Monday, 02 March 2015 09:28

የዶ/ር ተክለፅዮን ወ/ማርያም ፋውንዴሽን ተቋቋመ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(6 votes)

“ዶ/ር ተክለፅዮን ጠንካራ መሪ ባይሆኑ ኖሮ ምናልባትም ዛሬ ጅማ ዩኒቨርሲቲ የሚታወቅበትና የሚኮራበት የጤና ሳይንስ ላይኖር ይችል ነበር” - ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ - የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት


   ዶ/ር ተክለፅዮን ወ/ማርያም በሙያቸው ለግማሽ ምዕት ዓመት አገልግለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት መኖሪያቸውን በሰሜን አሜሪካ ያደረጉት የቀድሞ ተማሪዎቻቸው ዶ/ር ተክለፅዮን፣ የህክምና መምህር፣ መጽሐፍት፣ ቤተ መጻሕፍት፣ ላቦራቶሪ፣ … ምንም በሌለበት አስተምረውና እውቀት አስጨብጠው ለዛሬው ማንነታቸው እንዴት እንዳበቋቸው ምንጊዜም አይዘነጉትም፡፡
ከሦስት ዓመት በፊት እነዚያ ዶክተሮች የሚወዷቸውንና የሚያከብሯቸውን የቀለም አባታቸውን ወደ አሜሪካ ጠርተው ማመስገን ፈለጉ፡፡ በዚህ መሰረት ለክብራቸው በዋሽንግተን ዲሲ እራት አዘጋጅተው ጋበዟቸው፡፡ በሥነ-ስርዓቱ ላይ በተማሪነት ዘመናቸው ያጎናፀፏቸውን እውቀት መክፈል እንደማይችሉት ቢያውቁም ጥቂት ነገር በማድረግ ሊያመሰግናቸው እንደሚፈልጉ ገለጹላቸው፡፡
ዶ/ር ተክለፅዮን ግን የምታደርጉልኝን ነገር ሁሉ ከጅማ ጤና ሳይንስ ጋር የተያያዘ ይሁን አሉ፡፡ “ሐሳባችንን ወደ አዲስ አቅጣጫ አዞሩት” ይላል የሀሳቡ ጠንሳሽና የቀድሞ ተማሪያቸው ዶ/ር ዳውድ ሲራጅ፡፡ ምን እንደሚያደርጉላቸው ሲወያዩ “ለምን በጅማ ዩኒቨርሲቲ በስማቸው ፋውንዴሽን አናቋቁምላቸውም?” የሚል ሐሳብ ቀረበና ሁሉም በአንድ ድምፅ ተስማሙ፡፡ “በዚያን ምሽት በተደረገው ውይይት ከ80 ሺህ ዶላር በላይ ቃል ተገባ፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ እኔ በበጎ  ፈቃደኝነት በብዙ ድርጅት እሳተፋለሁ፡፡ ብዙ ጊዜ ቃል ከተገባው ውስጥ ግማሽ ያህሉ እንኳ አይሰበሰብም፡፡ ነገር ግን ለመጀመሪያ ጊዜ በተደረገው በዚያን ዕለት ስብሰባ ቃል ከተገባው ውስጥ 100 ፐርሰንት ተሰበሰበ፡፡ በ2ኛው የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ከ60 በመቶ በላይ ገንዘብ ተገኘ፡፡ ዋና መስራቾች ተሰብሰብን በፋውንዴሽኑ ዘላቂነትና ቀጣይነት ላይ ተወያይተን ነበር፡፡ በቀጣይነቱ ላይ ሁላችንም በአንድ ቃል ተስማማን” ብሏል ዶ/ር ዳውድ፡፡
የፋውንዴሽኑ ምስረታ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የተከናወነው ባለፈው ታህሳስ ወር ቢሆንም በህመም ምክንያት ዶ/ር ተክለፅዮን በሥነ ስርዓቱ ላይ አልገተኙም ነበር፡፡ ስለዚህ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች ዶክተሩ አሁን ወደሚኖሩበት አዳማ ሄደው ደስታቸውን አብረው ለማክበር በወሰኑት መሰረት የዛሬ ሳምንት የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ፣ የዩኒቨርሲቲው የቢዝነስና ልማት ም/ፕሬዚዳንት አቶ ኮራ ቱሹንና ሌሎችም የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች በአዳማ ከተማ ተገኝተው ዶ/ር ተክለፅዮንን “እንኳን ደስ አለዎት” በማለት አክብሮትና ደስታቸውን ገልጸውላቸዋል፡፡
የሐሳቡ ጠንሳሽ እኔ ብሆንም ስራው ከባድ ስለነበር ሌሎችም ረድተውኛል ያለው ዶ/ር ዳውድ፤ አትላንታ ኗሪ የሆነው ዶ/ር መስፍን ፍራንሷ፣ ከኒውዮርክ ዶ/ር ፋሲል ደስታ፣ ከኖርዝ ዳካታ ዶ/ር ኦልማ ቡሸን፣ ከኒውዮርክ ዶ/ር መስከረም አስረሳኸኝ፣ በኢትዮጵያ ተወካይ እንዲኖረን ዕቅድ ስለነበረን ዶ/ር ማርቆስ ፈለቀና ዶ/ር ሚካኤል ደጀኔ እዚህ ሆነው ከፍተኛ ድጋፍ ስላደረጉልኝ አመስግኛቸዋለሁ፣ ዕቅዳችን እንዲሳካ ስላደረጉ እናንተም አመስግኑልኝ ብሏል፡፡
ዶ/ር ተክለፅዮን፣ ዕድገት ማለት የህብረተሰቡን ችግር መፍታትና ኑሮውን መቀየር ነው የሚል እምነት ስላላቸው፣ ከ1ኛ ዓመት ጀምሮ ወደ ገጠር እየወሰዱን የአርሶ አደሩን ጓዳና የተጫነውን የድህነት መጠን እንድናይ ስላደረጉን የአርሶ አደሩ ኑሮና ህይወት በውስጣችን ተቀርፆ እንዲቀር አድርገዋል ያለው ዶ/ር ዳውድ፤ ከእሳቸው በኋላ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንትና አመራር የነበሩት እንዲሁም አሁን ዩኒቨርሲቲውን በመምራት ላይ ያላችሁት ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ፣ አቶ ኮራ ቱሹንና ሌሎችም የዶ/ር ተክለፅዮንን ሐሳብ ደግፋችሁ ዩኒቨርሲቲው በማህበረሰብ ጤና ትምህርት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቀዳሚ፣ ከአፍሪካ ተመራጭና በዓለም ታዋቂ እንዲሆን እየሰራችሁ ስለሆነ በጣም አመሰግናችኋለሁ፡፡ ዶ/ር ተክለፅዮን፣ ዩኒቨርሲቲውን ለማጠናከር እናንተ በውጭ አገር ያላችሁት ልጆቼ እየመጣችሁ ከዩኒቨርሲቲው ጋር ግንኙነት ፍጠሩ ስላሉን በዚህ ጉዳይ ላይ እየተነጋገርን ሲሆን በቅርቡ የመጀመሪያውን ፍሬአችንን ለማሳየት ኢንተርቬንሽናል ካርዲዎሎጂ ትምህርት ለማስጀመር መሰረት እየተጣለ ነው በማለት ዩኒቨርሲቲውን ለመደገፍ እያደረጉ ያለውን እንቅስቃሴ አስረድቷል፡፡
በውጭ የሚኖሩት የቀድሞ ተማሪዎች፣ የዶ/ር ተክለፅዮን ፋውንዴሽንን ለመመስረት ያቀረቡት ፕሮፖዛል ይህን ይመስላል፡፡ 1ኛ፣ ዓመታዊ የዶ/ር ተክለፅዮን ሌክቸር፡- በአገር አቀፍ ደረጃ በተለይ ለጅማ አካባቢ ማህበረሰብ ጠቃሚና ችግር ፈቺ በሆኑ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ የሚያቀርቡ ታዋቂ ተመራማሪዎችን ስፖንሰር ያደርጋል፡፡ 2ኛ- የዶ/ር ተክለፅዮን ሽልማት፡- ለጅማ ዩኒቨርሲቲ ዕድገትና ተልዕኮ መሳካት በጥናት፣ በማስተማር ወይም በማኅበረሰብ ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገ ግለሰብ ይሸልማል፡፡
3ኛ - የዶ/ር ተክለፅዮን ነፃ የትምህርት ዕድልና ሜንቶርሺፖ፡- በዚህ ፕሮግራም ከፍተኛ ውጤት (ወደፊት ይገለጻል) እያላቸው በገንዘብ ችግር ትምህርታቸውን መከታተል ያልቻሉ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ይደገፋሉ፡፡
በጅማ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የዶ/ር ተክለፅዮንን ሌጋሲ ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ የሚችል ህንፃ በስማቸው እንዲሰየም አመራሩን እንጠይቃለን የሚል መልዕክት የያዙ ሦስት ፕሮፖዛሎች ለጅማ ዩኒቨርሲቲ ላኩ፡፡ ዩኒቨርሲቲውም መልዕክቱን የተቀበለው በደስታ ሲሆን የማያቋርጥ ድጋፍም እንደሚያደርግላቸው ገልጾ “የዶ/ር ተክለፅዮን ወ/ማርያም ፋውንዴሽን” ተቋቋመ፡፡
በአዳማው ሥነ - ሥርዓት ላይ ፋውንዴሽን ማቋቋም ቀላል ነገር አይደለም ያሉት የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ፣ ለዶ/ር ተክለፅዮን ፋውንዴሽን እንዲቋቋም ሲጠየቅ፣ ለራሳቸው ሳይሆን የሕዝብና የአገርን ጥቅም ለሚያስቀድሙ ሰው የዩኒቨርሲቲው ሴኔት የተስማማው በሙሉ ድምፅ ነው ብለዋል፡፡
ጅማ ጤና ሳይንስ ኢንስቲትዩትና ጅማ አግሪካልቸራል ኮሌጅን አንድ ላይ አድርጐ ጅማ ዩኒቨርሲቲ የተመሰረተው በ1991 ዓ.ም እንደነበር ዶ/ር ፍቅሬ ጠቅሰው፣ የግብርናውን ባለሙያ ክህሎት ለማጠናከር በኢትዮጵያና በአሜሪካ መንግሥት በ1944 የተመሠረተውን ኮሌጅ ለሦስት ጊዜ በዳይሬክተርነት የመሩት አሜሪካኖች እንደነበሩና በ1975 ዓ.ም የተመሠረተውን ጅማ ጤና ኢንስቲትዩት ግን በዳይሬክተርነት የመሩት ዶ/ር ተክለፅዮን ወ/ማርያም መሆናቸውን በኩራት ገልፀዋል፡፡
ምንም የተሟላ ነገር (መምህራን፣ መጻሕፍት፣ ቁሳቁስ…) በሌለበት በቆራጥነት አገሪቷን ለማሳደግ የድርሻዬን መወጣት አለብኝ ብሎ ጥቂት ሰዎችን ይዞ የሳይንስ ባለሙያዎችን ለማፍራት መነሳት ከችግርም በላይ ፈታኝ እንደሆነ መገመት አያቅትም ያሉት ዶ/ር ፍቅሬ፣ ዶ/ር ተክለፅዮን ጠንካራ መሪ ባይሆኑ ኖሮ ምናልባትም የጅማ ዩኒቨርሲቲ፣ ዛሬ ጅማ ጤና ሳይንስ የምንለው ክፍል ላይኖረው ወይም በዚያው ሊቀር ይችል ነበር፡፡ እሳቸው ግን እንደመምህር አስተማሪ፣ እንደመሪ ተቋም መርተው፣ በሙያቸው አክመው ዛሬ ዩኒቨርሲቲው ለሚመካበትና ለሚኮራበት የማኅበረሰብ አጋር ለሆነው የጤና ሳይንስ ኢንስቲትዩት መሠረት ናቸው፡፡ ዶ/ር ተክለፅዮን ለጅማ ዩኒቨርሲቲ ምሰሶ ስለሆኑ ትልቅ ቦታ አላቸው፡፡ ዩኒቨርሲቲው ታሪካቸውን ምንጊዜም በአድናቆት ያስታውሳል፡፡ ለዚህም ነው ፋውንዴሽኑ እንዲቋቋም የፈቀደው በማለት አስረድተዋል፡፡
ዶ/ር ተክለፅዮን አለቃዬ ነበሩ ያሉት የዩኒቨርሲቲው የቢዝነስና ልማት ም/ፕሬዚዳንት አቶ ኮራ፣ ከእሳቸው ከተማሯቸው ነገሮች ዋነኞቹ ትዕግሥትና ቅንነት መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በ1983 መንግሥት ሲለወጥ ጅማ ከተማ በዘራፊዎች ተውጣ ድርጅቶች፣ መ/ቤቶች ሲዘረፉ የከተማዋ ነዋሪ እየሸሸ ሲሄድ ዶ/ር ተክለፅዮን ግን ከአዲስ አበባ ወደ ጅማ መጥተው ለጤና ሳይንሱ ኢንስቲትዩት የጥበቃ ሰራተኞች ከኪሳቸው ደሞዝ እየከፈሉ ያበረታቷቸው ነበር ብለዋል፡፡
ዶ/ር ተክለፅዮን 31 ዓመት ወዳገለገሉበት ጅማ ጤና ሳይንስ ኢንስቲትዩት የሄዱት በ1975 ዓ.ም ነበር፡፡ ሲሠሩበት ከነበረው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ለቅቀው ኮሙኒቲ ቤዝድ ኤጁኬሽን በተባለ አዲስ ፍልስፍና የጤና ባለሙያ እንዲያፈሩ ወደ ጅማ የተላኩት በወቅቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር በነበሩት ብርጋዲየር ጄኔራል ግዛው ፀሐይ ፊርማ ነበር፡፡  

Read 2935 times