Monday, 02 March 2015 10:14

እናትን ፍለጋ

Written by  መሐመድ ነስሩ
Rate this item
(9 votes)

የመክሰስ ሰዓት ነው፡፡
“እማ….” አለ ትንሹ እዮኤል ፈራ ተባ እያለ
“ምን ፈለግክ?” አለችው እናቱ ፊትዋን እንዳጨለመች
“ራበኝ!”
“የሚበላ ነገር የለም!”
“ማሚ…በጣም እኮ ነው የራበኝ” አለ እዮኤል፤ በልጅ አንደበቱ በፍርሃት እንደተያዘ፡፡
“አይ… እንግዲህ ነገርኩህ…ቻለው!”
እዮኤል ዝም ብሎ ዓይኑን እያቁለጨለጨ ያያት ገባ፡፡ በቆመበት ትታው ወደ ጓዳ ገባች፡፡
የሆነ የሚበላ ነገር ልትፈልግልኝ ይሆናል ብሎ አሰበ እዮኤል፡፡ ግን አይደለም፡፡ ወደ ጓዳ የገባችው የሱን የረሃብ ጥያቄ ልትመልስ ሳይሆን ጉዳይዋን ለመፈፀም ነበር፡፡ የራስዋን ጉዳይ፡፡ ጉዳዩ ምንድነው? ..ምንም አያገባንም፡፡ ስለዚህ ዝም ብለን እንለፈው፡፡
ሁለቱ ወንድሞቹ መክሰሳቸውን በልተው ውጪ እየተጫወቱ ነው፡፡ ምንድነው የሚጫወቱት?
ብይ፣ ቆርኪ፣ ሰኞ ማክሰኞ፣ ሱዚ፣ ኳስ፣ …. ወይም ከእነዚህ አንዱን፡፡ ወይም ከእነዚህ ሁለቱን፡፡ ወይም…
ከትምህርት ቤት የመጡት አብረው ነው፡፡ ዩኒፎርማቸውን ቀይረው እንደጨረሱ እናቱ እሱን ወደ ሱቅ ልካው፤ ለሁለቱ ልጆችዋ የሚበሉትን አቀረበችላቸው፡፡ እዮኤል ወደ ሱቅ የተላከው ክብሪት ግዛ ተብሎ ነው፡፡ ክብሪቱ ተፈልጐ ግን አልነበረም፡፡ በርካታ ክብሪት በፓኮ ፓኮ ሆኖ ቁምሳጥን ውስጥ ተቆልፎበታል፡፡ እዮኤል ወደ ሱቅ የተላከው ዞር እንዲል ስለተፈለገ ነው፡፡ ዞር ባለበት ወንድሞቹ መክሰሳቸውን በልተው ጨረሱ፡፡ እዮኤል ባዶ ሆዱን፣ የወስፋቱን ጩኸት እያዳመጠ ክብሪቱን ይዞ ገባ፡፡ እሱ (እዩኤል) ሲገባ እነሱ (ወንድሞቹ) ወጡ!
“እማ…እማ…” አለ እዮኤል፤ ሆዱን ይዞ እየተንቆራጠጠ፡፡ ማለት የፈለገውን አላለም፡፡ ማለት የፈለገው ምን ነበር? ጠፋበት፡፡ እና ዝም አለ፡፡ እናቱ የለበሰችው ረጅም ቀሚስ ላይ ነጠላዋን ደርባ ወጣች፡፡ ወዴት እየሄደች እንደሆነ አላወቀም፡፡ ሊከተላት ከጀመረ በኋላ እግሩ ተሳስሮበት እዚያው በቆመበት ደርቆ ቀረ፡፡
ሄደች እናቱ…….
እናቱ ሄደች….
ምናልባትም የሄደችው ጓደኛዋ ኤልሳ ጋር ይሆናል፡፡ ኤልሳን አብዝቶ ይወዳታል - እዮኤል፡፡ ፍቅር ትሰጠዋለች፡፡ እናቱ የነፈገችውን ፍቅር ከእሷ ነው የሚያገኘው፡፡
እቤት ስትመጣ፤
“እዩ……” ብላ ትጠራዋለች፡፡
“አቤት!”
“ና የኔ ቆንጆ”
ፀጉሩን በፍቅር ታሻሽለታለች፡፡ ሁለት ጉንጩን፣ ግንባሩን፣ አፍንጫውን፣ አገጩን፣ አንገቱን እያፈራረቀች ትስመዋለች፡፡
“አንተም ሳመኝ…” ስትለው እሱም አፀፋውን ይመልሳል፡፡ ጉንጭዋን ፣ ግንባርዋን፣ አፍንጫዋን፣ አገጯን፣ አንገቷን እያገላበጠ ይስማታል፡፡ የእናቱ ጓደኛ ኤልሳ ከወንድሞቹ ናትናኤልና በረከት ይልቅ ለእሱ ታደላለች፡፡ ለምን እንደሆነ አያውቅም፡፡ ግን ታደላለች፡፡ ህፃኑ እዮኤል የተመስገንን ትርጉም በአግባቡ ባያውቅም “ተመስገን!” ይላል እሷን ሲያገኝ፡፡ ወይም ሲያይ ወይም ስትስመው ወይም ሲስማት፡፡ ምን እንደሆነ በማያውቀው የፍቅር ሰንሰለት ተሳስረዋል - ሁለቱ - እዮኤልና ኤልሳ፡፡
አንዳንዴ ወደ ቤትዋ ይዛው ትሄዳለች፡፡ ትሄድና ምን የመሰለ ቀይ በርበሬ እንደ ሊፒስቲክ የተቀባ፣ በቅቤ ያበደ ፍርፍር ትሰራለታለች፡፡ ትሰራለትና በዝርግ ሳህን አድርጋ ታቀርብለታለች፡፡ እዮኤል አንገቱን ደፍቶ በተመስጦ ይመገባል፡፡ እያንዳንዱን ጉርሻ እያጣጣመ፡፡ ላጣጣመው እያንዳንዱ ጉርሻ ትርጉም እየፈለገ፡፡ ፍርፍርንና የፍርፍርን ምንነት እየተነተነ፡፡ ትርጉም አለው፤ እያንዳንዱ ጉርሻ ትርጉም አለው፡፡
ኤልሳ ቤት ሲመጣ የሚበላው ፍርፍሩን ብቻ አይደለም፡፡ ፍርፍሩንም ይበላል፡፡ ግን ከፍርፍሩ በላይ የሚበላው ፍቅርን ነው፡፡ በቅቤ ከወዛው ብጥስጥስ እንጀራ ውስጥ እራሱን እያየ፤ በዕድሉ እያዘነ፡፡ ሲጐርስ እየተፅናና፡፡ አንዳንዴ አጠገቡ ቁጭ ብላ ታጐርሰዋለች፡፡ ጉርሻዋን እየተስገበገበ ይውጣል፡፡ ከመብላቱ በላይ የሚያጐርሰው ሰው መገኘቱ እየደነቀው፣ ከጉርሻው ይልቅ ከጉርሻው ጀርባ ያለው ትርጉም እየመሰጠው በልቶ ይጨርሳል፡
አሁን እናቱ ጓደኛዋ ኤልሳ ጋ ሄዳ ይሆናል ብሎ ሲያስብ ኤልሳን አስታወሰ፡፡ አስታወሰና “ምን ነው አሁን በመጣች?” አለ፡፡ ፍርፍሩ፣ ምግቡ ቀርቶ መጥታ እንዲሁ ስትስቅለት፣ ስታጫውተው፣ ስታወያየው፣ ስትዳስሰው፣ ስትስመው…፡፡ ይሄ ቢሆን አሁን የተሰማው ባዶነት ይቀንስለት ነበር፡፡ የተሰማው ቅዝቃዜ ይለቀው ነበር፡፡ አዎ! የሰው አልባነት ስሜትና የብቸኝነት ቅዝቃዜው ይለቀው ነበር፡፡
“ወደ ቤትዋ ቀጥ ብዬ ብሄድስ?” ብሎ አሰበ፡፡ አይሆንም፡፡ እናቱ እዚያ ትኖር ይሆናል፡፡ ከኖረች ደግሞ በዋዛ አትለቀውም፡፡ “አንተ ቀላዋጭ!” ብላ ትጮህበታለች፡፡
“ምን ልትቀላውጥ መጣህ?”
…ከወንድሞቹና ከሰፈሩ ልጆች ጋር ሊጫወት አስቦ ወደ ደጅ ወጣ፡፡
የሰፈሩ ማቲዎች መንደሩን ሞልተውታል፡፡ ሌሎቹን ትቶ ወንድሞቹ ወደነበሩበት ቦታ ሄደ፡፡ ጥምጥሞ እየተጫወቱ ነበር፡፡
“አለሁበት…….” አላቸው፡፡
ወንድሙ በረከትና የሰፈሩ ልጅ ፍራኦል ናቸው እየተጫወቱ ያሉት፡፡ ሌላኛው ወንድሙ ናትናኤል ቆጣሪ ነው፡፡ አንዱ ሲሸነፍ ቦታውን ለመረከብ ነቅቶ እየጠበቀ ነው፡፡
“ካንተ ቀጥዬ ቆጣሪ ነኝ” አለ እዮኤል፡፡ ተስማሙ፡፡ እነሆ የእዮኤል ተራ ደረሰ፡፡ ያሸነፈው የሰፈሩ ልጅ ፍራኦል ነው፡፡ ስለዚህ እሱን (ፍራኦልን) ሊገጥመው ነው፡፡ ጨዋታው ተጀመረ፡፡
እዮኤልና ፍራኦል ብዙ ተፎካከሩ፡፡ ፍራኦል ጨዋታውን ባሸናፊነት የምወጣበት ምት ነች ብሎ ሲመታ እዮኤል ይመልስበታል፡፡ እዮኤል አሁን የወንድሞቼን ሽንፈት የምበቀልበት ምት ነው ብሎ ጥርሱን ነክሶ ሲመታ፤ ፍራኦል እግሩን አንስቶ ይመልስበታል፡፡ ብዙ ተፎካከሩ፡፡
እዮኤል አሸነፈ፡፡ ረሀቡን ረሳ፡፡ ደስ አለው፡፡ ናትናኤል ገባ፡፡ ወንድማሞቹ እነ እዮኤልና ናትናኤል ለመሸናነፍ ትግል ገጠሙ፡፡ እዮኤል ጥሩ እየተጫወተ ሳለ መሀል ላይ ሰውነቱ ጨርቅ ሆነበት፡፡ ደከመ፡፡ ሆዱ ጮኸ..አቅለሸለሸው፡፡ ወደ ላይ ሊለው ሲል፣ ጨዋታውን ትቶ አንድ ጥግ ላይ ባለ ድንጋይ ላይ ሄዶ ተቀመጠ፡፡
እናቱ “ልጆች” እያለች ወደ ቤት ገባች፡፡ እዮኤል ተጠቅልሎ በተኛበት ሆኖ፤
“አቤት!” አለ፡፡ ሠላምታም ሳትሰጠው “እ…አንተ ነህ?” ብላ አለፈች፤ እንደ ዋዛ፡፡ …ጓዳ ገብታ መንጐዳጐድዋን ጀመረች፡፡
እዮኤል ከተኛበት ተነስቶ ወደ እናቱ ሄደ፡፡
“እማ….”
“እ?”
“ቆሎ እንኳን የለም?” አላት ድምፁን አለሳልሶና ሀዘን አልብሶ፡፡
“የለም!” አለችው፡፡
“አሁን ደግሞ የእራት ሰዓት ደርሶ የለ እንዴ? ምንአስቸኮለህ ቀስ ብለህ ትበላለህ”
ቁጣዋን ስለፈራ፤ “እሺ” አለ፡፡ “እሺ” ብሎ ወደ አልጋው ተመለሰ፡፡ እና ጥቅልል ብሎ ተኛ፡፡ እንቅልፍ ግን አልወሰደውም፡፡ እንቅልፍም አልተኛም፤ የሆዱ ጩኸትም አልተቋረጠም፡፡ ሆዱ ውስጥ የሆነ ኦርኬስትራ ያለ መሰለው፡፡  ዜማው ሙሾ ነው፡፡ ምቱ ግን ልክ አይደለም፡፡ የተዘበራረቀ ነው፡፡ አንዴ በሐይል ይጮኻል፡፡ አንዴ ለስለስ ብሎ ይደመጣል፡፡ ግራ የገባው ኤርኬስትራ!
በረከትንና ናትናኤልን ከዚህ በፊት ጠይቋቸው ያውቃል፡፡ ስለ ማን? ስለ እናቱ፡፡
“በረከት” አለ እዮኤል
“አቤት!” አለ በረከት
“ናቲ!” አለ እዮኤል
“አቤት!” አለ ናትናኤል
“እማዬ ግን ለምንድነው የማትወደኝ?” ብሎ ጠየቃቸው፤ ሁለቱንም አፈራርቆ እያየ፡፡
“ኧረ ትወድሃለች” አለ በረከት
“አትወደኝም” አለ እዮኤል
“ለምን አትወድህም? ትወድሃለች እንጂ?”  አለ ናትናኤል፡፡
ሁለቱም ሊያፅናኑት እየሞከሩ ነበር፡፡ እንጂ እውነቱን ያውቁታል፡፡ ምክንያቱ ተሰወራቸው እንጂ ውጤቱ ለእነሱም ግልፅ ነው ወይም ነበር፡፡ እናታቸው ወንድማቸው እዮኤልን አትወደውም! አራት ነጥብ፡፡ ለምን እንደሆነ ግን አያውቁም፡፡
…ፀጋውና ፅጌ የሚዋደዱ ባልና ሚስት ነበሩ፡፡ በፍቅር “እፍ” ያሉ ጥንዶች፡፡
የፅጌ ፍቅር ግን ለየት ያለ ነበር፡፡ ባልዋን አብዝታ ትወደዋለች፡፡ ችግር እንዲገጥመው፤ እንቅፋት እንዲመታው አትፈልግም፡፡ አብራው ውላ፣ አብራው ብታድር ትወዳለች፡፡ ጠረኑን እየማገች ለዘላለም ብትኖር ደስ ይላታል፡፡ ከውጪ ሲመጣ ቤቱን አስውባ የሚወደውን ምግብ ሰርታ ትጠብቀዋለች፡፡ እየበላ የሚበላ አይመስላትም፡፡ አሁን አሁን የሚራብ ይመስላታል፡፡ እየተጫወተ የሚጫወት አይመስላትም፡፡ ዝም ካለ የሚቆዝም ይመስላታል፡፡ እየሳቀ የሚስቅ አይመስላትም፡፡ እሷ እንደምትፈልገው ወይም በምትፈልገው ደረጃ ሀሴት የሚያደርግ አይመስልም፡፡
ፍቅርዋ የእናት እንጂ የሚስት አይመስልም፡፡ ትሳሳለታለች፡፡ ልጆች ወልዳ እንኳን ከልጆችዋ የበለጠ እሱን ትንከባከበዋለች፡፡ እሱን ትወደዋለች፡፡ እሱን ታፈቅረዋለች፡፡
“ልጆችሽስ?” ስትባል፤ “ተዋቸው ባካችሁ… እነሱ ከፀጋው በኋላ የመጡ ናቸው፡፡ በብቸኝነቴ ዘመን የተንከባከበኝና ደስታን የሰጠኝ ፀጋው ነው፡፡ በዚያ በብቸኝነት ዘመናችን ያልዋለልኝ ውለታ፣ ያላደረገልኝ ነገር አልነበረም፡፡” ትላለች፡፡
“ለልጆቼ የምሆነው ለባሌ ከሆንኩ በኋላ ነው፡፡” ብላ ትናገራለች፡፡
በእርግጥ ልጆችዋን ትጠላቸዋለች ማለት አይደለም፡፡ ትወዳቸዋለች፡፡ ሌላው ቢቀር ፍሬዎችዋ መሆናቸውን አትክድም፡፡ የእሱ ልጆች በመሆናቸው ብቻ እነሱን (ልጆችዋን) ወዳም ባይሆን ተገዳ ትወዳቸዋለች፡፡ የፀጋው የዘር ፍሬ ናቸው፡፡ ለዚህ ምክንያት ስትል ብቻ ትወዳቸዋለች፡፡
ምንም ይሁን ምንም የፀጋው ማስታወሻዎች፤ የፀጋው ማስረጃዎች ናቸው፡፡ የማትወደው የመጨረሻ ልጅዋን እዩኤልን ነው፡፡ “ገፊ ነው!” ትለዋለች፡፡ እንደ አባትዋ ገዳይ ትቆጥረዋለች፡፡ነፍሰ  - ገዳይ ይመስላታል፡፡ ክላሽንኮቭ አላነገበም፡፡ ጩቤ አልያዘም፡፡ ጦር አልነቀነቀም፡፡ ግን ትጠላዋለች፡፡
“ይሄ እርኩስ ባልተወለደ ኑሮ ምን ነበር?” ትላለች፡፡
ታሪኩ እንዲህ ነው፡፡ ፀጋውና ፅጌ በፍቅርና በሰላም “እኔ ልሙትልሽ”፣ “እኔ ልሙትልህ” እየተባባሉ ይኖሩ ነበር፡፡ በመሀል እዮኤል ተፀነሰ፡፡ የሰው ህይወት ሊያጨናግፍ፤ እሷን ባል አልባ ሊያደርግ ተፀነሰ፡፡ ፅንስ ሳለ እንደ ማንኛውም እናት ልታየው ትጓጓ ነበር፡፡ “ልጄ!” ብላ ሆድዋን ትዳብስ፣ ታሻሽ ነበር፡፡
ሶስተኛውን ልጅዋን እንደ ሁለቱ ልጆችዋ ሁሉ በፍቅር የማሳደግ ተስፋ ነበራት፡፡ ከፀጋው ጋር እየተቀባበሉ ሲስሙትና ሲያጫውቱት ይታያት ነበር፡፡ አልሆነም፡፡ ለምን?! …
ፅጌ ምጥ ያዛት፡፡ ጎረቤቶች ተሰብስበው ሆስፒታል ወሰድዋት፡፡ ፀጋው ስራ ቦታው ነበር፡፡ ተደውሎ ተነገረው፡፡ ስራውን ጥሎ እየሮጠ መጣ፡፡ ለምታምጠው ሚስቱ ብርታት ሊሆናት፡፡ ልጁ ከእናቱ ማህፀን እንደወጣ ለማየት፡፡ እና ሊስመው፡፡ መጣ፡፡ ሆስፒታሉ ጋ ደረሰ፡፡
ሚስቱና ልጁ ጋ ለመድረስ ተቻኩሎ ሲከንፍ፤ እሱ ያላየው፣ የቆመውን ታክሲ ደርቦ የሚመጣ አንድ መኪና አገኘው፡፡ ፀጋው ተገጨ፡፡ ውሎ አላደረም፡፡ ከሰዓታት በኋላ ህይወቱ አለፈ፡፡ ፅጌ እንደ እብደት ነገር ቃጣት፡፡ ጮኸች፡፡ አለቀሰች፡፡ የምትወደው፣ የምታፈቅረው ባልዋ መንገድ ላይ ቀረባት፡፡ እንደወጣ ወደ ቤቱ ላይመለስ እስከ ዘላለሙ ተለያት፡፡ ፅጌ ጭንቀት እንደ አዞ አፉን ከፍቶ ዋጣት፡፡ ሀዘን በላይዋ ላይ ጎጆውን ሰራ፡፡
አራስ ልጅዋን ማጥባት እንኳን አስጠላት፡፡ እስከነመፈጠሩም ረስታ ከባልዋ ጋር ያሳለፉትን መልካም ጊዜ እያስታወሰች፤ በትዝታ ተሰቃየች፡፡
“እግዜር ያመጣው ነው” አሏት ጎረቤቶችዋ
“ቻይው፤ … እግዚአብሔር ልጆችሽን ያሳድግልሽ!”
“እግዜር ያመጣው አይደለም፡፡” አለች ፅጌ
“ይሄ የተረገመ ልጅ ያመጣው ነው፡፡” ወደ አራሱ ልጅዋ እያየች፡፡
ባልዋን በአጭሩ የቀጨባት እሱ እንደሆነ አሰበች፡፡
“ገፊ የሆነ ልጅ!” አለች፡፡
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ለእዩኤል ሆድዋ አልተፈታም፡፡ አቄመችበት፡፡ ልጅ መስሎ አልታይሽ አላት፡፡
“የባሌ ነፍሰ ገዳይ ነው” ብላ ደመደመች፡፡
ለምን?!
“እሱን ለመውለድ ሆስፒታል ባትገባ ኖሮ፤ ተደውሎ ባይነገረው ኖሮ፤ ልጁን ለማየት ባይጓጓ ኖሮ፤ ወደዚህ አይመጣም ነበር፡፡ ወደዚህ ባይመጣ ኖሮ ደግሞ አይገጭም ነበር፡፡ ባይገጭ ኖሮ  አይሞትም ነበር፡፡ ይህን ሁሉ ጣጣ ያመጣብኝ ይህ ልጄ ነው፡፡”
እና ለልጅዋ እዩኤል ያላት ፍቅር እንደ ሁለቱ ልጆችዋ በረከትና ናትናኤል ሊሆን አልቻለም፡፡ የልጅዋ ዓይን ውስጥ እየያች ባልዋ ፀጋውን ታስታውሳለች፡፡ ስሙ ሲጠራ ፀጋውን ስታውሳለች፡፡ ስታየውም ፀጋውን ታስታውሰዋለች፡፡ እዩኤል ራስ ምታትና የጭን ቁስል ሆነባት፡፡ እንዳታባርረው ልጅ ሆነባት፡፡ እንደ ልጅ እንዳትንከባከበው ሆድዋ እምቢ አላት፤ ገፊነቱ ከዓይንሽ አልጠፋ አላት፡፡ “የባሌ ነፍሰ ገዳይ” የሚል ሀሳብ ተፈታተናት፡፡ እና እዩኤልን አትወደውም፡፡ …
… የእራት ሰዓት ደረሰ፡፡ ልጆችዋ ሁሉ ለእራት ተጠርተው ጠረጴዛው ዙሪያ ታደሙ፡፡ በረከትና ናትናኤል አልበላም ሲሉ በግድ ተለማምጣና ለምና ታበላቸዋለች፤ እዩኤል በላ አልበላ ግን ግድ የላትም፡፡ አሁን እራት ቀርቧል፡፡ አራቱም ሳህናቸውን አነሱ፡፡ ለበረከትና ናትናኤል እፍታ እፍታውን ጨመረችላቸው፡፡ አጥንት አጥንቱን ሳህኖቻቸው ላይ ከመረች፡፡ ለእዩኤልም ከወጡ ሰጠችው፡፡ አጥንት ግን አልደረሰውም፡፡ ተከለከለ፡፡ በረከትና ናትናኤልን ማጉረስ ጀመረች፡፡ ሁለቱን ካጎረሰች በኋላ እንጀራ ስትጠቀልል “እኔንም ልታጐርሰኝ ነው” ብሎ ጠበቀ እዩኤል፤ አላደረገችውም፡፡ ለራስዋ ጎረሰችውና በረከትንና ናትናኤልን ደጋግማ ወደማጉረሱ ገባች፡፡
የእዩኤል የልጅ ልብ ሀዘን ቋጠረች፡፡ እንባው መጣ፡፡ ምግቡን ትቶ ተነሳ፡፡ ፅጌ ምንም አላለችውም፡፡ ናትናኤል “ወዴት ነው?” ሲል ጠየቀው፡፡
“እዚሁ ነኝ መጣሁ!” ብሎ ሲወጣ በረከት “ምን ሆነህ ነው? ና ብላ እንጂ!” አለው፡፡
“እሺ!” ብሎት ወደ መኝታ ክፍሉ አመራ፡፡
በረከትና ናትናኤል ይወዱታል፡፡ ከእነሱ ጋር እንዲበላ እንዲጠጣ ይፈልጋሉ፡፡ የእናታቸው ድርጊትም አያስደስታቸውም፡፡ ልጅ ስለሆኑ አፍ አውጥተው ሊነግርዋት ፈርተው እንጂ ቢናገርዋት፣ ቢቆጥዋት ይወዳሉ፡፡ ግን አልሆነም፡፡
እናት ከፋች! ታዲያ እነሱ ምን ያድርጉ?! እዩኤል አልጋው ላይ ወጥቶ ተጠቅልሎ ተኛ፡፡  

Read 3505 times