Monday, 16 March 2015 09:06

የአዲስ አበባ ሆቴሎች በሰኔ ደረጃቸውን ያውቃሉ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

     በመላው ኢትዮጵያ ለሚገኙ 400 ያህል ሆቴሎች ደረጃ ሊሰጥ መሆኑን የባህልና ቱሪዝም ሚ/ር አስታወቁ፡፡ ሚኒስትሩ ክቡር አቶ አሚን አብዱልቃድር ሰሞኑን በአክሱም ሆቴል የተጀመረውንና ለአንድ ወር የሚቆየውን ሥልጠና በከፈቱበት ወቅት፣ ግማሽ ያህሉ ሆቴሎች (ከ150 እስከ 200) የሚገኙት በአዲስ አበባ ከተማ ስለሆነ፣ በመጀመሪያው ዙር የእነዚህ ሆቴሎች ደረጃ ይገለጻል ብለዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ቀጥሎ በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በአማራና በትግራይ ክልሎች፣ በተከታይም በሁሉም ክልሎችና መዳረሻ ቦታዎች ተፈጻሚ እንደሚሆን ታውቋል፡፡
የደረጃው አሰጣጥ በሶስት ምዕራፎች የተከፈለ መሆኑን የጠቀሱት ሚ/ሩ፤ “በመጀመሪያው ምዕራፍ ሁለት ወራት (መጋቢትና ሚያዝያ) ቅድመ ዝግጅት ይካሄዳል፡፡ ይኼውም ለባለንብረቱ፣ ለመንግስት አካላት ለፖለቲካ አመራሮች፣ … የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ይሰጣል፡፡ እንዲሁም በዚሁ ጊዜ እንዴት መግባባት እንደሚቻል የኮሙኒኬሽን መመሪያ የተዘጋጀ ስለሆነ፤ ለሚዲያ፣ ለዓለም አቀፍ ተጓዦች፣ ለአስጎብኚ ድርጅቶችና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት ሥልጠና ይሰጣል፡፡ በሁለተኛው ምዕራፍ፣ በግንቦት ወር፣ በዓለም አቀፉ የቱሪስት ድርጅት በተወከሉትና የሆቴሎችን ደረጃ በመመደብ ከ198 አገራት በላይ ልምድና እውቀት ባላቸው በሚ/ር ጀምስ የሚመራው 8 አባላት ያለው ቡድን የደረጃ ምደባውን ያካሂዳል፡፡ በሦስተኛው ምዕራፍ፣ በሰኔ ወር የምደባው ውጤት ለሆቴሎች ይነገራል” በማለት አብራርተዋል፡፡
የስልጠናው ተሳታፊዎች ከዘጠኙ ክልሎችና ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በጥንቃቄ የተመረጡ 52 የሆቴል ባለሙያዎች ሲሆኑ ዓላማውም ባለሙያዎች ስለሆቴል ደረጃ ምደባ፣ ሥርዓትና አፈጻጸም መረጃዎችን እንዲያገኙና የተግባር ልምምድ በማድረግ እውቀታቸውን እንዲያሳድጉ መሆኑን ሚ/ሩ ገልጸዋል፡፡
ሥልጠናውን የሚሰጠው በኢትዮጵያ ለሆቴሎች ደረጃ መስጠት ከተቋረጠ 12 ዓመት ስለሆነው፣ መንግሥት ዓለም አቀፍ የሆቴሎች ደረጃ መመዘኛ መስፈርት እንዲወጣ ወስኖ፣ በዓለም ያሉ ተወዳዳሪዎች እንዲሳተፉ ባወጣው ጨረታ ያሸነፈው “ዱኔራ” የተባለ ድርጅት ሲሆን ያዘጋጀውን የሆቴሎች ደረጃ መመዘኛ መስፈርት፣ የሆቴል ባለንብረቶች ማህበር፣ የቱሪዝም ባለሙያዎች፣ የሆቴል ባለሙያዎች ማህበራት፣ ባለድርሻ አካላት፣ የሚ/ር መ/ቤቱ ባለሙያዎችና የስራ ኃላፊዎች፣ የክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የሥራ ኃላፊዎች እንዲወያዩበት ተደርጎ፤ ሰነዱ፣ በኢትዮጵያ ደረጃዎች መዳቢ ካውንስል የኢትዮጵያ ሆቴሎች ደረጃ መመደቢያ እንዲሆን የፀደቀ መሆኑን አቶ አሚን አስረድተዋል፡፡
ሰልጣኞቹ፣ በዚህኛው ምድብ፣ ከውጭ የመጣው ቡድን ምን እንደሚሰራና እንዴት እንደሚመድብ ከመመልከት በስተቀር በምደባው ተሳትፎ እንደሌላቸው ጠቅሰው፣ አንድ ላይ ሆነው ለ15 ቀናት ሌትና ቀን የሆቴሎች ደረጃ ምደባ፣ ትግበራና ለወደፊት ስራቸው መሰረት የሚሆናቸውን የንድፈ ሀሳብ ትምህርት ሲከታተሉ፣ በቀሪው 15 ቀን ከደረጃ መዳቢዎች ጋር በየሆቴሉ በመዘዋወር የተግባር ልምምድ ያደርጋሉ ብለዋል፡፡
ለሆቴሎች ደረጃ ምደባ፣ ለእውቀት ሽግግርና ሥልጠና መንግስት 500ሺ ዶላር መመደቡን የጠቀሱት አቶ አሚን አብዱልቃድር፣ የሆቴሎች ደረጃ በቀጣይ ሶስት ዓመት ምን መሆን አለበት? የሚል መመሪያ (ሮድማፕ) የተዘጋጀ በመሆኑ፣ የሆቴል ባለቤቶች፣ ማናጀሮች፣ የፖለቲካ አመራሮች … የሆቴል ኢንዱስትሪውን በእውቀት እንዲመሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና መዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡
አዲስ አበባ 3ኛዋ የዲፕሎማቶች መቀመጫ ናት፡፡ በየጊዜው በርካታ ቱሪስቶች ለተለያየ ጉዳዮች (ለንግድ፣ ለስብሰባ፣ ለጉብኝት…) ይመጣሉ ያሉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ገብረጻድቅ፤ መዲናዋ ከየትኛውም አካባቢ በላይ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች ሊኖሯት እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡ “የሆቴሎች የደረጃ መውጣት እርስ በእርስ በሚያደርጉት ፉክክር፣ የተሻለና ጥራቱን የጠበቀ ዓለም አቀፍ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላቸዋል፡፡ ስለዚህ ሆቴሎችን እውነተኛ ሚዛን ላይ አስቀምጦ ትክክለኛ ደረጃቸውን መንገር ያስፈልጋል፡፡ አዲስ አበባን በሆቴል አገልግሎት አሰጣጥ የተሻለችና ተመራጭ በማድረግ ሆቴሎች በ2ኛው የጂዲፒ ዕቅድ በኢኮኖሚው ውስጥ የሚጫወቱትን ከፍተኛ ሚና ማስቀጠል ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ደረጃ መዳቢ ካውንስል ካፀደቀው መመዘኛ በተቃራኒ ሆቴሎች ደረጃ ከተሰጣቸው ያልተገመተና ያልተጠበቀ ውጤት ያስከትላል” በማለት ሰልጣኞች በእውቀት ላይ የተመሰረተ ትክክለኛ ምደባ እንዲሰጡ አጥብቀው አሳስበዋል አቶ ገ/ፃድቅ፡፡

Read 2584 times