Monday, 16 March 2015 09:52

የዱበርቲዋ ጀበና

Written by  ፍጹም ገ/እግዚአብሔር
Rate this item
(4 votes)

(ለአዲስ አድማስ 15ኛው ዓመት በዓል በተደረገ የሥነ ጽሑፍ ውድድር 2ኛ የወጣ አጭር ልቦለድ)
ዕለተ ሀሙስ፣ ጥቅምት ወር 1998 ዓ.ም፣ ከረፋዱ 5፡15 ይላል፡፡
ከደሴ 18 ኪሎ ሜትር ርቀት ሊይ ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ ሲያቀኑ ተረግጠዋት የሚያልፉት ትንሽ የገጠር ወረዳ ውስጥ ነው… ይህችው የበሬ ግንባር የምታህል የኩታበር ከተማ በህዝበ አዳም ተጨናንቃለች፡፡ ከከተማዋ እንብርት ላይ ገበያተኛውን የሚያመላልሱ በርካታ አውቶብሦች ተደርድረዋል፡፡ አሁን ግን፣ ሁልጊዜ በዕለተ ሀሙስ ከየቦታው ነቅሎ የሚመጣው ገበያተኛ ወደ የመጣበት እየተመመ ነው፡፡
አንድ የሚያምር “ሥኒከር” ጫማ በጅንስ ሱሪ ያደረገ ወጣት ወደ ደሴ ለመንቀሳቀስ ሞተሩን እያሞቀ ያለውን ተረኛ አውቶብስ ተደግፎ ሲጋራውን ያቦናል። ከወደ ትከሻው ነተብ ብሎ ብዙም የማታሳጣው የቆዳ ጃኬቱም፣ “ሀብታምነቱን” ትለፍፋለች፡፡ በፊት ለፊት ብዙ ገበያተኞች ከሚያውካኩበት አረቄ ቤት ላይ የተተከለት ዐይኖቹ ግን አሁንም አልተነቀሉም፡፡
ሰዓቱን ተመለከተ - አርፍዷል፡፡ የሚጠባበቀው ነጋዴ አሁን በሞቀ ጨዋታ ውስጥ ሆኖ አረቄውን ሲያንጫልጥ እያየ ነው… የዛገ ብረት በመሰለት ጥርሶቹ ሾልኮ፣ ከኩበት ከናፍሩ ጋር እየተላተመ በሚወጣው የሲጋራ ጭስ በአየር ላይ ክብ እየሠራ ተክዟል…
እንዴዬ! ... አይገርምም! ድንገት ግን ነቃ። እንደተነቃቃም ወዲያው፣ ወደሚንቀሳቀሰው አውቶብስ በፍጥነት አመራ፤ በዓይነ ቁራኛ የሚከተለውን ሰው አሁንም አለቀቀውም… በዚች ግርግር በበዛባት ከተማ፣ የሰው ልጅ የዕለት ጉርሱን ለማግኘት በሚራወጥበት በዚህ ቀውጢ ሰዓት፣ ወጣቱ “ባለ ጉዳይ” ከዘመኑ መንፈስ የተጋባበትን በአቋራጭ የመክበር ልክፍት ሊያሳካ አቅሉን ስቶ ሲባክን ይታያል…
ሹለክ በከፍተኛ ጥንቃቄ ላይ ነው፡፡ የደምሴን ኮቴ በቅርብ እርቀት እየተከተለ ነው… ደምሴ፣ ወደ አሮጌው አውቶብስ ገባ፡፡ ከዱበርቲዋ ጎረቤቱ ጋር እያወጋ፣ ካጠገባቸው ተቀመጠ፡፡ ሹለክ ከጎኑ ቆሞ ሲመለከተው፣ ደምሴ ወደ ዱበርቲዋ ተጠጋ። አውቶብሱም ወደ ደሴ መጓዝ ጀመረ፤ ሹለክም ሥራውን … ጀመረ፡፡ የተጋሩት ወንበር፣ ሦስቱንም የልማድ እስረኞች ያነጋግራቸው ጀምሯል- እየቆየም ያግባባቸው ይሆናል፡፡
ሹለከም አውቶብሱም ለ“ቢዝነሣቸው” እየፈጠኑ ነው… ሕይወት በሴኮንዶች ክፍልፋይ ልትመተር ተዘጋጀች… ሹለክ እጁን ከደምሴ ትከሻ ላይ አደረገ፡፡ ልቡ በትንሹ ትርትር ማለት ጀመረች። ኪሥ በማውለቅ የተካኑት ጣቶቹ ስለታቸውን አፋጩ፡፡
“… ለገጠመኝ አተካሮ ብዬ እንጅ ነው የግራውን ጥማድ በሬዬን ነጥዬ የሸጥኩት!... ሽማግሎች፣ ልጅህ ጠልፎ የህጣኗን ህግ ስላበላሸ… ሠርግ ደግሠህ ወዳጅ ዘመድ መካስ አለብህ … ካለበለዚያ ዴም እንዳትቃባ ሲለኝ!...” አለ ደምሴ ከዱበርቲዋ እየተቀበለ በጉንጩ የወጠረውን ጫት በምላሱ እያማሰለ፡፡
“ህፃኗን ደፍሮ!?” ሹለክ በድንገት ጠየቀ፣ ዝም ከምል ብሎ፡፡
“ምን ይዴፍራል! ጠልፎ ሉያገባ ብል እንጂ! ነገር ሲያጣምሙይ ያስራ ሁለት ዓመት ሴት ህጣን ሁና ነው?” አለ ደምሴ፤ የካሣ ክፍያው ነገር እያናደደው፡፡
“አይዞ! ዱአ ነው ዋናው!... ትንሽ ዴም አፍሰህ ዱአ ይደረጋል!” አለ ዱበርቲዋ፣ ለሙሽራው ድንጋይ አድባር ቡና ማፍያ የገዟትን ጀበና እየደባበሱ፡፡ “አሁንም ያን ቅቤ ሙሽራውን ድንጋይ ቀባ ቀባ አርገህ ተለማምነህ ሂድ… እኔም ማምሻውን መንደርተኛውን ሰብስቤ ቡን አፈላለሁ…” አሉ ዱበርቲዋ ጀበናውን ለደምሴ እያቀበሉ፡፡
አውቶብሱ እየከነፈ ነው … ሹለከ ግን እስከ አሁን አልተሳካለትም፡፡ ዓላማው ግቡን ሳይመታ ደምሴ መውረጃው እየደረሰ ነው፡፡ ሹለክ፣ የሰውነቱን ሙለ ክብደት ከደምሴ ትከሻ ሊይ አሳረፈ፡፡ ደምሴም ከዱበርቲዋ ጋር ወሬውን ይኮመኩማል፡፡ ሹለክ ጣቶቹን ወደ ደምሴ ደረት ኪሥ አስጠጋ፡፡ ዘወርወር ብል ተጓዡን ቃኘ፡፡ በደምሴ ልጅ አስገድዶ መድፈርና በዱበርቲዋ ገድል ዙሪያ የሚወሩት ወጐች ይበልጥ ደርተዋል… ዱበረቲዋ ስለታምራቸው ሲነገር፣ በጫት ጉንጫቸውን እንደ ጐረምሳ ጉርሻ ወጥረው፣ ዐይናቸውን ፈጠጥ አድርገው ተጓዡን ይገላምጣሉ - በኩራት፡፡ ከእርሳቸው የበለጠ ታምረኛን፣ በመቼም ጊዜ በየትም ቦታ የመነተፈውን ይዞ ሹልክ ማለት የማይሳነውን የ“ሹለክ”ን ዝና የሚናገርለት ወይም የሚናገርበት ስለላለ፣ የልማድ ቧጋቿ ዱበርቲ ቢኩራሩ አይደንቅም- ይኩራሩ …
ሹለክ አሁን ልቡ በፍጥነት እየመታ ነው። ክንዱን ከአውቶብስ ወንበር መደገፊያ ሊይ ጣል አድርጐ እጁን ወደታች ላከ፡፡ ቀጫጭን ጣቶቹ ሲጋራ ብቻ ሳይሆን የደምሴን የኪስ አዝራር መያዝ ችለዋል፡፡ ችግራቸው ኪሱን መክፈት ላይ ነው። አውቶብሱም ፍጥነቱን ሥለጨመረ፣ ኮረኮንቹ መንገድ ገበጣ እያጫወተው ነው፡፡ አውቶብሱ ወደ ላይ ጉኖ ሲፈርጥ፣ ሲጠባበቅ የነበረው ሹለክ የደምሴን የደረት ኪስ ቁልፍ ከፈተ፡፡ 3
ደምሴ ወሬውን ቀጥሏል… ሹለክ ተጓዡን ዘወርወር ብል ከቃኘ በኋላ፣ የተማሩ ጣቶቹን ወደ ወርቁ ጉድጓድ ጨመራቸው፡፡ መቀሦቹ ያልሰራበትን መክሊት አፍሰው ወጡ… ደምሴ በሬ ሸጦ ኪሱ ውስጥ ያስቀመጠው 3 ሺህ ብር ከመቅፅበት በሰው እጅ መግባቱን አላወቀም፡፡ አውቶብሱ ቦሩ ሜዳ ሉደርስ ስለሆነ፣ ረዳቱ ትኬት መቀበል ጀምሯል፡፡
ሹለክ ወደ ኪሱ ከጨመራቸው የመቶ ብር ኖቶች ጋር ትኬት እንዳለ አረጋገጠ፡፡ የደምሴ ትኬት፣ እንደ ድርጭት በድንገት ቢያስደነግጠውም መሊ አላጣለትም፤ እጥፍጥፍ አድርጐ በመስኮቱ ወደ ውጭ ወረወረው! … ልቡ ግን እንደ ነጋሪት ይደልቅ ይዟል …
“ትኬት!” አለ እረዳቱ፡፡
ሹለክ ቀልጠፍ ብሎ ሰጠ፡፡ ደምሴ ግን “እህ!” ብል ተደሰቀ እንጅ፣ እጁን አልዘረጋም… ዱበርቲዋ እንደሰጡ የደምሴ ልብ ቀጥ ያለ መሰለ፡፡ የያዘውን ጀበና ለባለቤቲቱ መልሶ ከተቀመጠበት በድንገት ቆመ፡፡ ሹለክ ምንም ነገር እንዳልተከሰተ ተረጋግቶ፣ በተሰነጠቀው መስታወት ውጭ ውጩን ያያል። ደምሴ ደረቱን በሁለት እጁ እየዳሰሰ “ኧረ ጉድ ሆንኩ!” አለ ወደ ዱበርቲዋ ዞሮ፡፡
አላመነም፡፡
ጐንበስ ብል የወንበሩን ሥር ቃኘ፡፡
“ትኬቱ ጠፋህ?” አለ ሹለክ የሚደልቀውን ልቡን እየሸነገለ፡፡
“ብሬ ሁላ ጠፋይ!... ኧረ ጉድ! እሪ … እሪ!”
አሁን ደምሴ አመረረ… ተሳፋሪው ሁላ ተደናገጠ፡፡ ዱበርቲዋ፣ “የበሬህ ብር ሁሉ!? … እሪ!” በማለት አዳነቁት፡፡ ሹፌሩ አውቶብሱን አቁሞ እረዳቱን ጠየቀ፡፡
“ጋቢህን አራግፈህ እይ?... መቀመጫህንም፡፡” በማለት ሁለም በየአፉ ይናገራል፡፡
“ወይኔ ልጆቼ! ጉድ ሆንኩ ጐበዝ!... እሪ! ውይ ውይ!”
ደምሴ ጉንጮቹን ፈርክሰው መሃል ለመሃል የሚጐርፉ እንባዎቹን ለመጥረግ፣ ፊቱን ሞፈር በተጠየፈው እጁ ሞዠረው፡፡ ሰውነቱ በላብ ተጠመቀ፡፡ ወደ ፊት ወንበሮች ተንገዳግዶ እየሄደ ለቅሦውን ያስነካው ጀመረ፡፡
የቦሩ ሜዳ ወራጆች አውቶብሱን እንዲያስቆምላቸው ረዳቱን ተማፀኑ፡፡
“ልክ ነው!... እዛ ነው የወሰዱበት …” አለ፣ ሹለክ አፉ ላይ የመጣለትን፡፡ 4 አውቶብሱ ከቅድሙ የበለጠ እየከነፈ ነው፡፡ ሹፌሩ አንድ ነገር አውቋል… መንገድ ላይ ወራጅ እንዳለ ቢረዳም፣ አውቶብሱን ለማቆም ፈቃደኛ አልሆነም፡፡
“የት ነው የሚወስደን? … ተፈትሸንም ቢሆን እንውረድ!” እያለ ተሳፋሪው ይንጫጫል፡፡ ሹፌሩ ግን ጆሮ ዳባ ልበስ ብል ወደ ፊት ሸመጠጠ፡፡
“ጐበዝ በቃ ያለንን እንርዳው!” አለ፣ ሹለክ ከኪሱ 50 ብር አውጥቶ እያንቀረፈፈ፡፡ የቀረችው 10 ብር ብቻ እንደሆነች አላጣውም… አሁን ሹፌሩን ማንም አላሰተዋለውም እንጂ፣ ሹለክን አሽሟጦታል። ዱበርቱዋም ደንግጠው ኩምሽሽ እንዳለ ነው… ምርቃናቸው ተገፏል፡፡
ሹለክ ከፊት ወንበር አካባቢ ካለ ሰዎች የተሰጠ ገንዘብ ለመቀበል ወደ ፊት ሲያመራ፣ ከሹፌሩ ጋር ዐይን ላይን ተጋጩ፡፡ ሹለክ በጣም ደነገጠ … የሹፌሩ መልከ አዲሱ አይደለም… ሹፌሩ ዘወር ብል ገላመጠው፡፡
ከሁለት ሳምንት በፊት ነው፡፡ ሹለክ መደበኛ ሥራውን ለማከናወን ወደ ባቲ ሄዷል፡፡ ሲመለስ፣ ከአንድ የአፋር ቋንቋ ተናጋሪ ጋር በአንድ ወንበር ተቀምጦ ይጨዋወታል… ኮንቦልቻ ላይ አዲስ ተሳፋሪዎችን ሊጭን አውቶብሱ ቆመ፡፡ ከሹፌሩ ጥግ ከሞተሩ ኮፈን ላይ ሻንጣቸውን የጫኑ መንገደኞች እቃ ለመግዛት ወረዱ፤ ሹፌሩም ወረደ …
“ያን ሻንጣዬን ጠብቅ! እሺ?” አለ ሹለክ የመንገድ ጓደኛውን፡፡ ወዲያው መለስ ይልና፣ “አይ! … ለካ ብሬ ሁለ ሻንጣዬ ውስጥ ነው … መኪናው እንዳይሄድብኝ … ስመጣ እሰጥሃለሁ፡፡ እቃ የምገዛበት ሃምሳ ብር ሥጠኝ …” ብል ይጠይቀዋል፡፡
“ዝርዝር የለም!... ይሄ ነው ያለው” ብል መቶ ብር አውጥቶ ሰጠው፡፡ ከእቅድ በላይ የሠራው ሹለክ መቶ ብሩን እንደያዘ ወዲያው ሹልክ አለ። አውቶብሱ መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡ ሹለክ ግን አልመጣም - አይመጣምም…
“ሹፌር!... እዚህ ሰው አለ! … እቃ ጠብቅ ብሏል” አለ አፋርኛ ተናጋሪው ጣቱን ሞተሩ ላይ ወዳለው ሻንጣ ቀስሮ፡፡
“ይሄማ እቃ የኛ ነው!” አሉ ባለቤቶቹ፡፡
“እቃ እኔ ነው ጠብቅ ብል … መቶ ብር ከሱ ወሰደ” አለ፣ አፋሩ ኪሱን እያመለከተ፡፡ ወዲያው፣ ሹለክ አጭበርብሮ እንደጠፋ ታወቀ፡፡ ታዲያ በዚህ ጊዜ የነበረው ሾፌር፣ የዛሬው አውቶብስ ሾፌር ነው… አሁን ሹለክ ያሰባሰበውን 144 ብር ለደምሴ አስረከበ፡፡ ሹፌሩ እያከነፈ ያመጣውን አውቶብስ ደሴ ሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ በር ላይ 5
ገተረውና ወረደ፡፡ ሹለክ በጣም ደነገጠ… ሁሉም ነገር አሁን ገብቶታል፡፡ ፖሊሶች አውቶብሱን ከበቡ፡፡ ሁለቱ የፊት በሩን አስከፍተው ገቡ፡፡
“ይሄ ነው!” አለ ሹፌሩ፡፡ ደምሴ ፖሊሦችን ሲያይ፣ እሪታውን ጀመረ፡፡ ሹለክ በጣም ደንግጧል፡፡ ቀዝቃዛ ልብ በጀርባው እየፈለቀ ነው፡፡
“የት ጋ ነበረ የተቀመጠው?” ብሎ ፖሊሱ ሲጠይቅ፣ ሹለክ ተሽቀዳድሞ “እዚህ ነው!” በማለት ጠቆመ፡፡ ሁለም በያፉ ተልጐመጐመ፡፡
“አሁን ሁላችሁም እየተፈተሻችሁ ትወርዳላችሁ፡፡” አለ መቶ አለቃ፡፡
ሹለክ አንዳች ነገር ሆድ ዕቃውን አንጓጓው፤ ልቡ ሊፈነዳ እንደቀረበ ፊኛ ተወጠረ፡፡ ሰውነቱም ያለቅጥ መራድ ጀመረ፡፡ ፍርሀት ሆዱ ውስጥ ገብቶ፣ እንደ ቅቤ መግፊያ ቅል መናጡን ተያያዘው፤ ማንም ሰው ግን አላስተዋለውም፡፡
“በዚህኛው እረድፍ ያላችሁ ቀጥሉ!”
በእነ ሹለክ ረድፍ ያለው ተሳፋሪ ተነሳ፡፡ በሚቀጥሉት ወንበር ላይ ያሉትም መንገደኞች እየተነሱ፣ ፍተሻው ቀጥሏል፡፡ ሹለክ መውጫ ቀዳዳ ጠፋው፡፡ ፖሊሦችም እሱን መጠርጠራቸው እና በጥብቅ መፈተሻቸው አይቀርም፡፡ ልቡ ፈንድቶ፣ ሥራውን ሊያቆም ነው … መቶ አለቃው ሁሉንም እንቅስቃሴ የሚቆጣጠር ይመስላል፡፡
“ቀልጠፍ ቀልጠፍ ብላችሁ ተነሱ እንጅ ጐበዝ!” አለ፣ ፈታሹ ፖሊስ፡፡ ከእነ ሹለክ ወንበር ፊት ያሉት መንገደኞች ተሽቀዳድመው ተነሱ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ሹለክ መሽሎኪያ አጣ፡፡ ተፋፋው እንደ ሸክላ ሰሀን ከፊቱ ሊይ ተከሰከሰ… ከጭንቀቱ የተነሳ አንዳች ነገር ሊተነፍስ፣ ‘ይሄው ብሩ እዚህ ወድቋል!’ ሉል አሰበ… መሽሎኪያ ቢሆነው፡፡
ሹለክ፣ በድንገት አንዳች መሽሎኪያ ብልጭ አለለት፡፡ የተጠቀለሉትን ኖቶች ከኪሱ ውሰጥ ከፈለጋቸው በኋላ፣ የዱበርቲዋን ዓይን ቃኘ - በርበሩን ያያሉ፡፡ ጣቶቹ፣ የሦስት ሺህ ብር ኖቶች ይዘው በድንገት ከኪሱ ወጡ … ኖቶቹን ጠቀለለና በለሆሳስ ከዱበርቲዋ ጀበና ውስጥ ከተተው … ሥራውን ለማቆም የሴኮንድ ክፍልፋይ የቀሩት የሚመስለው መለኛ ልቡ፣ አሁን በደስታ ባይቦርቅም ትንሽ ተንፈስ አለ፡፡
“በሉ ተነሱ እስኪ!” ብሎ መቶ አለቀ የነሹለክን ወንበር በትኩረት ለመቃኘት ሞከረ፡፡ ሹለክንም በጥንቃቄ መፈተሻቸውን ተያያዙት፡፡ ከኃላፊያቸው ምልክት የተሰጣቸው ፖሊሦች፣ ወደ ጣቢያው አስገቡትና ፓንቱን ሳይቀር አስወለቁት፡፡ ሹለክ ግን ከአስር ብር ውጭ አምስት ሳንቲም አልተገኘበትም፡፡
“ምነው እኔን በተለየ ሁኔታ ፈተሻችሁኝሣ” ሊል አስቦ ነበረ፡፡ በኋሊ ግን ጐመን በጤና ማለትን መርጦ ፍተሻውን እንደጨረሰ በፍጥነት ወጣ… ቀልቡ ያለው የመቶ ብር ኖቶችን ከደበቀው የዱበርቲዋ ጀበና ላይ ነው፡፡ 6 ደምሴን የሚጠባበቁት ዱበርቲ፣ ከጣቢያው አለፍ ብል ከሚገኘው ፅድ ሥር ቆመዋል፡፡ ፖሊስ ጣቢያው በር ሊይ ዱበርቲዋን ሲያጣቸው በሀዘን መሰበር የጀመረው ልቡ፣ በርቀት እስከ ጀበናቸው ሲያያቸው በደስታ መጠገግ ጀመረ፡፡ ፈገግታ እያሳያቸው ቀረብ ሲል፣ “አንተን ዴሞ ምን አርግ ብለው ነው ወደ ውስጥ የጠሩህ ልጄ?” ብለው ሳይጨርሱት - “ብር አዋጥቼና አሰባስቤ በመስጠቴ አድናቆታቸውን እየገለፁልኝ ነው!” አላቸው- ጮላው፡፡
“ዴግ ሥራ ጥሩ ነው ልጄ! ካሊህ ታገኘዋለህ!”
“አዎ! እስዎም’ኮ ጥሩ ሰው ነውሁ… እናቴን ነው የሚመስልሁ!”
“አይ ልጄ! እናትህ አሉ?”
“አለች! እንደውም እንደስዎ ባለ ውቃቢ ናት!... እቺን ጀበና ስንት ገዙት! ጀበናዋ ሲሰበር ዛሯ ተነስቶ የቤቱን ሰው ሁላ ካልፈጀሁ ብል ነበር…” በማለት አስተዛዝኖ ጠየቃቸው- በወሎ ዘዬው፡፡
“ኧረ ቀላል ነው! ዴሞ ለዚህ ተጨነቅህ ሁለት ብር ነው” አለት ወደ ዘረጋላቸው እጁ ጀበናውን እያስተላለፉ…
“ቆንጆ ጀበና ናት!... እንደው እናቴ ካልደፈርኩህ… ላንቱም የቡና መግዣ ይሆንኋል… ለእኔ ሽጡልኝ፤ ደሞም ይመርቁኛል!” በማለት 10 ብር አውጥቶ አስጨበጣቸው፤ ዱበርቲዋ ደነገጡ፡፡ 2 ብር በገዙት ጀበና 8 ብር ማትረፍ አይታመንም … ደስታቸው ከፊታቸው ላይ እንደ ፈንዲሻ ቆል ይዘገናል፡፡
“አይ ልጄ! አላህ ይሰጥሀል! እናለሞቼ ይጠብቁህ…” ብለው መርቀው ሳይጨርሱ፣ አዲስ ሀሳብ ብልጭ አለባቸው፡ ሴቷ ዛራቸው ራሄል፣ ለሙሽራው ድንጋይ መከደሚያ እንዲገዙ የታዘዙትን በመሸጣቸው እንዳትጣላቸው ሰጉ፡ “ደግሜ እገዛው የለ!” በማለት ተፅናኑና ከሹለክ ጋር ተሰነባብተው ሄዱ… ወዲያው ደግሞ ልባቸው አመነታ፡፡
ወጣቱም፣ አዛውንቷም በአንድ ጉዳይ አንድ ናቸው፤ ሁለቱም የልማድ እስረኞች ናቸው፤ ሁለቱም በአንድ ዘመን የሚነፍስ፣ ሥልጡን ሽውታ ያልነካው፣ የንፋስ ወጀብ የሚያንከላውሳቸው የመንፈስ መጢቃ ናቸው። በጋራ የቆሙለት ልማድ፣ በተቃራኒ ያቆማቸዋል… በልማድ የታሰረ የሀበሻ ሕሉና ደግሞ፣ በትንሽ የማሟሻ እሳት እንደሚፈረካከስ ረጋ ሠራሽ ምጣድ ጽናት ይጎለዋል፤ የቆመለትም የቆመበትም “መርሁ” የሚገዛው፣ ከማይሰማ ምጣዱ ተፈቅፍቆ በወጣ “እንጀራው” ነው፡፡ ለዚህ ነው፣ ሀበሻ “በእንጀራዬ አትምጣብኝ ካለ …” አመረረ ማለት ነው የሚባለው …
አዛውንቷም የልማድ እስረኛ፣ ሆድና ልማድ በቁም እየተገጫጩ ሲያሸብሯቸው ሕሊናቸው መፈረካከስ ጀመረ- እንደ ረጋ ሠራሽ ሸክላ…  
ሹለክ ግን የሠራ አካላቱ ጥርስ ብቻ ሆኗል፡፡ ጀበናው ውስጥ የደበቀውን መክሊት ለማውጣት ጀበናውን በአፉ ዘቅዝቆ ቂጡን ቢጠበጥበውም ጠቅልል ያስገባው የብር ኖት ግን በቀላሉ ሊወጣ አልፈለገም፤ ውስጥ እንደ ገባ ስለ ተዘረጋም፣ የጀበናው አንገት ሊያስወጣው አልቻለም፡፡
ደገር ሄደው ሣለ የከላላው ሼህ፣ “ዴሞ ልሙሽራው ድንጋይ ገብሪ! እምቢ ካልሽ ዋ! ራሄል ቀልድ አታውቅም። ሰነካክላ ነው የምታስቀምጥሽ!” የተባሉት በእዝነ ሕሊናቸው ታወሳቸው፡፡ ከብብታቸው የሸጐጡትን 10 ብር መዥርጠው እያወጡ፣ “ማነህ! የኔ ልጅ …” እያሉ ወደ ሹለክ ሮጡ፡፡
“እህህ! አንቀጠቀጠኝ ልጄ! ... በራሄል ቀልድ የለም! እንዴምትጣሊኝ ትከሻዬ ነገረኝ … እንካ!” ብለው 10 ብሩን በቀኝ እጃቸው አንቀርፍፈው፣ በግራ እጃቸው ጀበናቸውን ለቀም አደረጉ፡፡ ሹለክ ሰፈሩ ሲደርስ ጀበናውን ሰብሮ ብሩን ለማውጣት ቢወስንም፣ እስከ አሁንም እየታገለ ነበርና፡፡ ዱበርቲዋ ግን፣ በጣም ስለጓጓለት በቀላሉ እንደማይሰጣቸው ገምተዋል፡፡
“እንዴ!... አንድዬ ሸጠውልኝ!... ካነሥዎት ወደዛ እንሂድና ብር ልጨምርልሁ!” አላቸው ለደምሴ 50 ብር በማዋጣቱ የኪሱ ባዶነት እየታወሰው፡፡ ዱበርቲዋ ጀበናቸውን በሁለት እጃቸው ግጥም አድርገው ይዘው እንዲለቅላቸው ተማፀኑ … ሹለክ ምሊጩ እንደተነካ ጓንዴ አባረቀ፤ “የተሸጠ አይመለስም!”
የልማድ ምርኮኞቹ ሥለ ልማዳቸው ሊዋደቁ ሙግት ገጠሙ… የቃላት ሰይፍ ተማዘዙ፡፡ “ከፈለጉ ብር ልጨምርልሁ እንጂ …” በማለት ሹለክ ያሰበውን ሁሉ ተናግሮ ሳይጨርስ፣ የውቃቢያቸውን ቅጣት የፈሩት ዱበርቲ፣ ጃኬቱን ሞጭጨው ይዘው ጮሁ፡፡ ከጣቢያው በር ላይ ሆኖ ሲያያቸው የነበረው ፖሊስ፣ ጩኸቱን እንደ ሰማ አንገቱን ወደ አለቃው ቢሮ አዞረ… በነ ሹለክ አጠገብ ሢያልፍ የነበረ አንድ መንገደኛ ወጣት፣ ወደ እነሱ አቅጣጫ ራመድ ራመድ አለ- የሆድና የልማድ እስረኞችን ሙግት ሊዳኝ፡፡
“ጀበናዬን አምጣ ብያለሁ! እንካ ብርህን!” ብለው ብሩን ወደ ኪሱ ከተው ጀበናቸውን በኃይል መንጭቀው ሊቀሙ ሲታገለ፣ “ወንጀለኛው” ጀበና አስፋልቱ ጠርዝ ላይ ተከሰከሰ፡፡ ተጠቅልለው ጀበናው ሆድ ውስጥ የተቀበሩት የመቶ ብር ቅጠሎች፣ እንደተነከረ ሥጋጃ አስፋልቱ ላይ ተሰጡ… አዙሮ የማያየው የጀበናው አንገት ብቻ አልደቀቀም፡፡
“እሪ … ያላለህ!”
ዱበርቲዋ እንደ ልጥ ሚስት ሐውልት ሆነው ቀሩ፡፡ ሹለክ ለመሮጥ እግሩን ሲያነሳ መንገደኛው ወጣት ጃኬቱን ጨምድዶ አቆመው…

Read 4667 times