Saturday, 14 February 2015 13:19

የሰሜን ብርድ ከማትወድደው ጋር ያስተቃቅፋል!

Written by 
Rate this item
(12 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን ዕመት ጦጢት ዘር ልትዘራ ወደ እርሻ ቦታ ትሄዳለች፡፡ ከዚያም በሰፊው እርሻ

ላይ በመት በመት ስትዘራ ትታያለች፡፡
በእርሻው ዳር የሚያልፈው ሰው ሁሉ ጥያቄ ይጠይቃል፡፡
ጦጢት ምን ዘራሽ?“ ይላታል አንዱ፡፡
“ዘንጋዳ” ትላለች ጦጢት፤ ኩራቷ ፊቷ ላይ እየተነበበ፡፡
“ጦጢት ምን ዘራሽ?” ይላታል ሁለተኛው፡፡
“ስንዴ!” ትላለች ጦጢት፡፡
“ጦጢት ምን ዘራሽ?” ይላታል ሌላው፡፡
“ጤፍ!” ትላለች፡፡
“ጦጢት ምን ዘራሽ?” ደሞ ሌላው፡፡
“አተር!” ትላለች፡፡
አንዳቸውም ከእጁዋ የሚወጣውን ዘር አለማየታቸው እየገረማት ነው መልስ የምትሰጠው፡፡ የመጨረሻው ሰው መጣና፣ “እሜት ጦጢት፣ ምን ዘራሽ?” አላት
“ባቄላ!” አለችው፡፡
“እንዲያው ባቄላ እዚህ መሬት ላይ ይበቅል ይመስል … ምን ይበጅሻል?
“ማምሻውን ሁኔታውን እዩ?” ብላ መለሰች፡፡ ጦጢት ስትዘራ ስትታይ ዋለችና ወደ ማታ ወደ እርሻው ተመልሳ መጣች፡፡ ከዚያም ቀን ስትዘራ የዋለችውን ዘር እንደገና ከእርሻው እያወጣች ስልቻዋ ውስጥ ትከት ጀመር፡፡ ቀን ስትዘራ ያዩዋት ሰዎች ከገበያ ሲመለሱ የምታደርገውን አይተው በመገረም፤ “እመት ጦጢት፤ ብልጥ የነበርሺው ሴትዮ አሁንስ ተጃጃልሽ መሰል! ደሞ ምን ልሁን ብለሽ ነው

የዘራሽውን መልሰሽ የምትለቅሚው?”
ጦጢትም፤
“ወዳጆቼ! ያለንበት ዘመን አያስተማምንም! የያዙትን ይዞ ወደ ቤት ክትት ነው የሚሻለው፡፡ ንብረትን በእጅ ይዞ ማደርን የመሰለ ነገር የለም!!” ብላ መለሰች፡፡
*                  *               *
በማናቸውም የህይወታችን መንገድ ጥርጣሬን ይዘን ከተጓዝን ዕቅዳችን በቅጡ አይሳካም፡፡ የምናደርገው ነገር ሁሉ ልባዊ አይሆንምና ውሽልሽል አጥር ነው የምናጥረው፡፡ ውሽልሽል አጥር ለአደጋ የተጋለጠ ነው፤ እንደጦጢት የምንዘራውን እየደበቅን መጓዝ፣ አልፈን ተርፈንም የዘራነውን መልሰን መልቀምና ይዘን ማደር ግዴታ እስኪሆን ድረስ ኑሮአችን ያልተረጋጋ ይሆናል፡፡ ያልተረጋጋ ዲሞክራሲ፣ ያልተረጋጋ  ፖለቲካን ነው የሚወልደው፡፡ ያልተረጋጋ ፖለቲካ ያልተረጋጋ ኢኮኖሚን ነው ይዞ እሚያዘግመው፡፡ የዚህ ባለቤት የሚሆነው ያልተረጋጋ ህዝብ ነው፡፡ ህዝብ ሲጠራጠር ደግ አይደለም፡፤ ይሄን ልብ ብሎ ማስተዋል ይጠይቃል፡፡ ሼክስፒር እንደሚነግረን፣
“ግን እንደዚሁ እንደህንፃ፣ ላዩ በሰም አንፀባርቆ
አካባቢው በጌጥ ደምቆ
መሰረቱ ግን በግድፈት፣ በአገም ጠቀም ተደባብቆ
በመሀንዲስ ጥበብ ጉድለት፣ ወይ ባጉል መራቀቅ ዘፍቆ
ከስህተቱም ከጥራቱም፣ ተቻችሎ አለ ተጣብቆ፡፡
እንግዲህ  ሐምሌት ምናልባት፣ ዛሬ እወድሻለሁ ሲል
በፍቅሩ የልብ ጥራት፣ አይገኝ ይሆናል እክል
ግን የልደቱን ደረጃ፣ ስታስቢው ደሙን ቅጅ
ፍቃዱ የሱ እንዳልሆነ፣ አስተውይ የእናቴ ልጅ፡፡”
ሌላው አስጊና አትጊ ነገር እርስ በርስ መጠራጠር ነው፡፡ መሪዎች ካልተማመኑ ተመሪዎች ተግባብተው መራመድ ይቸግራቸዋል፡፡ ተግባብተው የማይራመዱ ሰዎች ወንዝ ለወንዝ ሲማማሉ ነው የሚኖሩት፡፡
“ዕምነት ሲታመምሺ ወረቀት መፈራረም” ይለዋል ጸጋዬ ገ/መድህን፡፡ ቢሮክራሲያችን፣ ፓርቲዎቻችንም፣
አመራሮቻችንም ከአበሻ የጥርጣሬ ድርና ማግ ነው ተሰሩት፡፡ ዛሬ የተባለው ነገ የሚሻረው ለዚህ ነው፡፡
እኔ ከሁሉ በላይ ነኝ የሚል አስተሳሰብ አጥፊ ነው፡፡ የበላይነትን በተሻለ ሥራ ካላሳየን ከፉከራ አያልፍም፡፡
“የተሻልን ነን እያልን
ያልተሻለ ነገር ከሰራን
መሻላችን ምኑ ላይ ነው፣ ትላንት ላይ ከተጋደምን”እንደሚለው ነው ገጣሚው፡፡
ህዝብ መንግስትን አምኖ በራሱ ተነሳሽነት ካልተንቀሳቀሰ፣ ዲሞክራሲው ጤነኛ ነወይ? ብሎ መጠየቅ ያባት ነው፡፡ የምስራቅ አውሮፓ መንግስታት ብትንትናቸው እስኪወጣ ድረስ 98 በመቶ ምርጫውን አሸንፈናል ይሉ እንደነበር አለመርሳት ብልህነት ነው፡፡ ያልመረጠው ለምን እንዳልተመረጠ ብቻ ሳይሆን የመረጠው ለምን እንደሆነ መጠየቅ ያባት ነው፡፡ ቀስቅሰን፣ አስገድደን ወይ አታለን መመረጥ ጭብጨባን እንጂ ልባዊ ድጋፍን አያስገኝም፡፡ በእርግጥ የፖለቲካ ጸሀፍት፤ “ገባው አልገባው አይደለም የፖለቲካ ሚስጥሩ፡፡ ተቀበለ አልተቀበለ  ነው እንጂ” ይላሉ፡፡ ሆኖም ጊዜያዊ ነው፡፡ እንደሚታወቀው እንኳን ፖለቲካው ታሪክም አሸናፊዎች የሚፅፉት ተረት ነው፤ ይሏል፡፡ ስለዚህም ኢ-ተዓማኒ ሪፖርት በተነገረ ቁጥር፣ ሙገሳና የአፍ ሙካሽን የተንተራሰ ሲሆን “እሰይ እሰይ! እልል በይ ጉሜ!” ማለት ቢያንስ የዋህነት ነው፡፡ በማንኛውም የለውጥ ንፋስ ውስጥ ጊዜን፣ ወዳጅንና ባላንጣን ማሰብ ዓይነተኛ ብልህነት ነው፡፡ ጊዜው እንጂ ሁኔታው አይደለም ጥፋተኛው፡፡ “ሳህን ቢጠፋ አብረን በላን” እንደሚባለው የትግሪኛ ተረት፤ “የሰሜን ብርድ ከማትወድደው ጋር ያስተቃቅፋል” የሚለው ተረት ዋና ጉዳይ ነው!

Read 6539 times