Monday, 02 March 2015 09:38

አስተናጋጁ ባለ 5 ኮከብ ሆቴል ባለቤት “ሰው’ኮ የተፈጠረው ለመስራት ነው”

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(9 votes)

ዕድሜያቸውን ሙሉ ከሆቴል ቤት አስተናጋጅነት ሥራ ተለይተው አያውቁም፡፡ የዛሬው የ72 ዓመት ሸንቃጣ አዛውንት በጥቁር ሱፋቸው ላይ ቀይ ክራቫት አስረው፤ ሳህን፣ ሹካ፣ ማንኪያ፣ ብርጭቆ፣ ጠርሙስ፣ እያነሳሱ፣ ወይም ጠረጴዛውን እያፀዱና እያስተካከሉ “ታዟል? ምን ይምጣላችሁ? …” እያሉ እንግዶቻቸውን ያስተናግዳሉ፡፡ እንግዳ የሆነ ሰው የሆቴሉ ኃላፊ እንጂ ባለቤት ናቸው ብሎ አይገምትም  - አቶ ገ/ሥላሴ ወ/ገብርኤልን፡፡
የጋዜጠኞች ቡድን ለራያ ቢራ ፋብሪካ አ.ማ ምረቃ በሄድን ጊዜ መቀሌ አክሱም ሆቴል ነበር ያረፍነው፡፡ ሆቴሉ፣ ደረጃውን የጠበቀ ከመሆኑም በላይ የአክሱምንና በክልሉ የሚገኙትን አብያተክርስቲያናት ባህላዊ ይዘት ለማላበስ የተደረገው ጥረት ግሩም ነው፡፡ እዚያው ግቢ ውስጥ ከመግቢያው ፊት ለፊት የተሰራው ባለ 7 ፎቅ ሕንፃ ዲዛይን ቀልብን ይማርካል፡፡ ለህወሓት 40ኛ ዓመት ምስረታ በዓል ከላይ ወደታች የተለቀቀው የኢትዮጵያና የህወሓት ባንዲራ የተለያየ ቀለማት ባለው ብርሃን ታጅቦ ሲታይ ልዩ ውበት አጎናፅጎታል፡፡ ሆቴሉ የማን እንደሆነ የማወቅ ፍላጎት አደረብኝና “የማነው?” ስል ጠየቅሁ፡፡
“የአክሱም ነዋ! በቅርቡ ነው የተመረቀው” ተባልኩ፡፡ ይኼኔ፣ ባለቤቱን ለማነጋገር ተነሳሳሁ፡፡
አቶ ገ/ሥላሴ ግን መስራት እንጂ ሚዲያ አይወዱም፡፡ እኔ ግን ዕድለኛ ሳልሆን አልቀርም፡፡
አቶ ገ/ሥላሴ፣ ሜክሲኮ ከዋቢ ሸበሌ ሆቴል ጎን የነበረው ሎምባርዲያ ባርና ቴስቶራንት (አሁን ቦታው ለልማት ስለተፈለገ ቆሟል)፣ አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ ጎዳና ላይ የሚገኘው አክሱም ሆቴል እንዲሁም በመቀሌ ከተማ የሚገኙት ሁለቱ የአክሱም ሆቴሎች ባለቤት ናቸው፡፡ አዛውንቱ፣ እንዴት ለዚህ ስኬት በቁ? ምስጢሩ ውስብስብ አይደለም፡፡ ዓላማን ሰንቆ፣ የወጠኑት ግብ ላይ ለመድረስ ተግቶ መስራትና መጣር ነው፡፡
ባለሀብቱ በአዲግራት ዞን፣ በሃውዘን ወረዳ በ1936 ዓ.ም ከገበሬ ቤተሰብ ተወልደው እዚያው ያደጉ ሲሆን በትምህርት ከ5ኛ ክፍል በላይ አልዘለቁም፡፡ በ1950ዎቹ የትውልድ መንደራቸውን ጥለው ስራ ፍለጋ ወደ መቀሌ ከተማ ሲመጡ የገጠማቸው ምግብ ቤት ውስጥ በአስተናጋጅነት ተቀጥሮ መስራት ነበር፡፡ ከዚያም ወደ ሆቴል ቤት ተሸጋግረው በለመዱት  ሙያ ለተወሰነ ጊዜ ሰሩ፡፡ በታታሪነትና በጉብዝናቸው ተመርጠው፣ ለጥቂት ጊዜ በኃላፊነት እየሰሩ መንጃ ፈቃድ አወጡ፡፡
መቀሌ፣ ከዚያ በላይ መቆየት አልፈለጉም፣ እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል ብለው በ1960ዎቹ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ፒያሳ አካባቢ፣ ከጣይቱ ሆቴል ጀርባ ሆሮስኮፓ ፒዜሪያ በተባለ የጣሊያኖች ባርና ሬስቶራንት ውስጥ ተቀጥረው መስራት ጀመሩ፡፡ እዚያ እየሰሩ እያለ የ1966 አብዮት ፈነዳ፡፡ በዚህ ጊዜ ጣልያኖቹ ለሕይወታቸው ስለገሱ ባርና ሬስቶራንቱን እዚያው በአስተናጋጅነት ለሚሰሩት አራት ኢትዮጵያውያን ሸጠው ወደ አገራቸው ሄዱ፡፡
በድፍረት ሆቴሉን ከገዙት አራት ሰራተኞች መካከል አንዱ አቶ ገ/ሥላሴ ናቸው፡፡ በወቅቱ ያጠራቀሙትን ጥሪት አንድ ላይ አድርገውና ከባንክም ተበድረው ሬስቶራንቱን በ27ሺ ብር ገዙ፡፡ በርትተው በመስራትም የባንኩን ብድር ከመክፈላቸውም ባሻገር እዚያው ፒያሳ የአሁኑ ብሔራዊ ሎተሪ አካባቢ ከኮንትኔንታል ሆቴል በስተጀርባ ሌላ ፒዜሪያ ገዝተው ለአንዱ ሸሪካቸው ሰጡ፡፡ ከዚያም ሎምባርዲያ ተገዝቶ ለአቶ ገ/ሥላሴ ሲሰጥ፣ ኢሚግሬሽን አካባቢ ሐረር ሆቴል የሚባለው ተገዝቶ ለአራተኛው ሸሪካቸው ተሰጠ፡፡ በዚህ ዓይነት አራቱም ሸሪኮች የየራሳቸውን ድርጅት ይዘው መስራት ቀጠሉ፡፡
በ1981 ዓ.ም ደርግ ቅይጥ ኢኮኖሚ ሲያውጅ የነበራቸውን ገንዘብ ይዘው፣ 22 አካባቢ ትንሽ መሬት ገዝተው ባለ 30 መኝታ ቤት የመጀመሪያውን አክሱም ሆቴል ሰሩ፡፡ የሆቴሉ ግንባታ በ1984 ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡ የመጀመሪያው ቦታ በጣም ጠባብ ስለነበር በአጎራባች ከነበሩት ሁለት ሰዎች ቦታ ገዝተው በማስፋፋት መኝታ ክፍሎቹን ወደ 60 አሳደጉ፡፡ ሆቴሉ አልጋ ብቻ ሳይሆን ለሰርግ፣ ለስብሰባ፣ … የሚያገለግሉ አዳራሾች፣ ዘመናዊ ጂም፣ ሳውናና ስቲም ባዝ፣ የወንድና የሴት መዋቢያ ክፍሎች፣ ሱቆች፣ ባርና ሬስቶራንት፣ ላውንደሪ፣ … እንዲኖረው መደረጉን አቶ ገ/ሥላሴ ገልፀዋል፡፡
የአዲስ አበባው ማስፋፊያ ከተጠናቀቀ በኋላ በ1989 ተመሳሳይ ስም ያለው ሆቴል ለመገንባት በልጅነታቸው የአስተናጋጅነት ሥራ ወደ ጀመሩበት መቀሌ ተሻገሩ፡፡ እዚያም ሰፊ ቦታ በምሪት ወስደው፣ ባለ አራት ፎቅ ሆቴል ሰሩ፡፡ ሆቴሉ ደረጃቸውን የጠበቁ 60 የመኝታ ክፍሎች እንዲሁም እስከ 1000 ሰዎች የሚያስተናግድ ትልቅ አዳራሽ አለው፡፡ ሌሎች አነስ ያሉ አዳራሾች፣ ሰፊ መኪና ማቆሚያ፣ ልብስ ማጠቢያ፣ የጉድጓድ ውሃ ማጣሪያ፣ ዘመናዊ ጂም፣ ሳውናና ስቲም ባዝ፣ የሴቶችና የወንዶች መዋቢያ፣ ሱቆች፣ ተሟልተውለት በ1991 ዓ.ም ተመርቋል፡፡
እዚያው ግቢ ውስጥ፣ ግንባታው በ2000 ዓ.ም የተጀመረውና ከሦስት ዓመት በፊት አገልግሎት መስጠት የጀመረው አዲሱ ባለ 7 ፎቅ ሆቴል፤ ለህውሓት 40ኛ ዓመት አከባበር በመጡ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተይዞ ነበር፡፡
ሆቴሉ፣ በቅርቡ አገልግሎት የሚጀምርና ከህንፃው ጀርባ ባለ ቦታ ላይ በተሰራ ባለሁለት ፎቅ ሕንፃ ውስጥ 15 x 12 ሜትር ርዝመትና ስፋት ያለው መዋኛ አለው፡፡ እንዲሁም ሰፋፊ ክፍሎች ያሉት ዘመናዊ ጂም፣ ስቲም፣ ሳውናና ሞሮኮ ባዝ፣ ፋስት ፉድ ማዘጋጃ ዘመናዊ ኪችን፣ ባርና መዝናኛ … ተሟልተውለታል፡፡
በዚህ ህንፃ አናት ላይ (ቴራስ ባር) ሆነው የመቀሌ ከተማን በአራቱም አቅጣጫ እየተመለከቱ ለመዝናናት ምቹ ነው፡፡ ሆቴሉ ሲንግል፣ ደብል፣ ስዊትና ሰሚ ስዊት የተባሉ መኝታ ክፍሎች ሲኖሩት እንደየክፍሎቹ ደረጃ፣ የቁም የገንዳና የጃኩዚ መታጠቢያ አላቸው፡፡ ግቢው ውስጥ ያሉት ሁለቱ ሆቴሎች በአጠቃላይ 7 አዳራሾች፣ 4 ባርና 4 ኪችን አሏቸው፡፡
እስካሁን ድረስ ከሆቴሎችና ቱሪዝም መ/ቤት ለሆቴሎች የተሰጠ ደረጃ ባይኖርም፣ አቶ ገ/ሥላሴ የመቀሌው ቁጥር 1 አክሱም ሆቴል ባለ 4 ኮከብ እንደሆነ ቁጥር 2 ግን “ባለ 5 ኮከብ ሆቴል ሊያሟላቸው የሚገቡትን ዘመናዊ ፋሲሊቲዎች ስላሟላን፣ የጎደለም ነገር ካለ እናሟላለን እንጂ ከ5 ኮከብ በታች አንቀበልም፡፡ ደረጃ ማለት አንዴ ተሰጥቶ ዝም የሚባል አይደለም፡፡ በየሶስት ዓመቱ የሚታደስ ነው፡፡ የህንፃው መቆም ብቻ ዋጋ የለውም፡፡ አያያዝ…፣ የተማረ የሰው ኃይል፣ ጥሩ መስተንግዶ፣ … ስለሚያስፈልግ፣  ደረጃችንን ጠብቀን ለመቆየት ጠንክረን እንሰራለን” በማለት ገልፀዋል፡፡
“እኔና ሚስቴ ጠንክረን በመስራት ነው ለዚህ የደረስነው፡፡ ባለቤቴ ሌሊት በ11 ሰዓት ተነስታ መርካቶ ሄዳ ለሆቴሉ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ሸምታ ትመጣለች፡፡ በርበሬውን ገዝታ፣ ለቅማና ደልዛ ታስፈጫለች፡፡ መስተንግዶው ደግሞ የእኔ ነው፡፡ በጋራ የምንሰራቸው ነገሮችም አሉ፡፡ አሁንማ ልጆቻችን ስለደረሱ እየረዱን ነው፡፡ ሰው’ኮ የተፈጠረው ለመስራት ነው፡፡ ስራ ሳይንቅ ካልሰራ ማደግና መለወጥ ስለማይችል ህይወት ዋጋ አይኖራትም…” በማለት ሌሎችም የእሳቸውን አርአያ እንዲከተሉ መክረዋል፡፡

Read 5894 times