Saturday, 14 February 2015 15:22

ጋሽ ስብሃት - የዛሬ 29 ዓመት

Written by 
Rate this item
(52 votes)

ታዬ፡-     አንዳንዶቹ የበዓሉ ግርማ ገጸ ባሕርያት ጋብቻን በሚመለከት … በተለይ በኪነት ዓለም ውስጥ ስሜት ያላቸውና የሚሳተፉቱ … ጋብቻን በጥርጣሬ ዓይን ነው የሚያዩት።  ለምን? ጋብቻን ከኪነት ስራቸው ጋር እንደሚፎካከር፣ እና እንደልቡ ለመሆን እንደማይችል ደራሲው… ለምን? ላገባት ሴት ጊዜውን መስጠት አለበትና ያ ደግሞ የፈጠራ ጊዜውን እንደሚሻማ አድርገው የሚናገሩ፣ የሚሰማቸው ገጸ ባህሪያት አሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት ስሜት አንተ የለህም?
ስብሐት፡- እኔ እንደሱ አይሰማኝም፡፡ ግን ይገባኛል የነሱ ስሜት፤ በደንብ ይገባኛል … ምክንያቱም እውነት ነው፡፡ ሚስት የኪነትን ጊዜ፣ ሀሳብ፣ “ኢነርጂ”፣ ሁሉን ትሻማለች ሳይሆን ትጋራለች ብንል ነው ጥሩ፡፡
ታዬ፡-     ለምን?
ስብሐት፡- ሽምያ መነጣጠቅ ነው፡፡ መጋራት ግን የሷ ተራ ሲሆን ለሷ ጊዜህን ትሰጣለህ፡፡ የኪነት ተራ ሲሆን ለኪነት ጊዜህን ትሰጣለህ፡፡ እሷም ከተዋደድን ይሄ ይገባታል፡፡
ታዬ፡-     ስለዚህ የፈጠራ ስራውን ጋብቻ ሊያስተጓጉልበት አይችልማ?
ስብሐት፡- የፍቅር ጋብቻ ከሆነ አይችልም ነው የምለው፡፡ እንዲያውም ሴትዬዋ ብዙ ልታግዘው ትችላለች፤ ብዙ ልታበረታታው ትችላለች፡፤ ጉልበት ልትሆነው ትችላለች … ድክመት ሳይሆን፡፡
ታዬ፡-     ከበዓሉ ጋር ስለ ሥነ ጽሑፍ በምትወያዩበት ጊዜ ብዙ ልዩነት የታየበት ነጥብ አለ እስካሁን ድረስ? ለምሳሌ በዚህ ነገር ላይ እኔ አልስማማም የተባባላችሁበት አለ… ስለ ሥነ ጽሑፍ ባላችሁ አመላከከት?
ስብሀት፡- አዎ፡፡
ታዬ፡-     ምን ምንን በሚመስል ነገር?
ስብሐት፡- ቅድም ያልኩህ ነው … መነሻው ጥያቄ ሌላ ሆኖ ነው እንጂ፡፡ እሱ መጻፍ ስለምትችል ሳንሱር እንዲያልፍ እያሰብክ መጻፍ አለብህ … እና ማሳተም አለብህ፤ ልትነበብ ካልሆነ ለምን ትለፋለህ ያለኝ፡፡ እኔ ደግሞ ለሳንሱር ብዬ ከጻፍኩማ ምኑን ጻፍኩት? ለራሴ … እና በደንብ የሚሰማኝን ለመጻፍ፣ ለማውጣት ካልሆነ ምኑን ጻፍኩት ነው እንግዲህ ልዩነታችን፡፡
ታዬ፡-     ስለዚህ አንተ በምትደርስበት ጊዜ መጀመሪያ የምታተኩረው አድማጭህ ላይ ሳይሆን ራስህ …?
ስብሐት፡- አድማጩ ላይ ነው! አንባቢዬ ላይ ነው! ግን አንባቢዬ ሳንሱር አይደለም፤ ሰው ነው፡፡ እንጂ እንዲያውም አንባቢዬ ላይ ነው በጣም የማተኩረው፡፡ ተግባባን?
ታዬ፡-     አዎን፤ ገባኝ፡፡ ባንተ አስተያየት ደራሲው በሚጽፍበት ጊዜ ይሄ ሳንሱር ያልፋል፤ ይሄ ሳንሱር አያልፍም የሚለው ነጥብ አጻጻፉን ሊወስነው፣ ወይ ሊለውጠው አይገባም ነው?
ስብሐት፡- ልክ! እኔ ስጽፍ ይሄ ለአንባቢዬ ግልጽ አይሆንም፤ ይሄ ግልጽ ይሆናል … ስለዚህ እንደዚህ እያልኩ ነው፡፡ አንባቢ ነው ሀሳቤ ውስጥ ያለው፤ ሳንሱር የለም፡፡
ታዬ፡-     ስለ አንባቢ ካነሳን አልቀረ ምን ዓይነት አንባቢዎች ናቸው በአእምሮህ ውስጥ የሚጉላሉት… በምትደርስበት ጊዜ አንድን የሆነ ድርሰት፣ ልቦለድ? ለምሳሌ ወይ በመደብ፣ ወይ በትምህርት፣ ወይ በጾታ እንደዚህ ታስባቸዋለህ አድማጮችህን? … በዚህ ዓይነት አታያቸውም?
ስብሐት፡- እኔ የማስበው አንባቢዬ ከኔ እኩል ሊያስብ ይችላል፤ ከኔ እኩል ሊሰማው ይችላል፡፡ ስለዚህ እኔ ቃላቱን፣ አባባሉን አጥቼበት ካልሆነ በስተቀር አንባቢዬ አይስተኝም፡፡ ምክንያቱም እኔ ውስጥ ያለ ሁሉ አንባቢዬ ውስጥም አለ፡፡ ያው የሰው ነገር ስለሆነ የምጽፈው … ስለ ምኞት፣. ስለ ኩም ማለት፣ ስለ መውደድ፣ ስለ መጥላት፣ ስለ ተስፋ፣ እንደዚህ፣ እንደዚህ ስለሆነ ምንም ለአንባቢ የማይገባ ነገር አይኖርም፡፡ በቃ እኩያ ነን እኔና አንባቢዬ ማለት ነው፡፡ ስለዚህም ነው ምናልባት እኔ ላስተምር አይደለም የምጽፈው፤ ተረት ልነግር ነው እንጂ፡፡
ታዬ፡-     በዚህስ ነጥብ ላይ አትለያዩም? ለምሳሌ እሱ የስነ ጽሑፍ ሚና ህብረተሰብን ማስተማር …
ስብሐት፡- ነው ይላል እሱ፡፡
ታዬ፡-     ይላል? በዚህ ነጥብ ላይ ግን አትስማሙም?
ስብሐት፡- አንስማማም፡፡
ታዬ፡-     ለማስታረቅም አልሞከራችሁም? ያው እንደተለያየ ነው ያለው ሀሳባችሁ?
ስብሐት፡ አዎ! እርቅ ምን ያደርጋል? በዚህ በኩል እኮ ሲለያዩ ነው ጥሩ፡፡ እሱም የራሱን መንገድ ይይዛል፤ እኔም የራሴን፡፡ ሁለታችንም በየበኩላችን አስተዋጽዖ እናደርጋለን ማለት ነው፡፡
ታዬ፡- እንደዚያም ሆኖ ግን፣ ይህም የሀሳብ ልዩነት ኖሮ ትግባባላችሁ?
ስብሐት፡- በጣም!
(ከላይ የቀረበው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በትርፍ ጊዜ የሥነፅሁፍ ተባባሪ ፕሮፌሰርና የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር የሥነፅሁፍ መፅሔት “ብሌን” ዋና አዘጋጅ ታዬ አሰፋ፤ የዛሬ 29 ዓመት የለንደን ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳሉ ስለአማርኛ ልቦለዶች የትረካ ስልት ለሚያደርጉት ጥናት ከደራሲ ስብሃት ገ/እግዚአብሔር ጋር ያደረጉት ቃለምልልስ ሲሆን ሰሞኑን ከወጣው “ብሌን” መፅሔት የቀነጨበ ነው።)
ቅጽ 8፣ ቁ.፤  (ታህሣሥ 2007)

Read 10981 times