Saturday, 21 February 2015 12:39

በሽብር ለተከሰሱት የተቃዋሚ ፓርቲ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

አመራሮች አቤቱታ ማረሚያ ቤት ምላሽ ሰጠ

በሽብር የተከሰሱት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና ግለሰቦች በሌሊት ፍተሻ ንብረት ተወስዶብናል ሲሉ ላቀረቡት አቤቱታ ማረሚያ ቤት ባለፈው ረቡዕ በሰጠው ምላሽ፤ ፍተሻው የተደረገው በህጋዊ መንገድ ነው ብሏል፡፡
በተለያዩ የሽብር ተግባራት በመሳተፍ ወንጀል የተከሰሱት የአንድነት፣ የሰማያዊና የአረና ፓርቲ አመራሮች፡- አቶ ሃብታሙ አያሌው፣ ዳንኤል ሺበሺ፣ የሸዋስ አሰፋና አብርሃ ደስታን ጨምሮ ሌሎች ተከሳሾች ባለፈው ህዳር ወር አጋማሽ ላይ በማረሚያ ቤቱ በሌሊት በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ ንብረት እንደተወሰደባቸውና ሰብአዊ መብታቸው እንደተጣሰ በጠበቃቸው በኩል አቤቱታ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡
የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የቀጠሮ ማረፊያ አስተዳደር ዋና ሱፐር ኢንተደንት አምባዬ ክቡር፤ ፍተሻው የተከናወነው በፍ/ቤት ትዕዛዝ ከጠዋቱ 12 ሰዓት እንደነበር አስታውሰው፡፡ በአቤቱታው ላይ እንደቀረበው፤ ፍተሻው የተከናወነው ባልታወቁ ሰዎች ሳይሆን በማረሚያ ቤት ጥበቃዎች እንደሆነም ገልፀዋል፡፡ የፍተሻ አላማውን በተመለከተ ሲያስረዱ፤ የታራሚዎችን ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል የተከለከሉ ነገሮችን በፍተሻ ለማስወገድ መሆኑን ያብራሩት ኃላፊው፤ በፍተሻው ወቅት ሚስማር፣ ስለት ነገሮችና ብጥብጥ የሚቀሰቅሱ ፅሁፎች መገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ ፍ/ቤቱም የተከሳሾችን አቤቱታና የማረሚያ ቤቱን ምላሽ መርምሮ ብይን ለመስጠት  ለየካቲት 25 ቀን 2007 ዓ.ም ቀጥሯል፡፡

Read 2276 times