Monday, 16 March 2015 09:10

በሽብርተኝነት የተከሰሱት የተቃዋሚ አመራሮች ፍ/ቤት በመድፈር በእስራት ተቀጡ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

በአንድ ሳምንት ውስጥ 14 እና 16 ወራት እስራት ተፈርዶባቸዋል
   በሽብርተኝነት የተከሰሱት የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ፍ/ቤት በመድፈር ወንጀል በአንድ ሳምንት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ከትናንት በስቲያ የእስራት ቅጣት የተላለፈባቸው ሲሆን ዳኛው ቅጣቱን ሲናገሩ ለ3ኛ ጊዜ ቢያጨበጭቡም ፍ/ቤቱ “የዛሬውን አልፈዋለሁ” በማለት ሌላ ቅጣት ከማስተላለፍ ተቆጥቧል፡፡
ተከሳሾቹ በማረሚያ ቤት ላይ ያቀረቡት አቤቱታ በፍ/ቤቱ ተቀባይነት ማጣቱን ተከትሎ የካቲት 25 ቀን 2007 ዓ.ም “በጭብጨባ ችሎት ደፍራችኋል” በሚል መጋቢት 1 ቀን 2007 ዓ.ም እያንዳንዳቸው በ7 ወር እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ የተላለፈባቸው ሲሆን ተከሳሾቹ በድጋሚ በማጨብጨባቸውና “ያልተገባ ንግግር ተናግረዋል” በሚል ፍ/ቤቱ ችሎት በመድፈር ጥፋተኛ ናቸው ሲል ውሳኔ ሰጥቶ ቅጣት ለመወሰን ለትናንት በስቲያ ቀጥሮ ነበር፡፡
ከትናንት በስቲያ የዋለው ችሎትም ተከሳሾቹ ከመጀመሪያው ስህተታቸው ሳይማሩ በድጋሚ ችሎት በመድፈራቸው ተጨማሪ የ7 ወር እና 9 ወር እስር ቅጣት ወስኖባቸዋል፡፡
በጭብጨባ ፍ/ቤቱን ደፍረሃል የተባሉት የሰማያዊ ፓርቲ የብሄራዊ ም/ቤት ም/ሰብሳቢ አቶ የሽዋስ አሰፋ እና የአንድነት ፓርቲ የቀድሞ የድርጅት ጉዳይ ም/ኃላፊ አቶ ዳንኤል ሺበሺ ተጨማሪ የ7 ወር እስር ሲፈረድባቸው፣ በጭብጨባና “አሻንጉሊት ችሎት ነው” በሚል ንግግር ፍ/ቤቱን ደፍረዋል የተባሉት አቶ አብርሃ ደስታ ደግሞ በተጨማሪ የ9 ወር እስራት እንዲቀጡ ፍ/ቤቱ ወስኗል፡፡ ችሎት በመድፈር ወንጀል በጠቅላላው በአንድ ሳምንት ውስጥ አቶ የሽዋስ እና  አቶ ዳንኤል በ14 ወር እስራት እንዲሁም አቶ አብርሃ የ16 ወራት እስር ቅጣት ተጥሎባቸዋል፡፡
ተከሳሾቹ ከትናንት በስቲያ የቅጣት ውሳኔ ሲነገራቸው በድጋሚ ያጨበጨቡ ቢሆንም ፍ/ቤቱ በዚህ ሁኔታ መቀጠሉ ለእናንተም ተገቢ አይደለም” የሚል ማሳሰቢያ በመስጠት የዛሬውን አልፈነዋል ብሏል፡፡
ማክሰኞ መጋቢት 1 ቀን ተከሳሾቹ ችሎት በመድፈር የመጀመሪው የ7 ወር ቅጣት ሲጣልባቸው ፍ/ቤት አለመድፈራቸውንና በወቅቱ የተናገሩት በመማረራቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ችሎቱ እውነተኛ ችሎት ባለመሆኑም ችሎት አለመድፈራቸውን ጠቁመው ድርጊቱን የፈፀሙት ፍትህ እናገኛለን ብለው ባለማመናቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል ከትናንት በስቲያ ፍ/ቤቱ አመራሮቹ በሚገኙበት በእነ ዘላለም ወርቅ አገኘው መዝገብ ስር የተካተቱ 10 ተከሳሾችን የእምነት ክህደት ቃል ለመስማት ተሰይሞ የነበረ ቢሆንም ጠበቆች “አልተዘጋጀንም፤ አጭር ቀጠሮ ይሰጠን” በማለታቸው ለመጋቢት 10 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡
ለፓርቲ አመራሮቹ የፍ/ቤት መድፈር ወንጀል ቅጣት መነሻ የሆነው በሚገኙበት ማረሚያ ቤት ህሳስ 12 ከ 13 ቀን 2007 ዓ.ም አጥቢያ ባልታወቁ ሰዎች በተደረገ የሌሊት ፍተሻ ገንዘብን ጨምሮ የተለያዩ ንብረቶች ተወስዶብናል ብለው ላቀረቡት አቤቱታ ማረሚያ ቤቱ የሰጠውን ምላሽ ፍ/ቤቱ ከተከሳሾች አቤቱታ ጋር መርምሮ አቤቱታውን ውድቅ ማድረጉን ተከትሎ ነው፡፡   

Read 2615 times