Monday, 16 March 2015 09:11

አዲስ አበባ ባለ 7 ኮከብ ሆቴል ሊኖራት ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(22 votes)
  • ለሀገር መሪዎች ማረፊያ ይሆናል ተብሏል
  • ባለቤቱ ሼህ መሐመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ናቸው

    ንብረትነቱ የሼህ መሐመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ የሆነው በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ባለ 7 ኮከብ ሆቴል ግንባታ እየተገባደደ ሲሆን ከመጪው የፈረንጆች አዲስ ዓመት በፊት ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ አገልግሎት እንደሚሰጥ ታውቋል፡፡
በአዲስ አበባ አፍሪካ ህብረት ጽ/ቤት ግቢ ውስጥ እየተገነባ ያለው ያለው ባለ 7 ኮከቡ ሆቴል፤ በዓለማቀፍ ደረጃ በርካታ ሆቴሎችን በሚያስተዳድረው ዌስቲን ሆቴልና ሪዞርት ኩባንያ ይተዳደራል ተብሏል፡፡
በሚድሮክ ኩባንያ የኮንስትራክሽን ክፍል የሚገነባው ይህ ዓለማቀፍ ሆቴል መጀመሪያ ላይ  የ350 ሚሊዮን ዶላር (ወደ 7 ቢሊዮን ብር ገደማ) በጀት የተያዘለት ቢሆንም ወደ ማጠናቀቂያው ሲቃረብ ከተያዘለት በጀት የ20 በመቶ ተጨማሪ የግንባታ ወጪ እንዳስፈለገው ተገልጿል፡፡
ሆቴሉ ከሂልተን፣ ሸራተን አዲስና ራዲሰን ብሉ ሆቴሎች ቀጥሎ አራተኛው የሀገር መሪዎችንና ከፍተኛ ባለስልጣናትን የሚያስተናግድ ሆቴል ይሆናል ተብሏል፡፡
ሆቴሉን የሚያስተዳድረው “ዌስቲን ሆቴልና ሪዞርት” ዓለማቀፍ እውቅና ባለው ስታር ውድ ሆቴልና ሪዞርት በ1994 (እኤአ) የተመሰረተ ሲሆን በአሁን ወቅት በ37 ሀገሮች 192 ሆቴሎችን ያስተዳድራል፡፡ በጠቅላላው በ102 ሺህ ስኩዬር ሜትር ላይ ያረፈው ሆቴሉ፤ 27 የፕሬዚዳንቶችና 31 የሚኒስትሮች መኝታ ክፍሎችን ጨምሮ 610 የመኝታ ክፍሎች፣ 3500 ሰዎችን ማስተናገድ የሚቻል የስብሰባ አዳራሽን፣ 8 መካከለኛ ደረጃ ያላቸው የመሰብሰቢያ አዳራሾችን ማካተቱ ታውቋል፡፡ 2‚200 ሰዎችን በአንድ ጊዜ ማስተናገድ የሚያስችል የልዩ ግብዣ አዳራሽም አለው ተብሏል - ሆቴሉ፡፡
በተጨማሪም ተንደላቀቁ የመኝታ ክፍሎች፣ በፕሬዚዳንቶችና በከፍተኛ የቢዝነስ ሰዎች ምጣኔ የተዘጋጁ ባርና ሬስቶራንቶች፣ የመዋኛ ገንዳና ስፓ፣ ዘመናዊ ክለብ፣ የተለያዩ የግብዣ አዳራሾች፣ የቢዝነስ ተቋማት እና ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ ፓርክ ይኖረዋል ተብሏል፡

Read 15608 times