Saturday, 14 February 2015 14:45

‘ጁላይ ፎር’ን በቄጤማና በፈንዲሻ…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(6 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ከወራት በፊት የሆነ ነገር ነው… አንድ ወዳጃችን የሆነ ዘመዱ እንትናዬውን ስለተነጠቀ በሽቆ የሚይዘው የሚጨብጠው አጥቶ ነበር፡፡ (የዘመኑ ልጆች ቢሆኑ… “መነጣጠቅ ብርቅ ሆኖበት ነው እንዴ!” ብለው ‘ሙድ ይይዙበት’ ነበር፡፡)
ለካላችሁ በጣም ያበሸቀው…አለ አይደል…ነጣቂ የተባለው ሰው ‘የማይገፉት ዋርካ’ ቢጤ ኖሯል። ልጄ…የእኔ ቢጤ ቢሆን ኖሮ… “ሁለተኛ አጠገቧ ብትደርስ ሦስት ቀን ክፍቱን ያደረ አብሲት ነው የማደርግህ!” ብሎ ‘ቴረር’ መልቀቅ ይቻላል፡፡
ስሙኝማ…አሁን አሁን እኮ ‘ነጻ ዝውውር’ አይሉት፣ ‘የስውር ድርድር’ አይሉት… የእንትናና የእንትናዬ ቡድን የመለዋወጥ ‘የዝውውር መስኮት’ ዓመቱን ሙሉ ክፍት አይደል እንዴ!  
እኔ የምለው…ዘንድሮ ስንቱ ‘በማይገፉ ዋርካዎች’ እየተነጠቀ… “ለጣይም ፈንጋይ አለ…” እያለ አጨብጭቦ ቀርቶ የለ!
ሀሳብ አለን…የተነጠቃችሁ ሰዎች…ለእንትናዬዎቻችሁ የ‘ቫለንታይን ዴይ’ ጽጌረዳ ላኩላቸው፡፡ አሀ…ልክ ነዋ! ሰሞኑን ሚዲያ ላይ ስንማ እንደከረምነው ከሆነ…ይሄ ቫለንታይን ዴይ የሚባለው ነገር… “የመቃብሬን አፈር እንዳትረግጥ/እንዳትረግጭ…” የተባባሉ ሁሉ መልሰው የሚገናኙበት ይመስላላ!
ይቺን እውነተኛ ታሪክ ስሙኝማ…ልጅዬው አሥራ ዘጠኝ ዓመቱ ነው አሉ፡፡ እናማ… እንትንዬውን ለማስደሰት ከታወቀ የጌጣ ጌጥ መደብር እጅግ ውድ የሆነ የእጅ አምባር ይገዛል፡፡ የመደብሩ ባለቤትም… “የፍቅረኛህ ስም እላዩ ላይ እንዲቀረፅልህ ትፈልጋለህ?” ይለዋል፡፡ እሱዬውም ትንሽ አሰበና… “አልፈልግም…” ይላል፡፡ የመደብሩ ባለቤትም ምክንያቱን ይጠይቀዋል፡፡ ልጁ ምን ቢል ጥሩ ነው…“ድንገት ከእሷ ጋር ከተጣላን ለአዲሷ ገርል ፍሬንዴ እጠቀምበታለሁ…” ብሎ አረፈው፡፡ አሪፍ አይደል…ወጪ ቆጣቢ ነዋ!
በነገራችን ላይ ቀኑን ከብዙ አሥርት ዓመታት በፊት ጀምረው ሲያከብሩ የነበሩት ሰዎች እንኳን በቫለንታይን ዴይ አጀማመር ላይ ገና እየተጨቃጨቁ ነው፡፡ አንዳንዶቹ… የነጋዴዎች ቢዙ ማሟሟቂያ ነው ይላሉ፡፡ እንደውም በድሮ ጊዜ በነበረ የመልካም ምኞት መግለጫ ካርድ አምራች ኩባንያ የተፈጠረ ነው የሚሉት ነገር አለ፡፡ ይቺ እንኳን ትንሽ ታስቸግራለች…
ስሙኝማ…ስለ ‘ቫለንታይን ዴይ’ ሲያወሩ…አለ አይደል…በየአገሩ የሚቃወሙት እንዳሉ መግለጽ አሪፍ ነው፡፡
ይቺን ስሙኝማ…ባል ቁጭ ብሎ መጽሐፉን ያነባል፡፡ ሚስት ቅልጥ ያለ እንቅልፏን እየለጠጠች ነበር፡፡ ለካስ ህልም ስታይ ነበር፡፡ ታዲያላችሁ… ከእንቅልፏ ስትነሳ ለባሏ
“ምን የመሰለ ህልም አየሁ መሰለህ!...” ትለዋለች።
ባልም… “ምን አይነት ህልም አየሽ…” ይላታል፡፡
እሷም ምን ትለዋለች… “በ‘ቫለንታይን ዴይ’ የዕንቁ ሀብል ስትሰጠኝ አየሁ፡፡ ትርጉሙ ምን ይመስልሀል?”
እሱዬውም… “ዛሬ ማታ መልሱን ታውቂዋለሽ…” ይላታል፡፡
እናላችሁ…ባል ሆዬ ማታ ቤቱ ሲመጣ በአሪፍ ወረቀት የተጠቀለለ ስጦታ ይዟል፡፡ “የ‘ቫለንታይን ዴይ’ ስጦታዬ ይኸው…” ብሎ ይሰጣታል፡፡ እሷም ትጠመጠምበታለች፡፡
“እኔ አላምንም! ምንድነው ያመጣህልኝ?”
“ከፍተሽ እዪው…”
እሷዬዋ እንደ ዋንጫ ልቅለቃም፣ እንደ ትከሻ እንቅጥቅጥም እየሞከራት…  የስጦታ ጥቅሉን ትከፍተዋለች፡ እናላችሁ…  ምን ብታገኝ ጥሩ ነው… ‘የህልም ፍቺ’ የሚል መጽሀፍ! ልክ ነዋ… የህልሙን ትርጉም ጠየቀችው እንጂ ሀብል ግዛልኝ አላለችውማ!
እንትናዬዎች… “በህልሜ ቪትዝ መኪና ስነዳ አየሁ፣ ትርጉሙ ምን ይመስልሀል?”   “በህልሜ ሦስት መኝታ ቤት ኮንዶሚነየም ስትከራይልኝ አየሁ፣ (ቂ…ቂ…ቂ…) ምን ማለት ነው?” እያላችሁ ዙሪያ ጥምጥም አትሂዱ፡፡ በቃ ፊት ለፊት… “ቪትዝ የማትገዛልኝ ከሆነ በኋላ ማሪኝ ብዬሻለሁ እሞትብሻለሁ..ምናምን ብትለኝ የሚሰማህ አታገኝም፡፡” “ሦስት መኝታ ቤት ኮንዶሚኒየም ካልተከራየህልኝ ከእንግዲህ ከአንተ ጋር መንደር፣ ለመንደር አልጓተትም፡፡ እንዴ እየጎተትከኝ የምትዞረው የልዋጭ ዕቃ መሰልኩህ!” (ቂ…ቂ…ቂ…) እያላችሁ ዕቅጩን መናገር ነው፡፡
ለነገሩ ዘንድሮ ወንዱ ሁሉ “…ግዛልኝ…” እስኪባል ሳይጠብቅ መኪና እየገዛና ኮንዶሚኒየም እየተከራየ…ድፍኑን ዓመት ‘ቫለንታይን ዴይ’ ነገር አድርጎታል ይባላል፡፡ የምር ግን… የኮንደሚኒየም ኪራይ እኮ ዝም ብሎ እዚያ ላይ አልተሰቀለም!
ስሙኝማ…ይሄ ኮንዶሚኒየም እየተከራዩ…አለ አይደል…‘ማስቀመጥ’ የምር የአእምሮ ንብረት ባለቤትነት ልንጠይቅበት ይገባል፡፡ (“ጎተራ ኮንዶሚኒየም ሰው ልጠይቅ ነው…” “ብርጭቆ ኮንዶሚነየም ድረስ ብዬ መጣሁ…” ምናምን የምትሉ ወዳጆቻችን…በቃ ጠረጠርናችሁ፡፡ (እንትና…ማንም ሰው “ገንዘብ አታስቀምጥና እንትናዬዎች አስቀምጥ!” ብሎህ አያውቅም!)
እኔ የምለው…ምድረ ‘ሌጣ’ ዛሬ ማታ…ጉልበትህን አቅፈህ ተኛ፡፡
እኔ የምለው…እግር መንገዴን…‘ቫለንታይን ዴይ’ እኮ… አለ አይደል… ብዙ አገሮችም ተቃውሞዎች አሉበት፡፡ ለምሳሌ… ያለፈው ዓመት ቀኝ አክራሪ ሂንዱዎች ‘ቫለንታይን ዴይ’ ለማክበር የተሰበሰቡ ጥንዶችን በቲማቲም ወግረዋቸዋል ተብሏል፡፡ በፓኪስታንና በሌሎች አገሮችም… አለ አይደል… “ከባህላችን ውጪ ነው…” “ከእምነታችን ውጪ ነው…” በሚሉና በሌሎች ምክንያቶች ችግሮች ነበሩ።
ይሄን ዘመን ‘ቢዙም’ ተጧጡፏል፡ እኔ የምለው…‘ቫለንታይን ዴይ’ በቃ የቺስታ’ በዓል አይደለም፤ ልጄ…አንዷ ጽጌረዳ የምትገዛበት እኮ የወር የነጭ ሽንኩርት በጀትን ይይዛል፡፡ የይምር…ይቺን ሰሞን የአበባ ነጋዴ መሆን ነበር፡፡ አሀ…የዓመት በጀት ይዘጋላ! ልጄ ኑሮ ራሱ ‘ደም ብዛት’ የሆነበት ዘመን ነው፡፡ ልክ ነዋ…ሁለቱም ራስ ላይ ወጥተው አይደል መከራችንን የሚያሳዩን! ታዲያማ…የአሥራ አምስት ቀን የአበባ ነጋዴ ሆኖ የአሥራ አምስት ወር ፈራንካ ገቢ ማድረግ ነበር! ቢያንስ..ቲማቲም በወጣ ቁጥር ‘ደሙ’ በእኩል ፍጥነት አብሮ አይወጣም ነበር!
ስሙኝማ…እንግዲሀ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...ኮሚኩ ነገር ምን መሰላችሁ… ‘ቫለንታይን ዴይ’ን…  ልክ ከአጼ እከሌ ዘመን ጀምሮ ይዘን የመጣነው በዓል ሊያስመስሉት ሲሞክሩ ትሰማላችሁ፡፡ እንግዲህ ይከበር ከተባለ… በቃ ምን ይደረጋል ይከበር…ግን ከምስረታው ጀምሮ የእኛ ያልነበረ ነገርን… አለ አይደል… በዚህ፣ በዛ ብሎ ‘የታሪካችን አካል’ አይነት ነገር ለማድረግ መሞከሩ አሪፍ ነገር አይደለም፡፡
በውጪም ዓለም ቢሆን…‘ቫለንታይን ዴይ’ በዋነኛነት የቢዙ ቀን ነው፡፡ እንደውም “ዘ ቫለንታይን ዴይ” ኢንደስትሪ የሚሉት አገላላጽ አላቸው፡፡
እናላችሁ…እኛ ዘንድም ቢሆን አሁን “ዘ ቫለንታይን ዴይ ኢንደስትሪ” የሚል እየተፈጠረ ነው። ይህ ሁሉ ‘የሚዲያ ሽፋን’ በዋነኛነት የ‘ቢዙ’ ጉዳይ ነው፡፡ ከሁለት ሳምንታት ቀድሞ ወሬ የሚሞቅለት የትኛው በዓላችን ነው! የእኛ አገር የበዓል ‘ቢዙ’ በጉና ዶሮው ላይ ነዋ!
ስሙኝማ…ይህ ‘ቫለንታይን ዴይ’ የሚባለው ነገር የፍቅረኞች ቀን ነው አይደል የሚባለው! ሀሳብ አለን… እዚህ አገር ‘ፍቅረኞች’ የሚለው ቃል ትርጉም ግራ የሚያጋባበት ዘመን ላይ ስለተደረሰ መጀመሪያ በትርጉሙ እንስማማማ! ልክ ነዋ…ፍቅርና ‘እነሆ በረከት’ እየተምታታ ነዋ!
ደግሞላችሁ…የ‘ቫለንታይን ዴይ’ በዓል ‘ተቋዳሽ’ ለመሆን ፈራንክ ያስፈልጋል፡፣ እውነቱ ይኸው ነው፡፡ እናማ…በቃ፣ “ከሌለህ የለህም…” ነው፡፡ ጥያቄ አለን…በ‘ቫለንታይን ዴይ’ አከባበር እኛም እንድንሳተፍበት ቄጤማ ተጎዝጉዞ የሚከበርበት ዘዴ ይፈጠርልን። ልክ ነዋ…ለስጦታ እንደሁ ለእንትናዬዋ… አለ አይደል… ፈንዲሻ ዘገን አድርጎ… “ለአንቺ ያለኝን ፍቅር በዚህ በእፍኝ ፈንዲሻ ስጦታ ለመግለጽ እወዳለሁ…” ምናምን ብሎ ዲስኩር ቢጤ ማድረግ፡፡
እናላችሁ… ‘ቫለንታይን ዴይ’ን መኮረጃችን ካልቀረ ቄጤማና ፈንዲሻ ታሳቢ ይሁኑልንማ! ተበድረንም ቢሆን አናጣቸውማ!
ታዲያላችሁ…ከዕለታት አንድ ቀን… ‘ጁላይ ፎርን’ ኮርጀን የምናከብር ከሆነ፣ ቄጤማና ፈንዲሻ… ‘የበዓሉ አካላት’ የሚሆኑበት ዘዴ ይፈጠርልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2481 times