Saturday, 21 February 2015 14:08

ኦባማ፤ አይሲስንና ሌሎች ጽንፈኛ ቡድኖችን አለም በጋራ እንዲዋጋ ጠየቁ

Written by 
Rate this item
(9 votes)

“ ሲአይኤና ሞሳድ አይሲስ እና ቦኮ ሃራምን ይደግፋሉ” አልበሽር
“ አይሲስን ለመዋጋት የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ይነሳልኝ” ሊቢያ

ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፤ አይሲስ የተባለውን እስላማዊ ቡድን ጨምሮ ሌሎች ጽንፈኛ ቡድኖች በተለያዩ አገራት የሚፈጽሙትን የሽብር ተግባር ለመግታት የአለም አገራት ተባብረው እንዲሰሩ ጥሪ አቀረቡ፡፡
ኒውዮርክ ታይምስ እንደዘገበው፤ የ60 አገራት ተወካዮች በተገኙበትና በዋሽንግተን በተካሄደው በጽንፈኝነት ላይ ያተኮረ ስብሰባ ላይ ባለፈው ረቡዕ ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፣ የአለም አገራት መንግስታት የእስላማዊ መንግስት መርህን አንግበው የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ ቡድኖችን በተባበረ ክንድ መመከት ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
የሱኒ ታጣቂ ቡድኖችን አስተሳሰብ ማዳከምና እንቅስቃሴያቸውን መግታት የትውልድ ፈተና ሆኖ ቆይቷል ያሉት ኦባማ፤ ቡድኖቹን በስኬታማ መንገድ ከእንቅስቃሴያቸው መግታት የሚቻለው በእስልምና እምነት ተከታዮች፣ በመንግስታት፣ በሃይማኖት መሪዎች፣ በማህበረሰቦችና በመሳሰሉት የተቀናጀ ርብርብ ብቻ ነው ብለዋል፡፡
ኦባማ አሜሪካ ጦርነት ውስጥ የገባችው ከእስልምና ጋር ሳይሆን የእስልምናን አስተምህሮት ከሚያዛቡ የጥፋት ሃይሎች ጋር ነው ማለታቸውን የዘገበው ሮይተርስ፤ እስላማዊ ታጣቂ ቡድኖች ምዕራባውያን በእስልምና ላይ ጦርነት አውጀዋል በማለት የሚያቀርቡትን ውንጀላ መሰረተ ቢስ ነው ሲሉ ማጣጣላቸውን ጠቁሟል፡፡ አሜሪካም እና ሌሎች ምዕራባውያን አገራት እስልምናን ለመጨቆንና በእምነቱ ላይ ጥላቻ እንዲስፋፋ ለማድረግ ይሰራሉ በሚል ከአንዳንድ አክራሪ ቡድኖች የሚሰነዘረውን ውንጀላ መሰረተ ቢስነት ለማረጋገጥ የእስልምና መሪዎች ጠንክረው መስራት ይገባቸዋል ብለዋል ኦባማ፡፡
አለማችን ከእስልምና አስተምህሮት ጋር ጸብ የላትም፣ አይሲስ እና አልቃይዳን የመሳሰሉ ቡድኖች ግን የሃይማኖት መሪዎች ሳይሆኑ በሃይማኖት ሽፋን ጥፋት የሚፈጽሙ  ሽብርተኞች ስለሆኑ እንታገላቸዋለን ማለታቸውንም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በጠራው አስቸኳይ ስብሰባ ላይ የተሳተፈችው ሊቢያ በበኩሏ፤ አይሲስን እና ሌሎች ጽንፈኛ ታጣቂ ቡድኖችን በአግባቡ ለመመከት እንድትችል፣ የተመድ የጸጥታ ምክር ቤት የጣለባትን የጦር መሳሪያ ግዢ ማዕቀብ እንዲያነሳላት ጠይቃለች፡፡ ማዕቀቡ ከአራት አመታት በፊት እንደተጣለባት ያስታወሱት የሊቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሞሃመድ አል ዳሪ፤ በአገሪቱ ያለው የጸጥታ ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ጠቅሰው  የአገሪቱ ታጣቂ ቡድኖች ከአይሲስ ጋር ተባብረው የባሰ ጥፋት ሊፈጽሙ እንደሚችሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ ለዚህም በቂ የጦር መሳሪያ መያዟ ወሳኝ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
በቅርቡ  21 ዜጎቿ በአይሲስ ታጣቂዎች ተቀልተው የተገደሉባትና በቡድኑ ላይ የአየር  ላይ የአጸፋ ምላሽ የሰነዘረችው ግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሽኩርም፣ በሊቢያ ያለው የጽንፈኛ ቡድኖች እንቅስቃሴ ከፍተኛ ችግር የሚፈጥር በመሆኑ፣ በአገሪቱ ላይ የተጣለው የጦር መሳሪያ ግዢ ማዕቀብ መነሳቱ ጠቃሚ እንደሆነ ጠቁመው  ሃሳቡን እንደሚደግፉት ገልጸዋል፡፡
የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር ሃሰን አልበሽር በበኩላቸው፤ የአሜሪካና የእስራኤል የስለላ ተቋማት ሲአይኤና ሞሳድ ለአሸባሪዎቹ እስላማዊ ቡድኖች አይሲስ እና ቦኮ ሃራም በስውር ድጋፍ ይሰጣሉ ሲሉ መወንጀላቸውን  ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
አይሲስ ከቀናት በፊት በሊቢያ የኮፕቲክ ክርስቲያን አማኝ የሆኑ 21 ግብጻያውንን በመቅላት መግደሉን ተከትሎ ፕሬዚዳንቱ ከዩሮኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለመጠይቅ እንዳሉት፣ ይህን መሰሉን የጭካኔ ተግባር የሚፈጽም የእስልምና እምነት ተከታይ የለም፣ ይልቁንም ለዚህ ቡድን የጭካኔ ተግባር ድጋፍ የሚያደርጉት  ሁለቱ የስለላ ተቋማት ናቸው ብለዋል፡፡
መሰል የአሸባሪ ቡድኖችን ለመደምሰስ ሲባል የሚፈጸም ሃይል የተሞላበት እርምጃም ቡድኖቹ የከፋ የአጸፋ ምላሽ እንዲሰጡ የሚገፋፋ ሊሆን ይችላል ሲሉም አልበሽር አስጠንቅቀዋል፡፡ የሊባኖሱ ሂዝቦላህ መሪም ሲአይኤ እና ሞሳድ ከጽንፈኞቹ ቡድኖች በስተጀርባ ድጋፍ ያደርጋሉ ሲሉ መወንጀላቸውን አሶሼትድ ፕሬስ መዘገቡ ተጠቁሟል፡፡
የቱርኳ አንካራ ከተማ ከንቲባ ሜሊህ ጎኬክ በበኩላቸው፤ ሞሳድ በፓሪሱ የቻርሌ ሄቢዶ ጥቃት ውስጥ ተሳትፎ ነበረው ሲሉ መናገራቸውን ባለፈው ጥር ወር ለንባብ የበቃው ፋይናንሽያል ታይምስ ማስነበቡንም ዘገባው አስታውሷል፡፡ ከንቲባው በወቅቱ እንዳሉት፤ እስራኤል በእስልምና ሃይማኖት ላይ ጥላቻ እንዲነግስ በማሰብ ጥቃቱን በማቀነባበር ተሳትፎ አድርጋለች፡፡ በተደጋጋሚ አሰቃቂ ግድያዎችን መፈጸሙን አጠናክሮ የቀጠለው አይሲስ በያዝነው ሳምንትም፣ በ21 ግብጻውያን ላይ ከፈጸመው አንገት የመቅላት ግድያ በተጨማሪ በኢራቋ ከተማ አል ባግዳዲ 45 ሰዎችን በእሳት አቃጥሎ መግደሉ ተዘግቧል፡፡


Read 5636 times