Saturday, 21 February 2015 13:04

‘የቅበላ ሥጋ’ እና ‘የቫለንታይን ሥጋ’…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(11 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እኔ የምለው…ኧረ እኛ ብናስመስል አንድዬ ያያል! የቅበላ ቅዳሜና እሁድ ከተማውን አያችሁልኝ! (የሁለት ዲጂቱ ግሮውዝ ይከለስልን፡ አሀ…ኪሎ ሥጋ መቶ ሰባ ብር ለመግዛት የምንጋፋ ሰዎች በበዛንበት ‘የግሮውዝ ዲጂቷ’ ሦስት ልትሆን ትችላለቻ! ልክ እኮ… አለ አይደል… ‘የሥጋ ስምንተኛው ሺህ’ ምናምን የመጣ ይመስል ነበር፡ አሁንማ… ቅበላውም ወደ ‘ቢዙ’ ተለውጦ አንዳንድ ምግብ ቤቶች ድንኳን ሁሉ ጥለው ነበር! (‘ጉድ’ የምንለው ነገር አንጣ!)
እናላችሁ…በተለይ ቅዳሜ የሥጋ ቀንና፣ የሥጋ ምሽት ሆኖላችሁ ነበር፡፡ ልክ ነዋ…ቀን ‘የቅበላ ሥጋ፣’ ማታ ደግሞ ‘የቫለንታይን ሥጋ’! ቂ…ቂ…ቂ…
ይቺን ስሙኝማ…ሴትዮዋ በሰፈሯ ሉካንዳ ቤቱ አጠገብ ስታልፍ ባለ ሉካንዳው ይጠራታል፡፡ ገበያ ቀዝቀዝ ብሎበት ነበር፡፡ እናማ…ሥጋ እንድትገዛ ሲጠይቃት ገንዝብ እንደሌላት ትነግረዋለች፡፡ እሱም… “ግዴለም ቀስ ብለሽ ትከፍይኛለሽ፣ እንዴት እንደሚጣፍጥ እስቲ ይቺን ቅመሽ…” ይላታል፡፡ እሷም…
“አልቀምስም፣ ጾም ላይ ነኝ…” ትላለች፡፡
እሱም… “ከተፈሰከ ስድስት ወር ሆኖ የለም እንዴ!” ይላታል፡፡ እሷም
“አይ፣ የጾሙ ጊዜ አንዲት ቀን ተሳስቼ ስለበላሁ እሷን ለማጣጣት ዛሬን እጾማለሁ፡፡ ግን ሥጋውን ስጠኝና ለነገ ይሆነኛል፣” ትለዋለች፡፡ ባለ ሉካንዳው ምን ቢላት ጥሩ ነው…
“እርሺው፣ የፈጣሪን ዕዳ በስድስት ወር የከፈልሽ የእኔን በስንት ዓመት ልትከፍይ ነው!”
እናማ…ይሄኔ ለአንድ የቅበላ ቀን ስንት ዕዳ የገባን አለን! ኮሚክ ዘመን እኮ ነው… በብድር ቢራ የሚጠጣበትና ቁርጥ የሚቆረጥበት ዘመን!
እኔ የምለው… እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የምትቀጥለዋ ነገር ‘ህዝብ ሳይጠይቅ’ የተደገመች ነች፡፡ ለጾም ሰሞን ትሆናለች ብዬ ነው፡፡ (‘ነገርዬው’ አሁን እንደ ‘ሆቢ’ ነገር እየሆነ ነው ይላሉ..ቂ…ቂ..ቂ…) እናላችሁ…እንግዲህ የጾም ወቅትም አይደል… እሷዬዋ ‘ውል’ ብሎባት ነው መሰለኝ…እሱዬውን “ዛሬ እነሆ በረከት እንበባል። አይነት ነገር ትለዋለች፡፡ (‘ደግ’ ዘመን!) እሱዬው ደግሞ ‘ነፍሱንም አልረሳ’ ኖሮ…“አይ ዛሬ ጾም ነው፣ አይሆንም፣” ይላታል፡፡ እሷዬዋም ቁርጧን አውቃ እየከፋት ወደ ቤቷ ትሄዳለች፡፡
ታዲያላችሁ… በሆነ ምክንያት ያንኑ ዕለት እሱዬው ቤት ተመልሳ ትመጣለች፡፡ አጅሬው ሆዬ ከአንዷ ጋር ‘እነሆ በረከት’ ሲባባል እጅ ከፍንጅ ትይዘዋለች! ይሄኔ ምን ብትል ጥሩ ነው…
“ለእኔ ጾም ነው ያልከኝ እሷ ከሰላጣ ነው የተሠራችው!”
አሪፍ አይደል!
‘ከሰላጣ የተሠራችሁ’… ‘እንዳንሳሳት’ የሆነ ምልክት ወይ ደረታችሁ ወይ ክንዳችሁ ላይ አድርጉልንማ!
እንግዲህ ያው ‘ጾም’ ገብቷል አይደል… ምን ይመሰለኛል መሰላችሁ…በቃ፣ የጾም ሰሞን ማለት ብዙዎቻችን ራሳችንን የምናታልልበት ሰሞን ነው፡፡ በቀን የዘጠኝ ሰው ቤትን የሚበጠብጠው ሰውዬ… “እስከ ዘጠኝ ነው የምጾመው…” ይላል፡፡ የሰፈር ሰው … “ግዴለም ቲማቲሙም ይወደድ፣ ውሀም በአሥር ቀን አንዴ ጠብ ትበል፣ ‘የአንዳንድ የአዲስ አባባ ነዋሪዎች’ ነገርም ግራ ይግባን… “እንደው ይቺን ሴትዮ ከዚህ ሰፈር አልነቅላላችሁ አልከን!” እያለ ለሰማይ ቤት በጋራ አቤቱታ የሚያቀርብባት ሴትዮ ነጠላዋን ተከናንባ… “ላስቀድስ መሄዴ ነው ትላለች፡፡”እዚያው ጸሎት ስፍራው በር ላይ ሆና ምን ትላለች መሰላችሁ…
“የእከሌን እግር ቄጤማ፣ የእከሊትን ዓይን ጨለማ አላደርግልሽ አልከኝ!”
የሚገርም ነገር እኮ ነው ስንት የሚጠየቅ ነገር እያለን!…
ይቺን ስሙኝማ…ሰባኪው የሆነ ውቅያኖስ ውስጥ ይወድቃል፡፡ ክፋቱ ደግሞ መዋኘት አይችልም፡፡ ወዲያው አንድ ጀልባ መጣች፡፡ የጀልባዋ አዛዥም…
“አባት፣ እርዳታ ይፈልጋሉ?...” ሲል ይጠይቀዋል። ሰባኪውም…
“አልፈልግም፣ እግዚአብሔር ያድነኛል…” ይላል። ትንሽ ቆይቶ ሌላ ጀልባ ይመጣል፡፡ አዛዡም…
“አባት እርዳታ ይፈልጋሉ?...” ይለዋል፡፡ ሰባኪውም…
“አልፈልግም፣ እግዚአብሔር ይረዳኛል…” ይላል፡፡ ከዚያ ሰባኪውም ይሰምጥና ህይወቱ ያልፋል፣ መንግሥተ ሰማያትም ይገባል፡፡ ሰባኪውም እግዚአብሔርን…
“ውሀ ውስጥ ወድቄ ግቢ ነፍስ፣ ውጪ ነፍስ ስሆን ለምን አላዳንከኝም?” ይለዋል፡፡ እግዚአብሔርም ምን ቢለው ጥሩ ነው…
“አንተ ደደብ፣ ሁለት ጀልባዎች ልኬልህ እርዳታ ትፈልጋለህ ወይ ስትባል አልፈልግም አላልክም!” አለው ይባላል፡
ጀልባ ሲላክልን ማወቁ ብልህነት ነው፡፡
እናላችሁ…ራሱን በራሱ ‘መሸወድ’ የሚችል እንደ እኛ አይነት ህዝብ አለ! የምር እኮ ኮሚክ ነገር ነው! ከዓመቱ ውስጥ ‘ባላንስድ ዳየት’ የሚሉትን ነገር የምናገኘው በዚህ የጾም ወቅት ነዋ! ልክ ነዋ…አንድ ሳህን ጥብስ ጾመን…አሥራ ሦስት አይነት ‘የጾም ምግብ’ ሆዳችን የእንትን ከበሮ እስኪያክል የምንበላው እኮ በዚሀ ሰሞን ነው!
ራሳችንን ‘መሸወድ’ የምናቆምበትንና… አለ አይደል…ከነገርና ከክፋት የምንጾምበትን ዘመን ያቅርብልንማ!
ይቺን ስሙኝማ…ሰውዬው እግዚአብሔርን…
“እግዚአብሔር አንድ ሚሊዮን ዓመት ምን ያህል ይረዝማል?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ እግዚአብሔርም “አንድ ሚሊዮን ዓመት ለእኔ አንድ ደቂቃ ነች…” ይለዋል፡፡
ቀጥሎም ሰውየው… “አንድ ሚሊዮን ብር ምን ያህል ነው?” ይለዋል፡፡ እግዚአብሔርም ሲመልስለት…
“አንድ ሚሊዮን ብር ማለት ለእኔ አንድ ሳንቲም ማለት ነው…” ይለዋል፡፡ አጅሬው እንደገና ምን ይላል “እግዚአብሔርዬ፣ እስቲ አንድ ሳንቲም ስጠኝ…” ሲል ይጠይቀዋል፡፡
እግዚአብሔር ምን ብሎ ቢመለስለት ጥሩ ነው…
“አንድ  ደቂቃ ጠብቀኝና እሰጥሀለሁ፡፡”
እናማ…በጾም ወቅት እንኳን ከክፉ ነገር እንድንርቅ ያድርገንማ! የምር እኮ ዘንድሮማ…እኛን መስበክ ሥራቸው የሆኑ አንዳንዶቹ አብረውን በአደባባይ ‘ሲፕ’ እያደረጉ ነው እኮ!
ኒው ዮርክ ውስጥ ነው አሉ፡፡ ሰባኪው መጠጥ ተጎንጭተው መኪና እያሽከረከሩ ነበር፡፡ ታዲያ ከፍጥነት በላይ ሲነዱ ፖሊስ ያስቆማቸዋል፡፡ ፖሊሱም ጠጋ ሲል ሰባኪው ትንፋሽ ላይ የአልኮል ጠረን ይሽተዋል፡፡
“ጌታዬ መጠጥ ጠጥተዋል እንዴ?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ሰባኪውም…
“ኧረ ውሀ ብቻ ነው የጠጣሁት!” ይላል፡፡ ፖሊሱም…
“ታዲያ ለምንድነው ትንፋሽዎ አልኮል፣ አልኮል የሚሸተኝ?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ሰባኪው ምን ቢል ጥሩ…
“ወይ የፈጣሪ ሥራ! በዚች ቅጽበት ውሀውን ወይን አድርጎት አረፈው!” ብሎ ቁጭ!
እንትና …እኛ ጠላ የሚወዱት እንኳን…(በፈረንጅ አፍ…) ‘ሶል ፋዘር’ህ ናቸው የሚባለው አሉባልታ ነው እንዴ! ቂ…ቂ…ቂ…
እኔ የምለው…ጥያቄ አለን፡፡ ‘ኪሶሎጂ’ ለምንድነው ጾም የማይሆነው! አሀ…ያው እሱም ሥጋ አይደል እንዴ! ቂ…ቂ…ቂ…
እናላችሁ…የበቀደሟ ቅዳሜ… ቀን ‘የቅበላ ሥጋ’… ማታ ‘የቫለንታይን ሥጋ’… ‘ፌሽታ’ ሆና አለፈችላችሁ!
ጾሙን የእውነት ጾም የምናደርገበት ልቦናውን ይስጠንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2945 times