰጥኦዋ ብልፅግና እንደተጠየፈ ይኸው እንዳለች አለች፡፡ ከተሰጥኦዋ የተረፋት ጥሪት ቢኖር ማገልገል ብቻ ነው፡፡ ታዛዥነቷ በተሰጥኦዋ ጉያ ውስጥ ተሸሽጎ ጎለመሰ እና ቀናት ቀናትን ሲወልድ ለአይን የሚያጠግብ  ወደል ሆኖ ታያት፡፡ ለምሽት ክበቡ ማቀንቀን አሀዱ ስትል፣ ከሀሴት ጋር ጫጉላ ላይ ነበረች፡፡ ያኔ ታዛዥነቷን፣ አገልጋይነቷን ዞር ብላ የምታማትርበት አንገትን አልተቸረችም፡፡ ብታማትረውም ገና ከእቅፍ ያልወረደ ጨቅላ ስለነበረ ቁብ አትሰጠውም፡፡ ጥቂት አገልጋይነት ብዙ ደስታ ነበራት፡፡ በስኳር የተቀባ መራራ መድሃኒት፣ ስኳሩ እስከሚያልቅ መጣፈጡን ይቀጥላል፡፡ የስኳር መጠኑ ሲያልቅ፣ ለመራራው ጣዕም ቦታውን ያስረክባል፡፡ ስኳር አልቆባት ከመራራው ጋር እየተጋፈጠች ነው። ከንፈሬን መጠጥኩላት፡፡ አሁን ይህች አቀንቃኝ ለድፍረት ነው ለችሎታ እጅ ያጠራት?
“ምን ልታዘዝ?” የሚል የአስተናጋጅ ድምጽ፣ ለጥያቄው መልስ እንዳላፈላልግ ለጊዜውም ቢሆን ገታ አደረገኝ፤
የምጠጣው ቢራ ከጉሮሮዬ አልወርድ እያለ ቢታገለኝም፣ ለሞቅታ ብዙም ጊዜ አልፈጀሁም። ሞቅታዬ ግን ቅድም ብልጭ ያለብኝን ጥያቄ ማሸነፍ  አልተቻለውም፡፡ ከድፍረት እና ከተሰጥኦ ማን ያስከነዳል? በእርግጥም ይህቺ ውብ አቀንቃኝ ከድፍረት ጋር ዓይን እና ናጫ ባትሆን ኖሮ እንዲህ በቢራ ለሚነፍዘው ታዳሚ ከመባከን አልፋ ለሀገር ምድሩ በበቃች ነበር፡፡ የአቀንቃኟ ሁኔታ ከበቀቀኗ ታሪክ ጋር ተገጣጠመብኝ፡፡ በቀቀኗ በታጠረላት ሽቦ (ኬጅ) ውስጥ ሆና ወዲህ ወዲያ ትበራለች። መብረር ተሰጥኦ ቢሆንም ከሽቦ ወሰን በላይ ፈቀቅ ማለት አልቻለችም፡፡ ሰማይ እየገመሰች መብረር ተክና፣ ክንድ በማትሞላ አጥር ውስጥ መንከላወሷ ምቾት ስላልሰጣት፣ የአድኑኝ ጩኸት ማሰማቷን ቀጥላለች፡፡ በጩኸቱ ልቡ የተነካ ደግ ሰው ወደ ሽቦው ተጠግቶ በሩን ከፈተና ወደ ሰማይ ለቀቃት። የተወሰነ ርቀት እንደተጓዘ ግን በድጋሚ ጆሮው የበቀቀኗን የአድኑኝ ጩኸት ይሰማው ጀመረ። መለስ ብሎ ወደ ኬጁ ሲጠጋ በቀቀኗ ልክ እንደ በፊቱ ከኬጁ ውስጥ ሆና እየጮኸች ነው፡፡ አሁን ግን የኬጁ መዝጊያ ወለል ብሎ ተከፍቷል። በቀቀኗን መርዳት ባለመቻሉ እያዘነ ተለያት፡፡ በቀቀኗ ከኬጁ ውጪ ያለው ህይወት ከማያውቁት መልአክ ሆኖባታል፡፡ ተሰጥኦዋን በሽቦ አጥሩ ልክ ገድባ መኖርን መርጣለች፡፡ በሌላ ጐን ደግሞ ደፋር መሰሎቿ በየዳሩ እንዳሻቸው እየከነፉ ከምንጩ ውሀ እየተጐነጩ፣ ከመስክ ላይ ጥሬ እየለቀሙ የሚኖሩት ኑሮ አስቀንቷታል፡፡ መብረር የሚችሉት ይቅርና ገና የተጐነደሸ ክንፍ ያላቸው ጫጩት በቀቀኖች ሳይቀሩ ከእርሷ በተሻለ ደፍረው ከቅርንጫፍ ቅርንጫፍ ይዘላሉ፡፡ የመብረር ተሰጥኦዋ ከጫጩቶቹ እጅግ ቢልቅም ድፍረት ስላነሳት ከእነርሱ በተሻለ በአደባባይ ልትታይ አልቻለችም፡፡
የእንስቷን አቀንቃኝ ተሰጥኦ ለማየት የታደሉት በምሽት ክበቡ ቅጥር ግቢ ውስጥ የታደሙት ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡ ከቅጥር ግቢ ባሻገር ላለው ህዝብ ተሰጥኦዋ ባይተዋር ነው፡፡ ታዲያ እንዲህ አላላውስ ብሎ ቀፍድዶ የያዛት አባዜ ምንድን ነው? መፅሐፍ ቅዱስ የትጉህ እጅ አለምን ይገዛል ይላል፡፡ ይህ አባባል ለደፋሮች ቦታ የለውም፡፡ ደፋሮችም ለአባባሉ ቁብ አይሰጡም፡፡ ከትጋት ይልቅ ለብልጠት ይባትታሉ። ባትተውም አይቀሩም፤ በመጨረሻ ሲያሸንፉ ይታያሉ፡፡ የቀዬው አድባር ልቡ የሚሸፍተው ለሚደፍሩ እንዲ ለሚችሉ አይደለም፡፡ ጥያቄው ደፋር እንድሆን ማን ያስተምረኝ ነው? መልስ የለም፤ ከራስ ጋር ሙግቱ ቀጥሏል፤ የጠየቅሁት ጥያቄ እንደ ገደል ማሚቱ ተመልሶ ይሰማኛል፡፡
እንስቷ አቀንቃኝ መድረኩን ለሌላ አቀንቃኝ ለቃ ወርዳለች፡፡ ቅድም ክፍት ቦታ በብዛት ይታየኝ ነበር፡፡ አሁን ግን መፈናፈኛ እስኪታጣ ሁሉም መቀመጫዎች በታዳሚዎች ተይዘዋል፡፡ ከእኔ ቅርብ ርቀት ያሉት ቦታዎች በታዋቂ ሰዎች ምርኮ ስር ወድቀዋል፡፡ ታዳሚው ውስጡን በቢራ፣ አይኑን በታዋቂ ሰዎቹ ፊት እያጠበ መዝናናቱን ተያይዞታል። ታዋቂዎቹም ከታዳሚው ያገኙት ከልክ ያለፈ እንክብካቤ ሙቀት ጨምሮላቸው ልባቸውን እንደ ተራራ ቆልለዋል፡፡
“የደፋሮች ሀገር” ብዬ ከብርጭቆ ውስጥ የቀረችውን እንጥፍጣፊ ቢራ ወደ ጉሮሮዬ ላኳት፡፡
እነዚህ ባለ ጉንድሽ ክንፍ ደፋሮች ከእንስቷ አቀንቃኝ ሲነፃፀሩ መብረር ቢሳናቸውም እየዘለሉ መራቅ ችለዋል፡፡ ለተሰጥኦ እጅ ቢያጥራቸውም ለድፍረቱ ግን አልተቸገሩም፡፡ ለድፍረታቸው ምስጋና ይግባው እና ሁሉንም ዘርፍ እንዳሰኛቸው አክሮባት ይሰሩበታል፡፡ ለነገሩ የሚጠብቅባቸውን ግብር ነው ለአውደ ርዕይ ያቀረቡት፡፡ ባለተሰጥኦዎች ተሟልተው ወደ አደባባይ እስኪወጡ ድረስ እጃቸውን አጣጥፈው ይቀመጡ ማለት ኢ-ምክናያታዊ ነው፡፡ “If you wait until you become perfect, you will wait forever” የሚለውን የፈረንጆቹን አባባል ከባለ ተሰጥኦዎቹ በተሻለ ደፋሮቹ ተረድተውታል። ባላቸው ጉንድሽድሽ ክንፍ ለመብረር ይሞክራሉ፡፡ ለሚያያቸው ሰው የሚበሩ ይመስላሉ፡፡ በመብረር ህግ ግን መሬት ለቀቁ እንጂ በረሩ አይባልም። ከእይታ ገሸሽ አሉ እንጂ አልጠፉም፡፡ የሀሳብ ትርምሱ ከቤቱ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ወርውሮ አውጥቶኝ ነበር፡፡ አሁን ወደ ቤቱ ተመልሻለሁ፡፡
ቤቱ ውስጥ የማየው ትእይንት ምንም ሰላም ሊሰጠኝ አልቻለም፡፡ ሁሉም የሚጠጣው የሚዝናናው አንዱ አንዱን እየጠበቀ ነው፡፡ ክብር እና ሞገስ ለሞቅታ እንኳን እጅ መስጠት አልቻሉም፡፡
ኪሴን ስዳብሰው ሟሽሿል፡፡ ብዙ ሳልሟሟቋ የያዝኳቸው የብር ኖቶች ጭዳ መሆናቸው ሰላም አልሰጠኝም፡፡ የቀበሌ መዝናኛ ውል አለኝ፡፡ እንደ እናት ጓዳ ያለስስት የሚቃመሱበት፤ በጥቂት የብር ኖቶች በርከት ያሉ ባለ አረንጓዴ እና ቢጫ ቦኖዎችን እጅ በእጅ የሚቀባበሉበት፤ ቦኖዎችን ተገን አድርጐ የከርስን ውትወታ በነፃነት አደብ የሚያስገዙበት፡፡ ሰዓቱ ባይገፋ ቀሪ የስራዬን ምስ እኔም እንደ ወዳጆቼ እዚያው ለማግኘት እንደረደር ነበር፡፡ ይህ ግን እንዳይሆን ምሽቱ ነጉዷል፡፡ ክበቦቹ ደርግ ላወጀው ሰዓት እላፊ ቃል አባይ ላለመባል በታማኝነት የፀኑ ናቸው፡፡ እነዚህ ገራገር የብዙሃን ማጀቶች፣ “ሶሻሊዝም” ትቶ ያለፋቸው የህዝባዊነት ዳናዎች፤ ለአይን ያዝ እንዳደረገ ፍጥምጥ ማለትን ያውቁበታል፡፡ በእርግጥም ተፈጣጥመዋል፡፡ በእዚህ ሰዓት ወዴትም መላወስ የሚበጅ አይደለም፡፡ አንዱን ይዤ አንዱን መጣሌን ቀጥያለሁ፤ ድንገት ከወለል ጋር የተሳሳመ የቢራ ጠርሙስ ከሰጠምኩበት የምናብ ንትርክ ጐትቶ አወጣኝ፡፡
ድፍረቱም ተሰጥኦውም ድብልቅልቅ ብለውብኝ ስምታታ ኖሬያለሁ፡፡ ልድፈር ወይስ ልቻል? አሁንም ጥያቄው አልተመለሰም፡፡
የፅድቁ መንገድ የትኛው ነው? የእንስቷ ወይስ የታዋቂ ሰዎቹ? የታዋቂ ሰዎቹን መንገድ ይሻለኛል ብል “የጭቦ ክህነት ይቅርብህ” የሚል ተግሳፅ አዘል ሀይለኛ ድምፅ በውስጤ ያስተጋባል ብዬ ፈራሁ፡፡
አይ የእንስቷን መንገድ ልከተል ብዬ ብደመድም “ባክህ ተሰጥኦ ለበቀቀኗም አልጠቀመ” እያለ የሚሳለቅብኝ መሰለኝ፤ ታዲያ ብችል ነው ብደፍር የሚሻለው፡፡
ላም እሳት ወልዳ አይነት ምርጫ ሆነብኝ፤ እንደምንም ጥሪት ቋጥሬ፣ የቢራ አምሮቴን ልቆርጥ ፈልጌ ካልጠበቅሁት የሃሳብ ጋጋታ ጋር ስፋለም አመሸሁ፡፡
የእንስቷ አቀንቃኝ ድምፅ ተመልሶ ተሰማኝ፡፡ ከቅድሙ በተዛነፈ ሁኔታ ለዘፈኑ የምትደረድራቸው ስንኞች ቤት የማይመቱ ስድ ንባቦች ሆነው ወደ ጆሮዬ ይንቆረቆራሉ፡፡ ተስረቅራቂ ድምጿን ከሞቅታ ጋር ስሰማው የጣር ድምፅ ሆኖ ውስጤን ሸነቆጠኝ። የበቀቀኗ የአድኑኝ ተማፅኖ በእንጉርጉሮ መልኩ የመጣ መሰለኝ፡፡ እባክሽ እህቴ ደፈር በይ፤ መቻል ለበቀቀኗም አልጠቀመ… ብዬ የሚከተለውን ስንኝ በመቋጠር ከቤቱ ውልቅ ብዬ ወጣሁ፡፡
ሀገሬ ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ
የቻለብሽ ቀርቶ የደፈረሽ በላ  

Read 3980 times