Monday, 16 March 2015 09:18

“የመቃብር ሥቃይ የሚታወቀው ለሟቹ ብቻ ነው” የስዋሂሊ ተረት

Written by 
Rate this item
(12 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ብዙ ጋሻ ቡና መሬት፣ ይጭኑት አጋሠሥ ይለጉሙት ፈረስ ያላቸው የበለፀጉ አባት ያሉት ልጅ አባቱን እንዲህ ይላቸዋል፡፡
“አባዬ”
“ወይ”
“እንግዲህ ለአቅመ - አዳም ደርሻለሁ፡፡ እንዴት አድርገህ ነው የምትድረኝ?” ሲል ይጠይቃል፡፡
አባቱም፤
“ለመሆኑ ኃላፊነት ለመቀበል ዝግጁ ነህ ወይ?”
“አዎን፤ ዝግጁ ነኝ”
“እንግዲህ ለሁሉም ወሳኙ የቡና አዝመራችን ነው”
“እንዴት አባዬ?”
“አየህ ከአሁኗ ሰዓት ጀምረህ መሬቱን መኰትኮት አለብህ፡፡ አረሙን መንቀል አለብህ፡፡ ውሃ ማጠጣት አለብህ፡፡ ከዚያ በትዕግስት እስከአዝመራው ሰዓት መጠበቅ አለብህ”
“ከዚያስ አባዬ?”
“ከዚያ ደግሞ ትለቅማለህ?”
“ቡና ለቃሚ ሠራተኞች አሉን አይደለም እንዴ?”
“አሉን”
“ታዲያ እኔ ለምን እለቅማለሁ?”
“አየህ ኃላፊነት የበላይ ተቆጣጣሪነትን ብቻ አይደለም የሚጠይቀው፡፡ ወርደህ ሥራውን ማወቅ፣ አውቀህም ሠርተህ ማየትን ይጠይቃል፡፡”
“ከዚያስ በኋላ?”
“ከዚያማ አዝመራው የሰጠና ያልሰጠ መሆኑ ተጣርቶ ያንተም የእኔም ዕጣ - ፈንታ ይወሰናል”
“ይሄ ምን ማለት ነው አባዬ?”
“ይሄ ማለት አዝመራው የሰጠ ከሆነ አንተን ድል ያለ ድግስ ደግሼ እድርሃለሁ፡፡ የማር - ጨረቃህንም (Honey - moon) ወይም የጫጉላ - ሽርሽርህንም በየባህሩ ዳርቻ አደርግልሃለሁ፡፡
በአንፃሩ አዝመራው የሰጠ ካልሆነ ግን አንተም አታገባም፡፡ እኔም ያለችኝን ሚስት እፈታ ይሆናል!” አሉት፡፡
***
አዝመራው መስጠት አለመስጠቱ የእኛ መሠረታዊ ጥረት ውጤት ነው፡፡ ያልዘራነውን፣ ያላረምነውን፣ ያልኮተኮትነውን ማጨድ፣ ማዝመር አንችልም፡፡ ለምርጫ መዘጋጀት ማለት ነው፡፡ “ከሠርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ” ሩጫ መውጣት አለብን፡፡ በአንፃሩ ‘ገባው አልገባው አይደለም የፖለቲካ ምሥጢሩ፤ ተቀበለ አልተቀበለ ነው’ ከሚለውም የባለ ድሎች መዝሙር  መላቀቅ አለብን፡፡ ዲሞክራሲ ሂደት ነውና አሸናፊ ተሸናፊ የሚሆንበት ጊዜ እንደሚኖር አንርሳ፡፡
“ተቃዋሚዎች አንዴ በርቶ ተቃጥሎ ከመቅረት (Burn bright and burn out) የተሻለ መላ ማሰብ አለባቸው፡፡ ሁሉን አቀፍ ራዕይ ያለው ሥርዓት መፍጠርን ማሰብ አለባቸው፡፡ ሥርዓቱ ቢወድቅ የሚኖረን ፖለቲካዊ ስትራቴጂ ምን መሆን አለበት? እስከሚል ድረስ ማሰብ ያሻቸዋል” ትለናለች ኖኦሚ ክላየን፡፡
አንድ መምህር ተማሪዎቹን ሲያስተምር፤
“አንዳንዴ ትናንሽ የነገ እርምጃዎችን የግድ መቀበል ይኖርብናል፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ ‘እንደ ጐሽ መሮጥ ይኖርብናል’ ያለውንም አንርሳ” ይላል፡፡ ሁልጊዜ ሩጫ አይመረን ማለቱ ነው፡፡  
ሎሬት ፀጋዬ እንደሚለን፤ “በሁሉም ጐራ ላሉ የአፍሪካ የሕዝብ መሪዎች፣ ገዢዎችና በስሙ ለሚነሱ አማጺያን ያለኝ መልዕክት አንድ ብቻ ነው፡፡ መርኋችሁ እውነት ለዲሞክራሲ ከሆነ ‘እኔ አውቅልሃለሁን’ ትታችሁ ሕዝቡን ተከተሉ” የሚል ብቻ ነው፡፡ ሕዝብ ይሄዳል፣ ይንቀሳቀሳል፤ ግመሉንም እየነዳ ይሄዳል፡፡ ግን አንድ ቦታ ሲደርስ “አትሒድ ከእንግዲህ በኋላ ያንተ አገር አይደለም” መባል የለበትም፡፡ የአፍሪካ መሪዎች ተልዕኮ መሆን ያለበት የህዝቡን የኑሮ ጉዞ፣ ነፃነቱን፣ ክብሩን፣ መብቱን፣ ማመቻቸትና መጠበቅ ነው መሆን የለበት፤ እንጂ የራሳቸውን ወይም የአዛዦቻቸውን ፍላጐት ማሟላት አይደለም፡፡ አዛዥ ሕዝብ ነው መሆን ያለበት!” ይህን ሁሉም እያንዳንዱ የፖለቲካ ፓርቲ ማወቅ ነው የሚገባው፡፡
“ያለመስዋዕትነት ድል የለም” የሚለው የዱሮ መፈክር ዛሬም ደርዝ አለው፡፡ እጅግ ረዥም መንገድ እንሄዳለን ብሎ ለተነሳ ፓርቲ ወይም ድርጅት፤ “ጉዟችን ረዥም ትግላችን መራራ” የሚለው ከዓመታት በፊት የነበረ መፈክር ይዘቱ ለዛሬም ፋይዳ አለው ብሎ ማሰብ የአባት ነወ፡፡ በተተነኮስን ቁጥር አገር ይያዝልን ማለት ቢያንስ የዋህነት ነው፡፡ መተንኮስና መገፋት ብቻ አይደለም መስዋዕትነት፡፡
ጨርሶ ከጨዋታው መባረርስ ቢሆን ብሎ ማሰብ ያሻል፡፡ አንድ ልብ፣ አንድ አፍ፣ አንድ ማህበር ሆነው እንዲኖሩ ማሰብ ቀዳሚ ነገር ነው!
“ከደደብ ሰዎች ጋር አትከራከር፡፡ ወደነሱ ደረጃ ዝቅ ያደርጉሃል፡፡ ከዚያ በኋላ በልምዳቸው ያሸንፉሃል!” (ማርክ ትዌይን)
ተፎካካሪያችንን በቅጡ ማወቅ፣ ድልን ያለጉራ፣ ሽንፈትን በፀጋ ለመቀበል ይጠቅማል፡፡ ዞሮ ዞሮ ባለጉዳዩ ብቻ የሚያቀው ነገር ሁሌም አለ፡፡ “የመቃብር ሥቃይ የሚታወቀው ለሟቹ ብቻ ነው” (The torture of the grave is known only to the dead) የሚለው የስዋሂሊ ተረት የሚነግረን ይሄንኑ ነው!

Read 4772 times