Monday, 16 March 2015 09:08

የአራዳ ጊዮርጊስ ማህበር ካህናት የአዲስ አድማስን ዘገባ አወገዙ

Written by 
Rate this item
(7 votes)

“የአራዳ ጊዮርጊስ ደብር በገንዘብ ብክነት እና በመልካም አስተዳደር እጦት መቸገሩ ተገለጸ” በሚል ርዕስ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ የካቲት 21 ቀን 2007 ዓ.ም የወጣውን ዘገባ  “የተባለው ሁሉ ሀሰት ነው” ሲሉ የደብሩ ማህበረ ካህናት አወገዙ፡፡
ዘገባው ከሃቅ የራቀ መሆኑን ለአዲስ አድማስ የገለፁት ካህናቱ፤ በአስተዳዳሪውና በሰራተኛው መካከል ችግር አለ ተብሎ በዘገባው የተጠቀሰው ከእውነት  የራቀ ነው ብለዋል፡፡ “የደብሩ አስተዳዳሪ ሰራተኞችና ባለሙያዎችን በዛቻ ቃል ያሸማቅቃሉ የተባለውም ፈፅሞ ሃሰት ነው፤ አባታችን ይኸን አያደርጉም” ሲሉ  ተናግረዋል፡፡
“በአሁን ሰዓት ያለው አስተዳደር፣ ሰበካ ጉባኤውና የልማት ኮሚቴው በልዩ ሁኔታ ያለምንም ተፅዕኖ ሁሉም በራሱ በጎ ፍቃድ እየሰራ ነው” ብለዋል፤ ካህናቱን ወክለው የተናገሩት ሊቀ ካህናት ቄሰ ገበዝ ብርሃኑ፡፡
መምህር ወልደሰላም አለሙ በበኩላቸው፤ ደብሩ የሰላም፣ የአንድነትና የልማት ቦታ መሆኑን ጠቅሰው “በመልክአ መንክራት ኃይሉ አብርሃ የሚመራው አስተዳደር የሰላም አስተዳደር ነው” ብለዋል፡፡ በዘገባው ላይ ለግንባታ የተያዘው በጀት ከ61 ቢሊዮን ብር ወደ 80 ሚሊዮን ብር አሳማኝ ባልሆነ ምክንያት እንዲያድግ ተደርጓል የተባለው ውል ተደርጎ ሁላችንም አምነንበትና ፈርመን እድሳት የተደረገበት ነው እንጂ የደብሩ አስተዳዳሪ ብቻቸውን የወሰኑት ነገር የለም ብለዋል፡፡የደብሩ አስተዳዳሪ ለማህበረ ካህናቱ ሳያሳውቁ በራሳቸው የወሰኑት ውሳኔም የለም ሲሉም የአዲስ አድማስ ዘገባን አስተባብለዋል፡፡ “በኮንተራክተር መረጣ ወቅትም አስተዳዳሪው አማክረውን ነው ኮንትራክተሩ እንዲመረጥ የተደረገው” ብለዋል፤ መምህር ወልደ ሰላም፡፡
አስተዳዳሪው እንኳን ሰራተኛን ሊያሸማቅቁ የተጣላን አስታራቂና ሃገሪቷ ሰላም የምትሆነው ቤተክርስቲያን ሰላም ስትሆን ነው ብለው የሚያምኑ አለቃችን ናቸው ብለዋል - መምህር ወልደሰላም፡፡ በቤተ ክርስቲያኑ የገንዘብ ብክነት እንዳለ ተደርጎ የተዘገበው ሃሰት ነው ያሉት መምህሩ፤ እንኳን በገንዘብ ብክነት ሊታማ ከ40 ሚሊዮን በላይ ተቀማጭ ገንዘብ ያለው ነው ብለዋል፡፡ ይህም ለአዲስ አበባ አድባራት በሙሉ ምሳሌ እንደሆነ በመግለፅ፡፡
የማህበረ ካህናቱ ተወካዮች “አዲስ አድማስ ጋዜጣ ከቤተክርስቲያናችን ላይ እጁን ያንሳ” ሲሉም ጠይቀዋል፡፡  


Read 2496 times