Saturday, 14 February 2015 15:58

የናይጀሪያው ፕ/ት ምርጫውን ያራዘምኩት እኔ አይደለሁም አሉ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

“ምርጫውን ያራዘሙት ሽንፈት ስላሰጋቸው ነው” ተቃዋሚዎች
*የአሜሪካና እንግሊዝ መንግስታት ምርጫው መራዘሙን ተቃውመዋል


በዛሬው ዕለት ይከናወናል ተብሎ ቀን የተቆረጠለትን የናይጀሪያ ፕሬዚዳንታዊና የፓርላማ ምርጫ ለስድስት ሳምንታት አራዝመዋል በሚል በአለማቀፍ ደረጃ ትችት እየተሰነዘረባቸው ያሉት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን፣ ምርጫውን አላራዘምኩም ሲሉ አስተባበሉ፡፡
ቢቢሲ እንደዘገበው፤ ፕሬዚዳንቱ ምርጫውን ለማራዘም በተላለፈው ውሳኔ ውስጥ እጃቸው እንደሌለበትና ውሳኔውን ያስተላለፉት አካላት በጉዳዩ ዙሪያ እንዳላማከሯቸው አስታውቀዋል፡፡
የአገሪቱ የምርጫ አስፈጻሚ ባለስልጣናት፣ ቦኮ ሃራም የተባለው ጽንፈኛ ቡድን ምርጫውን የሚያስተጓጉል ድርጊት ሊፈጽም ይችላል በሚል ከጸጥታ ሃይሎች የተገለጸላቸውን ስጋት መነሻ በማድረግ ምርጫው ለስድስት ሳምንታት እንዲራዘም መወሰናቸውን ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል።
የናይጀሪያ ምርጫ ኮሚሽን ሃላፊ አታሂሩ ጃጋ፣ ምርጫው ሊራዘም የቻለው መራጮችን ከቦኮ ሃራም ከሚሰነዘሩ የሽብር ጥቃቶ መከላከል የሚችል በቂ የጸጥታ ሃይል ባለመኖሩ ነው ቢሉም፣ በምርጫው ለመወዳደር የተዘጋጁ የአገሪቱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በበኩላቸው፤ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን ምርጫውን ያራዘሙት እንዳይሸነፉና ስልጣናቸውን እንዳይነጠቁ በመስጋት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን እና ፓርቲያቸው ፒዩፕልስ ዲሞክራቲክ ፓርቲ፣ ከቀድሞው የአገሪቱ የጦር መሪ ሙሃማዱ ቡሃሪ እና ኦል ፕሮግሬሲቭስ ኮንግረስ ከተሰኘው ተፎካካሪ ፓርቲ ከፍተኛ ፉክክር ይጠብቃቸዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለጸው ዘገባው፤ቡሃሪ በስልጣን ላይ ያለው የጆናታን መንግስት የቦኮ ሃራምን የጥፋት እንቅስቃሴ ለመግታት አቅምም ሆነ ፈቃደኝነት ይጎድለዋል ሲሉ መተቸታቸውንና እሳቸው ስልጣን ላይ ከወጡ ቦኮ ሃራምን በወራት ጊዜ ውስጥ እንደሚያጠፉ ቃል መግባታቸውን ጠቁሟል፡፡
የናይጀሪያ መንግስት ምርጫው መራዘሙን ማስታወቁን ተከትሎ፣ ውሳኔው በአለማቀፍ ደረጃ እየተተቸ እንደሚገኝ የዘገበው ዘ ኢንዲፔንደንት በበኩሉ፤የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ በአገሪቱ ያሉ የጸጥታ ስጋቶች ምርጫን ለማራዘም በቂ ምክንያት ሊሆኑ አይችሉም ማለታቸውን ጠቁሟል፡፡
የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ጸሃፊ ፊሊፕ ሃሞንድ በበኩላቸው፤ ናይጀሪያ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት የምታደርገውን ጥረት የምንደግፍ ቢሆንም፣ በአገሪቱ ያለው የጸጥታ ችግር ናይጀሪያውያን ዲሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን እንዳይጠቀሙ ለማገድ ምክንያት ሊሆን አይገባም በማለት ምርጫው መራዘሙን ተችተዋል፡፡

Read 1410 times