Saturday, 14 January 2012 12:23

ከወሊድ በሁዋላ...ድብርት (Postpartum Depression)

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)
  • ከወሊድ በሁዋላ በሚፈጠር የአእምሮ ጭንቀት ወይንም ድብርት እናቶች እራራሳቸውንና የወለዱትን ልጅ በተለያየ መንገድሊጎዱይችላሉ፡፡
  • ልጅ ከተወለደ በሁዋላ የሚፈጠር የአእምሮ ጭንቀት ወንዶችንም ሊይዝ ይችላል፡፡

ከወሊድ በሁዋላ በጥቂት ወራራት ውስጥ አንዳንድ እናቶች ላይ የሚፈጠር የመንፈስ ጭንቀት ቀላል የማይባል ሕመም ነው፡፡ በተለይም እናቶች እርግዝናው በራራሱ ጊዜ ሲወርድና ሕይወት የሌለው ልጅ ወይንም የተለያየ የአካል ጉድለት ያለበትን ልጅ ሲገላገሉ የአእምሮ ጭንቀት ሊከሰት እንደሚችል ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡ ከወሊድ በሁዋላ ለሚከሰት የአእምሮ ጭንቀት የሚዳረጉት ሴቶች ከ5-25 % የሚደርሱ ሲሆን ወንዶችም የልጅ አባት ሲሆኑ ከ1.2-25.5% የሚሆኑት ለችግሩ ይዳረጋሉ፡፡ ይህንን በሚመለከት አንዲት ተሳታፊ ያደረሰችንን መልእክት እነሆ ለንባብ እንላለን፡፡

“..ልጄን ከማርገዜ ምፊት በጣም የሰላም ኑሮ የምኖር ...ከባለቤም ጋር የሚያስቀና ፍቅር ያለን ነበርን፡፡ በምንም ምክንያት አልበሳጭም ነበር፡፡ ከተጋባን ወደ አንድ አመት ገደማ ድረስ ልጅ ስላልወለድን የሚያሳስበኝ እሱ ብቻ ነበር፡፡ እናም...እርግዝናው እምቢ ይለኝ ይሆን እንዴ...የሚለው ብቻ ትንሽ ያሳስበኝ ነበር፡፡ ነገር ግን እርግዝናው ዘግየት ቢልም ተሳካ፡፡ ልጅ በተረገዘ ወደ ሶስተኛው ወር ጀምሮ ግን ባለቤ ችላ ይለኝ ጀመር፡፡ እንክብካቤው በጣም ቀነሰ፡፡ ምክንያቱን ይኼ ነው ብዬ እስከዛሬም ድረስ ልናገር አልችልም፡፡ እየረሳሁት ነው እንጂ ...በጊዜው የነበረውን ሁኔታ ሳስታውስ እጅግ አዝናለሁ፡፡የናፈቅሁትን ማርገዜን ጠልቼው ነበር፡፡ እንዲያውም ይቅርብኝ ብዬ ለማስወጣት ሁሉ አስቤ ነበር፡፡ ነገር ግን ...እና በአንድ በኩል ዘር እፈልጋለሁ...ውለጂ እንጂ...ትላለች፡፡ የእሱ እናት በበኩላቸው ...እንዴ...ልጅ የማትወልድ ናት እንዴ ሚስትህ ...ይላሉ፡፡ ይሄ አስጨንቆኝ እንጂ ባልወልደው ይሻለኛል ከሚል ውሳኔ ላይ ሁሉ ደርሼ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ምክንያቱም...ይህን ልጅ ብወልድስ ከባለቤ ጋር በምን ሁኔታ ልኖር ነው ? የሚል ከባድ ጭንቀት ነበር ያደረብኝ...፡፡ ባለቤ አንድ ቀን እንኩዋን አብሮኝ ሆስፒታል ሳይሄድ ነበር ልጄን የተገላገልኩት፡፡ ስወልድ ብቻ ነው ወደ ሆስፒታል በመውሰድ የተባበረኝ፡፡ ከወለድኩ በሁዋላም ከሆስፒታል ያወጣኝ የመስሪያ ቤቱ ሹፌር እንጂ እሱ አልነበረም፡፡ የሰጠው ምክንያትም ስብሰባ ላይ ነኝ የሚል ነበር፡፡ ወልጄ ወደቤ ከገባሁ በሁዋላ ግን ሕመም ተብሎ የማይገለጽ ነገር አእምሮዬን ረበ ሸው፡፡ የባለቤን ነገርማ አታንሱብኝ፡፡ ድምጹን ነበር መስማት ያቃተኝ፡፡ እሱ ሲመጣ ጀምሮ ጥቅልል ብዬ መተኛት ብቻ ሆነ ስራዬ፡፡ ልጄ ቢያለቅስ እንኩዋን ከአጠገቤ ውሰዱልኝ እላለሁ እንጂ ተነስቼ ጡት አልሰጥም ነበር፡፡ምግብ መብላት አልችልም ነበር፡፡  እና ጸበል እያመጣች እያጠመቀችኝ ልታድነኝ ብዙ ሞከረች፡፡ በሁዋላ ግን እህ የምታውቃትን የሳይኮሎጂ ባለሙያ አምጥታ እንደጉዋደኛ እያዋራች... እየመከረች ...እኔ ሳልነግራት እራስዋ እንዲህ ይሆን እንዴ ...እንደዚህ እኮ ነው ... እያለች በጣም እረዳችኝ፡፡ በሁዋላም ...ባለቤን ስታነጋግረው ...እኔ የሚፈለግብኝን ሁሉ አሟል ቻለሁ...ከእኔ ምን ትፈልግ ነበር...አትናገርም እንዴ... የሚል መልስ ነበር የሰጠው፡፡ በቃ...እኔም በእራሴ አቅም ልጄን መርዳት እንደምችል...ለእራሴም የምፈልገውን ነገር ማድረግ እንደምችል ከሌላ ሰው የምጠብቀው ነገር ካልተሟላ መተው እንዳለብኝ ከሳይኮሎጂ ባለሙያዋ ተረድቼ ...እነሆ ዛሬ ... ልጄ የሶስት አመት እድሜ ይዞአል፡፡ ድጋሚ ለመውለድ ግን ዛሬም ልቦናዬ አልፈቀደም፡፡ እፈራለሁ፡፡

የላንቹና ላንተ ፕሮግራም አዘጋጆች...ይህ ችግር የእኔ ብቻ አይመስለኝም፡፡ ሌሎችም በዚህ ጉዳይ የሚቸገሩ ሊኖሩ ስለሚችሉ እባካችሁ የባለሙያ ምክር ለግሱን”

...ናርዶስ አምሀ ከቃሊቲ...

(Postpartum Depression ) በወሊድ ጊዜ የሚከሰት የአእምሮ ጭንቀት ሴቶች በወለዱ ከአራት ሳምንት ጀምሮ ሊከሰት የሚችል ሲሆን ማብቂያው ከተወሰኑ ወራት እስከ አንድ አመት ሊደርስ ይችላል፡፡ ምናልባትም በትክክል የህክምና እርዳታ ካላገኘ ለከፋ ሁኔታ ሊጋብዝ ይችላል፡፡ በዚህ ርእሰ ጉዳይ የስነአእምሮ ሕክምና ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር አታላይ አለም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕክምና ፋክልቲ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ዶ/ር አታላይ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዳይሬክተር ናቸው፡፡

ዶ/ር አታላይ እንደገለጹት ልጅ መውለድ ተፈጥሮአዊ የሆነና እናትየውንም ሆነ አባትየውን የሚያስደስት መሆኑ የታመነበት ነው፡፡ እናቶች በእርግዝናቸው ወቅት ስለወደፊቱ ሁኔታ ማለትም በምን ሁኔታ ልጅ እወልድ ይሆን ?እንዴትስ አሳድገዋለሁ የሚሉት እና ሌሎችም ተያያዥ የሆኑ ነገሮች የሚያስጨንቋቸው ሲሆን ልጃቸውን በሰላም ሲገላገሉ ግን የሚጠበቀው ደስተኛ እንዲሆኑ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን ስሜታቸው በተቃራኒው መንገድ ይሄድና ልጃቸውን ከወለዱ በሁዋላ ሊያሳዩ የሚገባቸውን የደስታ ስሜት ማግኘት የማይቻልበት ሁኔታ ያጋጥማል፡፡ ብዙዎቹ እናቶች ልጃቸውን ከወለዱ በጥቂት ቀናት ውስጥ ስሜታቸው መረበሽ ፣የሚያዩትና የሚሆነው ነገር አለመገናኛት፣ ስለራሳቸው፣ ስለቤታቸው ፣ስለቤተሰባቸው የሚያስቡት ሁኔታና እውነታው አልገናኝ ስለሚላቸው የሀዘን ስሜት በውስጣቸው ይፈጠርና ስሜታቸው ይረበሻል፡፡ እናቶች ከእርግዝናው ጋራ በተያያዘ የሆርሞኖች ፣የንጥረ ነገሮች እና የተለያዩ ነገሮች ለውጦች ስለሚኖሩ እነዚህ ለውጦች ከአስተሳሰብ ወይንም ከአእምሮ ጋር ስለሚገናኙ በድንገት በሚቋረጥበት ጊዜ የአእምሮ መረበሽንና መጨነቅን ሊያስከትል የሚችል ሲሆን ነገር ግን ይህ ስሜት ቀላልና በብዙዎች ዘንድ የሚታይ ሕክምናን የማይፈልግ እና በጥቂት ጊዜያት በራሱ የሚወገድ ነው፡፡

ከላይ ከተገለጸው በተለየ በተለያዩ አገሮች በተደረጉ ጥናቶችከ 10-16 ከመቶ የሚሆኑ እናቶች ከወሊድ ጋር በተያያዘ የድብርት  ስቅቈስቋቋሽቄቃ የሚባለው የስሜት ለውጥን ያሳያሉ፡፡ ይህ ግን ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆይ ሕክምናንም የሚፈልግ ነው፡፡ በእርግጥ ይህ ስሜት በመውለድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን አልፎ አልፎ እናቶች ቀደም ሲልም ጀምሮ አብሮአቸው የቆየ ሊሆን እንደሚችል ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡

ከወሊድ በሁዋላ  ድብርት Depression የያዛቸው እናቶች የሚያሳዩት ምልክት

...የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ እንቅልፍ ማጣት ፣ጥልቅ የሆነ ብስጭት፣ የፍቅር ግንኙነት መቀነስ ፣የደስተኝነት መጠን መቀነስ ፣በጣም ከፍተኛ የሆነ የድካም ስሜት፣ የእፍረት ስሜት ፣የጥፋተኝነት ስሜት መጨመር፣ የፀባይ መለዋወጥ፣ ከልጅ ጋር ጥሩ ግንኙነት መፍጠር አለመቻል፣ እንዲሁም በእራስ ወይንም በተወለደው ልጅ ላይ ጉዳት ለማድረስ መሞከር...ወዘተ ናቸው፡

ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚታየው ድብርት Depression ምክንያቱ

እርግዝናውና ጽንሱ የተፈለገ መሆን ያለመሆን ፣

ከትዳር ጉዋደኛ ጋር ያለው ግንኙነት ፣

ከሴት አማት ጋር ያለው ግንኙነት ፣

የገቢ መጠን ማነስ ...ረሀብ፣

በወሊድ ጊዜ የሚጠብቁት ነገር ሳይሳካ ሲቀር፣

ድጋፍ ማጣት እና ስሜትን የሚጎዱ ችግሮች የደረሱባቸው ሴቶች ላይ በአብዛኛው ይታያል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም...

የሰውነት ለውጥ፡- ከወሊድ በሁዋላ በሰውነት ውስጥ ያለው የሆርሞን መጠን መቀነስ ፣የደም መጠን መቀነስ ወይም ግፊት መጨመር ለድካምና ለጸባይ መለዋወጥ ሊዳርጋት ይችላል፡፡

የስሜት ለውጥ፡-አንዲት እናት ከወለደች በሁዋላ ለመልኩዋ ፣ለቁመናዋ ያላትን አመለካከት ችላ ማለት ፣ በህይወቷ ላይ መወሰን ያለመቻል ፣ስጋት የመሳሰሉት ጭንቀትዋን ያባብሱታል፡፡

ኢኮኖሚ፡-  እናት የተወለደውንም ልጅ ለማሳደግ ይሁን በአራስነት ወቅት እራስ ዋን በትክክል ለመርዳት የሚያስችል አቅም ማጣት በወሊድ ጊዜ ለሚፈጠር ድብርት ይዳርጋል፡፡

የአኗኗር ሁኔታ፡-በቤት ውስጥ ስራን ለመስራት ድጋፍ የሚያደርግ ሰው አለመኖር ፣የኑሮ አጋርን ድጋፍ ማጣት ባል፣ በባህርይው አስቸጋሪ የሆነ ቀደም ብሎ የተወለደ ልጅ በቤት ውስጥ ካለና ካለእናቱ የሚዳኘው ሲጠፋ...ወዘተ

እንደ ዶ/ት አታላይ ማብራሪያ በኢትዮጵያ በዚህ ዙሪያ ጥናት የተደረገ ሲሆን በአብዛኛው በምክንያትነት የተገኘው ከሴት አማቶች ጋር አለመስማማትና ይደረግልኛል ብለው የሚጠብቁት ነገር አለመሟላቱ እንዲሁም የኑሮ ውጣ ውረድ ሲያበሳጨቸው ይህ ችግር እንደሚባባስ ጥናቱ ይጠቁማል፡፡  አንዲት እናት በዚህ ሁኔታ ድብርት ውስጥ ስትወድቅ መበሳጨትና አለመደሰትን በተደጋጋሚ ታሳያለች፡፡ ስለዚህ እንደዚህ ያለ ሁኔታ ሲታይ ቤተሰቡ በደንብ ትኩረት ሰጥቶ የወለደችውን ሴት ሊንከባከባት ይገባዋል፡፡

አንዲት ሴት ከወለደች በሁዋላ፡-

ጥሩ ስሜት የማይሰማት ከሆነ፣

ለነገሮች ትኩረት ማጣትና ማሰብን ማቋረጥ፣

ልጅዋን በትክክል መንከባከብ  ካቃታት፣

ለእራራስዋ ተገቢውን ለማድረግና በየእለቱ ልትወጣው የሚገባትን ግዴታ መወጣት ሲያቅታት፣

ልጅዋን የመጉዳት ስሜት ሲፈጠርባት...ወዘተ በአስቸኩዋይ ወደሐኪም ቤት መሔድ ይጠበቅባታል፡፡

 

ESOG – Ethiopian Society of Obsettricians and Gynacologists የኢትዮጵያ ፅንስና ማህፀን ሃኪሞች ማህበር ማለት ሲሆን ይህንን አምድ ከአድማስ አድቨርታይዚንግ ጋር በመተባበር የሚያቀርብላችሁ ድርጅት ነው፡፡ (በፖ.ሣ.ቁ 8731 ስልክ 011-5-506068/69 ልታገኙን ትችላላችሁ)

 

 

Read 3521 times Last modified on Saturday, 14 January 2012 12:33