Saturday, 21 February 2015 12:44

አቶ ኤርሚያስ አመልጋ አዲስ አበባ ገቡ

Written by 
Rate this item
(31 votes)

አክሰስ ሪል እስቴትን ለማስቀጠል ያቀረቡት ጥናት አዋጪ ነው ተብሏል

ከሁለት አመታት በፊት በአክሰስ ሪል እስቴት ውስጥ የተፈጠረውን ቀውስ ተከትሎ አገር ጥለው የተሰደዱት አቶ ኤርሚያስ አመልጋ፤ ከመንግስት አካላት ጋር በተደረገ ድርድር ወደ አገራቸው ገብተው የጀመሯቸውን ስራዎች ለማስቀጠልና ከተለያዩ አካላት ለቀረቡባቸው ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት በመስማማት ከትናንት በስቲያ አዲስ አበባ ገቡ፡፡
አክሰስ ሪል እስቴት አክስዮን ማህበር ክፍያ የተቀበለባቸውን ቤቶች በወቅቱ ሰርቶ ማጠናቀቅና ለቤት ገዢዎች ማስረከብ ባለመቻሉ ከቤት ገዢዎችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ከቀረቡባቸው ክሶች ለመሸሽ አገር ጥለው የወጡት የአክሰስ ሪል እስቴት፣ የአክሰስ ካፒታልና የዘመን ባንክ መስራች አቶ ኤርሚያስ አመልጋ፤ በሺህዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ሲባል መንግስት በሰጣቸው ያለመከሰስ ዋስትና ወደ አገር ቤት መመለሳቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡
የአክሰስ ሪል እስቴት ቤት ገዢዎችና ባለአክስዮኖች በጋራ ባቋቋሙት ኮሚቴ አማካይነት በኩባንያው ውስጥ የተፈጠረውን ቀውስ ለመፍታት ያደረጉት ጥረት ውጤት አልባ መሆኑን ተከትሎ፣ መንግስት በጉዳዩ ጣልቃ እንዲገባ ባመለከቱት መሰረት የሚመለከታቸው የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናትን ያቀፈ ኮሚቴ ተቋቁሞ ጉዳዩን ሲያጣራ ቆይቷል፡፡
የአክሰስ ሪል እስቴትን ችግር ለመፍታት ያስችላል በሚል አቶ ኤርሚያስ አዘጋጅተው የላኩትን የአክሲዮን ማህበሩ ወቅታዊ ሁኔታና የቀጣይ አቅጣጫ አመላካች ሰነድና የማገገሚያ ዕቅድ ማስፈጸሚያ ዝርዝር ሃሳብ ሲመረምር የቆየው ኮሚቴው፤ የግለሰቡን ሃሳብ አዋጭነት በመገንዘብ ያወጡትን ዕቅድ ተግባራዊ ማድረግ የሚችሉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ሲሰራ ቆይቷል፡፡
አቶ ኤርሚያስ ችግሩን መፍታትና ዕቅዱን በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ የሚችሉት፣ ከተመሰረቱባቸውና ሊመሰረቱባቸው ከሚችሉ ክሶች ነጻ ሆነው መንቀሳቀስ ሲችሉ እንደሆነ ያስቀመጡትን ቅድመ ሁኔታ ያጤነው ኮሚቴው፤ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር ባደረገው ውይይት ያለመከሰስ ዋስትና ተሰጥቷቸው ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ መደረጋቸውንም ምንጮቻችን ገልጸዋል፡፡
ኮሚቴው ከወራት በፊት በሰጠው መግለጫ፤ አክሰስ ሪል እስቴት አክሲዮን ማህበር ካሉበት እዳዎች ይልቅ ሃብቱ እንደሚበልጥ ጠቅሶ፤ ተገቢው የተቀናጀ ስራ ከተሰራ ኩባንያው ማገገምና የጀመራቸውን ስራዎች ማጠናቀቅ እንደሚችል መገለፁን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

Read 7801 times