Saturday, 21 February 2015 12:42

አልጀዚራ ኢትዮጵያውያንን በፕሬስ ነፃነት ላይ አሟገተ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(20 votes)

“መንግስትን ተችቶ መፃፍ በሽብር ያስጠይቃል” - ሶሊያና ሽመልስ
“ሃሳብን የመግለፅና የፕሬስ ነፃነት በህገ መንግስቱ የተረጋገጠ ነው” - አቶ አብይ ብርሃነ

ሰሞኑን በአልጀዚራ ቲቪ በኢትዮጵያ የፕሬስ ነፃነት ዙሪያ በተካሄደ ውይይት ጋዜጠኞች፣ በሃገሪቱ ሃሳብን የመግለፅ መብት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸረ ነው ሲሉ የመንግስት ተወካይ በበኩላቸው፤ መንግስት የሃገሪቱን ደህንነት ከአደጋ የመጠበቅ ሚናውን እየተወጣ ነው ብለዋል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ ምሽት “Ethiopian’s Media War” (የኢትዮጵያ ሚዲያ ጦርነት) በሚል ርዕስ በአልጀዚራ “The Stream” የተሰኘ ፕሮግራም ላይ በተዘጋጀው ውይይት በሽብርተኝነት የተከሰሰችው  የዞን 9 ጦማሪያን መስራችና አባል ሶሊያና ሽመልስ፣ የ“ፎርቹን” ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር ታምራት ገ/ጊዮርጊስ፣ የቀድሞ “አዲስ ነገር” ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ታምራት ነገራና በእንግሊዝ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የፐብሊክ ዲፕሎማሲና ኮሙኒኬሽን አማካሪ አቶ አብይ ብርሃነ ተሳትፈዋል፡፡
የዞን 9 ፀሐፊ ሶሊያና ሽመልስ፤ በኢትዮጵያ በህገመንግስቱ የሰፈረውን ሃሳብን የመግለፅ መብትን ተጠቅሞ መንግስትን መተቸት በቀጥታ በአሸባሪነት እንደሚያስጠይቅ ጠቁማ በአጋሮቿና በእሷ ላይ የተመሰረተው ክስም ለዚህ ማስረጃ እንደሆነ ተናግራለች፡፡ “ህገ መንግስቱ ይከበር ብለን ስለጻፍን ነው አሸባሪዎች ተብለን የተከሰስነው” ብላለች- ለአልጀዚራ፡፡
የቀድሞ “የአዲስ ነገር” ጋዜጣ መስራችና ዋና አዘጋጅ ታምራት ነገራ በበኩሉ፤ እሱና በርካታ  የሙያ አጋሮቹ ለስደት የተዳረጉት መንግስት ሊያሰራቸው ባለመቻሉ መሆኑን ጠቅሶ “አዲስ ነገር” ጋዜጣን አቋርጠው ከሃገር ከወጡ በኋላ በሁለቱ የስራ ባልደረቦቹ ላይ የቀረበው የአሸባሪነት ክስ በሃገሪቱ የፕሬስ ነፃነት መብትን ተጠቅሞ መንግስትን መተቸት ዋጋ እንደሚያስከፍል ያመላክታል ብሏል፡፡
የ“ፎርቹን” ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር ታምራት ገ/ጊዮርጊስ በሰጠው አስተያየት፤ ሃገሪቱ የፕሬስ ነፃነትን ሊያስጠብቁ የሚችሉ የህግ ማዕቀፎች ቢኖራትም ካለፉት 10 እና 15 ዓመታት ወዲህ በፖለቲካ፣ በርዕዮተ ዓለምና በህግ  ረገድ የፕሬስ ነፃነት እየተሸረሸረ መሆኑን ተናግሯል፡፡ ጋዜጠኞች በየጊዜው መታሰራቸው ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትና የፕሬስ ነፃነት ፈተና እንደበዛባቸው ያሳያል ብሏል - ታምራት፡፡
መንግስት የሃገሪቱን ህግ የማስከበር ኃላፊነት እንዳለበት በአፅንኦት የተናገሩት በእንግሊዝ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የፐብሊክ ዲፕሎማሲና ኮሙኒኬሽን አማካሪ አቶ አብይ ብርሃነ በበኩላቸው፤ ሃገሪቱ ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ አንፃር የፕሬስ ነፃነቱ በአግባቡ ጥቅም ላይ ስለመዋሉ መንግስት ማረጋገጥ መቻል አለበት ብለዋል፡፡ የፕሬስ ነፃነትና ሃሳብን የመግለፅ መብት በህገ መንግስቱ የተረጋገጠ መሆኑን በመጥቀስም አቶ አብይ ተከራክረዋል፡፡ “አንዳንድ ሰዎች ይሄን መብት በአግባቡ እየተጠቀሙበት አይደለም” ያሉት አቶ አብይ፤ መንግስት ይሄን ዲሞክራሲያዊ መብት ለማጠናከር ከምንጊዜውም በላይ እየተጋ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
(ተሳታፊዎቹ በአልጀዚራ ያደረጉትን ክርክር አንኳር ሃሳቦች ለጋዜጣ በሚመች መልኩ በገፅ 5 ላይ ተርጉመን አቅርበነዋል፡፡)

Read 7669 times