Monday, 16 March 2015 09:06

የፓርቲዎቹን የምርጫ ክርክር እናዳምጥ - የሚያከራክር ነገር ባይኖራቸውም!

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(3 votes)

      ኢህአዴግ፣ መድረክና ኢዴፓ ያካሄዱት የመጀመሪያው የምርጫ ክርክር፣ ብዙም ትኩረት ሳያገኝ ማለፉ ያሳዝናል። በጥሞናና በንቃት ልንከታተለው ይገባ ነበር። በእርግጥ አዝናኝ አይደለም፤ አሰልቺ ነው። ቁምነገረኛ ሃሳቦች፣ ጠርተውና ጎልተው የወጡበትም አልነበረም። የፓርቲዎቹ ክርክር በትኩረት ብንከታተል ኖሮ፣ ትልልቅ ሃሳቦችን፣ መሳጭ ማብራሪያዎችን፣ አነቃቂ ራዕዮችን እናገኝበት ነበር ማለቴም አይደለም። የፓርቲዎቹን የሃሳብ ልዩነት ለማየትና የትኛው ፓርቲ ከየትኛው እንደሚሻል ለማመዛዘን እድል ይሰጣል ማለቴም አይደለም። በተቃራኒው፣ የአገራችን ፓርቲዎች ያን ያህልም የተራራቀ አስተሳሰብም ሆነ የተራራቀ ሃሳብ እንደሌላቸው በቀላሉ የምናይበት ጥሩ አጋጣሚ ይሆንልን ነበር። በተመሳሳይ የአስተሳሰብ ቅኝት የሚያቀርቧቸው ሃሳቦች የቱን ያህል ተመሳሳይ እንደሆኑ ማየት በቻልን ነበር። እንዲያውም፤ ተመሳሳይ ሃሳባቸውን ለመግለፅ፣ ተመሳሳይ ቃላትና ሃረጋትን ነው የሚጠቀሙት።
በኢኮኖሚ ውስጥ የመንግስት ድርሻና ቁጥጥር በማሳነስ ነፃ ገበያን ማስፋፋት ያስፈልጋል የሚለው የ“ሊበራሊዝም ወይም የካፒታሊዝም አስተሳሰብ”፤ “የኒዮሊበራሊዝም አስተሳሰብ” ተብሎም እንደሚታወቅ የጠቆሙት የክርክር መድረኩ ተሳታፊ፤ “የገበያ አክራሪነት” ሲሉ ፈርጀውታል። “ደሃውን የበለጠ ድሃ እያደረገ፣ ሃብት በተወሰኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንዲያዝ እያደረገ” ነው በማለትም አውግዘውታል። ይሄ አዲስ ውንጀላ አይደለም። ራሳቸውን ከሶሻሊዝም አባዜ ለማላቀቅ ፍላጎት የሌላቸው ሰዎች ዘወትር የሚያሰራጩት ውግዘት ነው። “ነፃ ገበያ የሃብት ልዩነትን ስለሚያሰፋ፣ መንግስት ጣልቃ ገብቶ ሃብት ያከፋፍል፤ ከዜጎች የስራ ገቢ ገሚሱን እየወሰደ ለድሆች ድጎማ ይስጥ” ለሚለው ዲስኩር ፈፅሞ እንግዳ አይደለንም። እኚሁ የክርክር ተሳታፊ ግን፣ ልክ እንደ አዲስ ግኝት፤ ዛሬ ዛሬ በኢኮኖሚ ውስጥ የመንግስት ሚና በአውንታዊነት መታየት” መጀመሩንም አብስረዋል።
እንዲያው፣ እውነታውን ለመደበቅ ነገሩን በከንቱ እያድበሰበሱ ያወሳስቡታል እንጂ፤ የካፒታሊዝም ወይም የነፃ ገበያ ስርዓት መሰረታዊ ሃሳብ ግልፅ ነው - “እያንዳንዱ ሰው በሰላምና በፍትህ እንዲኖር፤ በጥረቱ ፍሬ ላይ የባለቤትነት መብቱ ይከበር። ምርቱን ይጠቀሙበታል፤ ወይም ይገበያይበታል፤ ወይም በልግስና ለሌላ ሰው ይሰጣል፤ ውሳኔው የራሱ ነው”። በቃ ይሄው ነው፣ መሰረታዊው የነፃ ገበያ ሃሳብ። ቁልጭ ያለ ፍትሐዊ ሃሳብ ቢሆንም፤ ግን ብዙዎቻችን ልንቀበለው አንፈልግም። በተቃራኒው፤ የስራ ሰዎች በራሳቸው ጥረት ሕይወታቸውን ለማሻሻል የሚያመርቱትን ነገር፣ ልክ እንደራሳችን ንብረት ገሚሱን እየወሰድን ለሌሎች የማከፋፈል ‘ስልጣን’ እንዲኖረን እንፈልጋለን። በሌሎች ሰዎች ምርትና ንብረት ላይ አዛዥ ናዛዥ መሆን ያምረናል። እና ይህንን የቅሚያ ስርዓት፤ “ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል”፣ “ማህበራዊ ፍትህ” እያልን እንጠራዋለን።
በእርግጥ ገና ድሃ የሆነች አገር ውስጥ፣ ከሃብት ክፍፍል በፊት ሃብትን ማመንጨት እንደሚቀድም ጠቅሰዋል - የክርክሩ ተሳታፊ። ሶሻሊስቶች “ነፃ ገበያን፣ ካፒታሊዝምን፣ ሊበራሊዝምን” ለማንቋሸሽ የሚያዘወትሯቸው አገላለፆችን በመጠቀም፣ ‘ሊበራሊዝም ወይም ኒዮሊበራሊዝም የገበያ አክራሪነት ነው’ በማለት የተናገሩት እኚሁ ተሳታፊ፤ ተጨማሪ ጥላሸት ሳይቀቡ አላለፉም። ሊበራሊዝም፣ “ግለሰብን ልክ እንደ እንጉዳይ ብቻውን... የበቀለና በራሱ ምሉዕ አድርጎ የሚያስብ ነው። አንድ ግለሰብ ግን ምሉዕ ሰው የሚሆነው ... ባለበት ማህበረሰብ ውስጥ ነው” በማለት አጣጥለውታል።
ከየትኛው ተሳታፊ ነበር ይህ ትችትና አቋም የተሰነዘረው? ኦ... ይቅርታ። ተከራካሪ የፓርቲ ተወካዮች አይደሉም ይህንን የተናገሩት። የክርክር መድረኩን በገለልተኝነት ለማስተናበር የተሰየሙት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ምሁር ናቸው ይህንን አቋማቸውንና ትችታቸውን ያቀረቡት። በአሽሙር ቢጤ፣ ምሁሩን እየተቸሁ እንዳይመስላችሁ። ያልተለመደና እንግዳ የሆነ ስህተት አልፈፀሙም። ለካፒታሊዝም ወይም ለነፃ ገበያ ያለን ጥላቻኮ፣ የረዥም ዘመናት ቅርሳችን ነው። በትጋት ሃብት የሚያፈራ ሰው አይወደድም። የዚህ ጥንታዊ ባህል ዋና ጠበቃ ሆነው በፍቅር እስከ መቃብር መፅሐፍ ላይ የተገለፁት ፊታውራሪ መሸሻ፣ ለሃብታሞች የነበራቸውን ጥላቻ የምታውቁት ይመስለኛል። በጥረት ሃብት ያፈሩ ሰዎች ናቸው፣ የጥላቻው ኢላማዎች።
በዚህ ጥንታዊ ባህል ላይ፣ የሶሻሊዝም አስተሳሰብ ተጨምሮበት፣ አብዛኛው ዜጋ፣ አብዛኛው ፖለቲከኛና ምሁር የነፃ ገበያ ጠላት ቢሆን አይገርምም። በሌላ አነጋገር፣ ክርክሩን ያስተናበሩ ምሁር፣ ገለልተኛ አይደሉም ብሎ መተቸት አስቸጋሪ ነው። እንዴት በሉ።     
ስለመንግስት ጣልቃ ገብነትና ሚና፤ ስለሃብት ልዩነትና ክፍፍል፣ ከተከራካሪ ፓርቲ ተወካዮች የተሰነዘሩ ተመሳሳይ አስተያየቶችንና አቋሞችን ተመልከቱ። በእርግጥ፣ ኢህአዴግ፣ መድረክ እና ኢዴፓ ሦስት የተለያዩ አስተሳሰቦችን የሚከተሉ ፓርቲዎች እንደሆኑ ተደርጎ ነው የቀረበው - አንዱ የልማታዊ ዲሞክራሲ አስተሳሰብ፣ ሌላኛው የሶሻል ዲሞክራሲ፣ ሦስተኛው ደግሞ የሊበራል ዲሞክራሲ አስተሳሰብ። ግን፣ ብዙም አይለያዩም። ሦስቱ ፓርቲዎች የየራሳቸውን አስተሳሰብ በማሞገስና ትክክለኛነቱን በመግለፅ የተናገሩትን ሃሳብ ልጥቀስላችሁ። ሁሉም፣ “የሐብት ክፍፍል” እና “የመንግስት ጣልቃ ገብነት” እንደሚያስፈልግ ይሰብካሉ።
ተከራካሪ ቁ.1
“የአገሪቱን ሃብት በአጠቃላይ ህብረተሰቡ እኩል የሚከፋፈልበትና የሚያድግበትን የልማት አቅጣጫ የሚከተል ነው” በማለት የፓርቲያቸውን አስተሳሰብ ያወደሱት አንደኛው ተከራካሪ፣ በኢኮኖሚ ውስጥ የመንግስት ጣልቃ ገብነት ተገቢ እንደሆነ ተናግረዋል - “ከድህነታችን አኳያ በህግ በተገደበ አኳሃን የመንግስት ጣልቃ ገብነት [ማስፈለጉ] ምንም የሚያጠራጥር አይደለም” በማለት።
የየትኛው ፓርቲ ተወካይ ይሆኑ? ምናልባት፣ “እኩል የሃብት ክፍፍል” እና “በተመረጠ አኳሃን የመንግስት ጣልቃ ገብነት” የሚሉ አባባሎችን ስታዩ፣ በእርግጠኛነት የኢህአዴግ ንግግር ነው ትሉ ይሆናል። ግን አይደለም። የኢዴፓ ተወካይ ዶ/ር ጫኔ ከበደ የተናገሩት ነው።
ተከራካሪ ቁ.2
የሃብት ክፍፍል እንደሚያስፈልግ በምሳሌ ጭምር ያስረዱት ሌላኛው ተከራካሪ፣ “ሃብት ማካበት በቻለው መካከልና በቀረው ተራ ህዝብ መካከል ያለው ልዩነት ይህን ያህል ሊራራቅ አይገባም”  በማለት ሲያስረዱ፤ “ግብር ሰብስቦ የሚያስተዳድረው መንግስት ሚና ሊኖረው ይገባል” ብለዋል። በአንዳንድ አገራት የሰዎችን ኑሮ ለማመጣጠን ከዜጎች ገቢ ግማሽ ያህል በታክስ እየተቆረጠ መንግስት እንደሚወስድ እኚሁ ተከራካሪ ጠቅሰው፤ “ይህ ግን ኅብረተሰቡን የሚያሳስበው ሆኖ አልተገኘም። ምክንያቱም ጽዳት ሰርቶም ኖረ፣ የህክምና ባለሙያም ሆነ የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ኑሯቸው ተመጣጣኝ ስለሆነ... በደስታ ነው የሚኖሩት” ብለዋል።
የህክምና ዶክተርና የፅዳት ሰራተኛ ተመሳሳይ ገቢ እንዲኖራቸው ማድረግ አስደሳች ሲሆን ይታያችሁ። የአገራችን ሃኪሞች፣ ወደ ውጭ የሚጎርፉት አስደሳች ኑሮ እየሰለቻቸው መሆን አለበት። እዚህ ካሉት ሃኪሞች ይልቅ በዋሺንግተንና በአቅራቢያዋ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ሃኪሞች በቁጥር እንደሚበዙ አልሰማንም ማለት ነው?
የሆነ ሆኖ እኚህ ተከራካሪ በምሳሌነት የጠቀሷቸው አገራት አስገራሚ ናቸው፤ የእነዚያ አገራት ሰዎች ልዩ ፍጡራን ሳይሆኑ አይቀሩማ - ጥረው ግረው ካገኙት ገቢ 50% ታክስ ቢቆረጥባቸውም አያስጨንቃቸውም፤ ለምን? እኚህ ተከራካሪ ምላሽ አላቸው፤ “ለጋራ ሕልውናና ጥቅም የሚደረግ መስዋዕትነት... የሰው ፍጡር አንዱ ከሌላው እጅግ በሰፋ ሁኔታ መኖር የለበትም ብለው ነው የሚያምኑት” በማለት እኚሁ ተከራካሪ የሃብት እኩልነትንና የመንግስት ጣልቃ ገብነትን አወድሰዋል።
እኚህ ተከራካሪስ ከየትኛው ፓርቲ የመጡ ይሆን? “የጋራ ሕልውና፣ መስዋዕትነት፣ የሃብት ክፍፍል፣ በግብር ከፋይነት መደሰት፣ የመንግስት ሚና” ... እነዚህን ቃላትና ሐረጋት ስትመለከቱ፣ የየትኛው ፓርቲ አባባሎች ሊሆኑ እንደሚችሉ መገመት አያቅታችሁም። የኢህአዴግ ነዋ። አይደለም እንዴ? ይቅርታ፣ ተሳስቻለሁ። የመድረክ አመራር አባል የሆኑት ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ ከተናሩት ማብራሪያ የተወሰዱ ጥቅሶች ናቸው።
የትኛው ንግግር የየትኛው ፓርቲ እንደሆነ ለመለየት ተቸግረን ብሳሳትና ብትሳሳቱ አይገርምም። ሃሳባቸው ይመሳሰላል። ሃብት ለሁሉም በፍትሃዊነት የሚዳረስበትን መንገድ በመፍጠር እንሰራለን በማለት የቀሰቅሱ ተከራካሪ፤ ፓርቲያችን የሚከተለው አስተሳሰብ፣ “ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ያለበት ፈጣንና ተከታታይ እድገትን ያመጣል” በማለት ገልፀዋል። ለዚህም በኢኮኖሚ ውስጥ የመንግስት ጣልቃ ገብነት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ... በነገራችን ላይ፣ ይሄ የሌላ ተከራካሪ አባባል መሆኑን ልብ በሉ - የሦስተኛው ተከራካሪ አባባል ነው። እንዳይደባለቅባችሁ ሰጋሁ። አንዳች ማስጠንቀቂያ ምልክት ሳልሰጥ፣ ከሁለተኛው ተከራካሪ ወደ ሦስተኛው ተከራካሪ መሻገር አልነበረብኝም። ለማንኛውም፤ የኢህአዴግ ተወካይ አቶ አባይ ፀሐዬ የተናገሩትን ነው የጠቀስኩላችሁ።


Read 2820 times