Monday, 16 March 2015 10:04

የአፍሪካ መሪዎችና የምርጫ ጨዋታቸው

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(1 Vote)

“የቻለ ያሸንፈኝ!”

   አሜሪካዊው ደራሲ ኤድዋርድ በቻንሪ “Brushstrokes of a Gadfly” በሚል ርዕስ በፃፈው መጽሀፉ፤ “በምርጫ ወቅት መምረጥ ካልቻልክ የሚገባህን መንግስት ታገኛለህ ይሉሀል፡፡ እውነታቸውን ነው ብለህ ስትመርጥ ደግሞ የድምጽህን ውጤት ጧ ፍርጥ ብትል እንኳ አታገኝም” ሲል የአፍሪካ ሀገራትን ምርጫ በሚገባ ገልፆታል፡፡
የቡርኪናፋሶ ህዝብ ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት አብሮ አደግ የልብ ጓደኛቸው የነበሩትን ፕሬዚዳንት  ቶማስ ሳንካራን በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ገድለው ስልጣን ከነጠቁት ብሌዝ ኮምፓወሬ ሌላ ፕሬዚዳንት አይቶ አያውቅም፡፡ እንግሊዛዊው ደራሲ ዳግላስ አዳምስ፤ “ሰዎችን መምራት የሚፈልጉ   ለመምራት ምንም ዓይነት ብቃት የሌላቸው መሆናቸው አለም ያወቀው፣ ፀሀይ የሞቀው ሀቅ ነው” እንዳለው፣ የቡርኪናፋሶ ህዝብ ብሌዝ ካምፓወሬ አገር ለመምራት የሚያስችል የሚያወላዳ ብቃት እንደሌላቸው የተገነዘቡት ገና ከወዲሁ ነበር፡
ይሁን እንጂ ሰውየውን የጓደኛቸውን ህይወት አጥፍተው ከተቆናጠጡት የመሪነት ስልጣን ላይ ለማውረድ ከምርጫ ሌላ ምንም መሳሪያ አልነበራቸውም፡፡ እናም በ1991 ዓ.ም በተካሄደው ምርጫ ተዘጋጅተው ጠበቋቸው፡፡ ይህንን የተገነዘቡት ፕሬዚዳንት ብሌዝ ኮምፓወሬም፤ የፖለቲካውን ምህዳርና የምርጫውን ሂደት ለራሳቸውና ለራሳቸውን ብቻ እንደሚመች አድርገው አበጃጁት። በሁኔታው እግር ተወርች ተቀይደው መንቀሳቀሻ ያጡት ተቃዋሚዎች፣ የፕሬዚዳንቱን አምባገነናዊ ድርጊት አውግዘው ከምርጫው ራሳቸውን አገለሉ። ፕሬዚዳንት ብሉዝ ካምፓወሬም ብቻቸውን በተወዳደሩበት ምርጫ ከዘጠና በመቶ በላይ ውጤት በማግኘት አሸናፊ ተባሉ፡፡
የቡርኪናፋሶ ህዝብ በነገሩ ቢከፋም ያሰበውን ከግብ ለማድረስ ተስፋ ሳይቆርጥ ቀጣዩን ብሔራዊ ምርጫ በጉጉት መጠባበቅ ጀመረ፡፡ ይሁን እንጂ በ1998 ዓ.ም የተካሄደው ብሔራዊ ምርጫ እንደጠበቀው  ሳይሆን ቀረ፡፡ ፕሬዚዳንት ብሌዝ ኮምፓወሬ በ1991 ዓ.ም በተካሄደው ምርጫ ወቅት ያደረጉትን ሁሉ በዚህኛው ምርጫም ላይ ደገሙት፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም የሰውየውን ድርጊት አውግዘው ከምርጫው ራሳቸውን በድጋሚ አገለሉ፡
የቡርኪናፋሶ ህዝብ በፕሬዚዳንቱ አምባገነናዊ ድርጊት ቆሽቱ ቢያርም የሀገሪቱ ህገ-መንግስት አንድ ፕሬዚዳንት ከሁለት ጊዜ በላይ እንዲወዳደር ስለማይፈቅድ፣ ሰውየውን በቀጣዩ ምርጫ አናያቸውም በሚል ራሱን አፅናንቶ ነበር፡፡ በ2005 ዓ.ም በተካሄደው ብሄራዊ ምርጫ ወቅት ግን ህዝቡ ያየውን ማመን አቃተው፡፡ ፕሬዚዳንት ብሌዝ ኮምፓወሬ፤ ህገመንግስቱ ወደሁዋላ ተመልሶ ስለማይሰራ፣ ለሶስተኛ ጊዜ የመወዳደር መብት አለኝ በሚል ራሳቸውን በዋነኛ እጩነት አቀረቡ፡፡
ተቃዋሚዎች ጉዳዩን ለሀገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በማቅረብ የፍትህ ያለህ ብለው አቤት አሉ፡፡ ትዕዛዙን ከፕሬዚዳንቱ በቀጥታ የሚቀበለው ጠቅላይ ፍርድ ቤት ግን ፕሬዚዳንት ብሌዝ ኮምፓወሬ ለሶስተኛ ጊዜ መወዳደር ይችላሉ ብሎ ፍርደ ገምድል ውሳኔውን አሳለፈ፡፡
የቡርኪናፋሶ ህዝብ ይህንን ድርጊት በዝምታ ማለፍ አልፈለገም፡፡ ውሳኔውን ተቃውሞ አደባባይ ወጣ። ፕሬዚዳንት ብሌዝ ኮምፓወሬም የተቃጣባቸውን አመፅ በሰላማዊ መንገድ ሊፈቱት አልሞከሩም፡፡ ይልቁንም የፀጥታና ደህንነት ሀይላቸውን አሰማርተው አመጹን በመጨፍለቅ ባለ ሀያል የብረት ክንድ መሆናቸውን አሳዩ፡፡ በርካታ የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅት መሪዎችንና እንደ ኖርበርት ዘንጎ የመሳሰሉ ስመጥር ጋዜጠኞችን ሳይቀር በማስገደልና ደብዛቸውን በማጥፋት፣ በተቃውሞ የተነሱባቸውን ሀይሎች አይቀጡ ቅጣት ቀጡ፡፡
በ2006 ዓ.ም ላይም “የቻለ እስኪ ያሸንፈኝ” በሚል ለምርጫ ቀረቡ፡፡ በዚህ ምርጫ ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ ድምፁን ለተቃዋሚ እጩዎች በመስጠቱ ከሀያ ዓመት በላይ የዘለቀው የፕሬዚዳንት ኮምፓወሬ አገዛዝ አለቀለት ተባለ፡፡ የምርጫ ታዛቢዎችም ይህንኑ መሰከሩ፡፡ የምርጫው ውጤት ሲገለጽ ግን ነገሩ ሁሉ ከታሰበውና ከተገመተው ውጪ የተገላቢጦሽ ሆነ፡፡ እንደ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሁሉ በፕሬዚዳንቱ በቀጥታ የሚታዘዘው የሀገሪቱ የምርጫ ቦርድ፣ ፕሬዚዳንት ብሌዝ ኮምፓወሬ እጅግ በከፍተኛ ድምጽ ማሸነፋቸውን ይፋ አደረገ፡፡
እስራኤላውያን ፖለቲከኞች፤ “ምርጫ ማን ወደ ስልጣን እንደሚወጣ እንጂ ስልጣን እንዴት ጥቅም ላይ እንደሚውል መወሰን አይችልም” የሚል ምርጥ አባባል አላቸው፡፡ ፕሬዚዳንት ብሌዝ ኮምፓወሬ ለሀያ ሰባት ዓመታት የዘለቀው አምባገነናዊ አገዛዛቸው ፍፃሜውን ያገኘው በህዝባዊ ምርጫ ሳይሆን በአጓጉል የስልጣን አጠቃቀማቸው ነው፡፡ የሀገሪቱ ህገ መንግስት በሚያዘው መሰረት ስልጣናቸውን መልቀቅ የሞት ሞት የሆነባቸው ፕሬዚዳንት ኮምፓወሬ፤ ባለፈው አመት ለአራተኛ ጊዜ መወዳደር እንዲያስችላቸው ህገመንግስቱን ለመደለዝ ሙከራ በማድረግ፣ ከፍተኛ ህዝባዊ ቁጠባና አመጽ ቀሰቀሱ፡፡ ያም ህዝባዊ አመጽ ከመንበረ ስልጣናቸው ጠራርጎ በማስወገድ፣ ለአምባገነን አገዛዛቸው ፍፃሜውን አበጀለት፡፡  
ካሜሩን ከፈረንሳይና እንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ተላቅቃ፣ በነፃ ሉአላዊ ሀገርነት ከቆመች ሀምሳ አምስት አመታትን አስቆጥራለች፡፡ ላለፉት አርባ አመታት ግን ከፕሬዚዳንት ፖል ቢያ በቀር በሌላ ፕሬዚደንት ተመርታ አታውቅም፡፡ የአንድ ፓርቲ አገዛዝ የነበረበትን ከ1975 እስከ 1991 ዓ.ም ያለውን ዘመን ትተን፣ የብዙኃን ፓርቲ ምርጫ ከተጀመረበት ከ1992 ዓ.ም ወዲህ ያለውን ጊዜ ብንቆጥር በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሳተፉበት ብሔራዊ ምርጫዎች ተካሂደዋል፡፡
በእነኝህ ብሔራዊ ምርጫዎች የካሜሩን ህዝብ ከፕሬዚደንት ፖል ቢያ ሌላ አሸናፊ ፕሬዚደንት አይቶም ሰምቶም አያውቅም፡፡ ፕሬዚዳንቱም በእነዚህ ሁሉ ምርጫዎች ከሠማኒያ ስምንት በመቶ ድምጽ በታች አግኝተው አያውቁም፡፡ “ስፊንክስ” በሚል ቅጽል ስም የሚጠሩትን የፕሬዚደንት ፖል ቢያን ነገር ከሌሎች የተለየና ምናልባትም አስገራሚ የሚያደርገው የተካሄዱትን ምርጫዎች ሁሉ እጅግ ከፍተኛ በሆነ ድምጽ ተፎካካሪዎቻቸውን በልጠው ማሸነፋቸው አይደለም፡፡ ይልቁንስ አብዛኛውን ጊዜአቸውን ከሀገራቸው ውጪ በፈረንሳይ ፓሪስ በቀን እስከ 40 ሺ ዶላር በሚከፈልበት እጅግ ቅንጡ ሆቴል ማሳለፋቸውና አንድም ቀን እንኳ ቢሆን ምረጡኝ ብለው ህዝባቸውን ቀስቅሰው አለማወቃቸው ነው፡፡
እኒህ ሰው ምርጫንና ተፎካካሪዎቻቸውን በተመለከተ ለሚቀርብላቸው ተደጋጋሚ ጥያቄ የሚሠጡት መልስ አጭርና ግልጽ ነበር፡ “እስኪ ከቻሉ ያሸንፉኝ!” የሚል፡፡
አምባገነን መሪዎች ምርጫ የሚያሸንፉባቸው በርካታ ህገወጥ ዘዬዎች አሏቸው፡፡ አንዳንዶቹ ህዝባዊ ብጥብጥ በማስነሳት ምርጫውን ራሱን በቁጥጥራቸው ስር ሲያደርጉ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ በጠራራ ፀሐይም ቢሆን የምርጫ ሳጥን ይገለብጣሉ፡፡
አንዳንዶቹ የምርጫውን ሂደት ከጅምር እስከ ፍፃሜው በመቆጣጠር ማሸነፋቸውን ሲያረጋግጡ፣ ሌሎቹ ደግሞ ኢ-ዲሞክራሲያዊ ከልካይና ገዳቢ የሆኑ የምርጫ ህግና ደንቦችን በማውጣት ተፎካካሪዎቻቸውን ከምርጫ ጨዋታው በማስወገድ ድሉን በእጃቸው ያስገባሉ፡፡
የተወሰኑት ደግሞ የፖለቲካ ምህዳሩን አለቅጥ በማጥበብ፣ተፎካካሪዎቻቸው የእግር መትከያ አንዲትም ጋት ቦታ እንዳይኖራቸው በማድረግ፣ ሁሉንም ምርጫዎች እስከ 99.6 በመቶ የሚደርስ እጅግ ከፍተኛ ውጤት በማምጣት አሸነፍን ይላሉ፡፡
ሌሎቹ ደግሞ ሁሉንም አይነት የዲሞክራሲ ተቋማት በመቆጣጠር፣ ቀጥተኛ ትዕዛዝ ተቀባይና አስፈፃሚ በማድረግ በከፍተኛ ድምጽ አሸናፊነታቸውን ያረጋግጣሉ፡፡ የቡርኪናፋሶው ፕሬዚዳንት ብሌዝ ኮምፓወሬ ለሃያ ሰባት አመታት በስልጣን ላይ የቆዩት የተካሄዱትን ምርጫዎች ሁሉ ከላይ ከተዘረዘሩት ዘዴዎች አንዱን ወይም ሁሉንም በመጠቀም ነው፡፡
ካሜሩንን ላለፉት 40 ዓመታት የመሩት ፕሬዚዳንት ፖል ቢያ ደግሞ ተፎካካሪዎቻቸውን
“እስኪ ከቻሉ ያሸንፉኝ” እያሉ የሚዝቱባቸውና የምርጫ ቅስቀሳ ለማድረግ እንኳ ላፍታም ቢሆን የማይጨንቃቸው በሌላ ሳይሆን የካሜሩን የምርጫ አስፈፃሚ ቦርድ በሌሉበት ወቅትም ቢሆን እንኳ (ለምሳሌ በ2011 ዓ.ም በተደረገው ምርጫ) የምርጫውን ሂደት ከጅምር እስከ ፍፃሜው እርሳቸውን በመወከል ሳይሆን ልክ እንደ እርሳቸው ሆኖ በከፍተኛ ድምጽ ማሸነፋቸውን አረጋግጦ ውጤቱን መጀመሪያ ለእሳቸው፣ ከዚያ በኋላ ደግሞ ለህዝቡ በይፋ ስለሚያሳውቅ ብቻ ነው፡፡
እንደ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ሁሉ ኢኳቶሪያል ጊኒም የብዙኃን ፓርቲ የፖለቲካ ስርአት ዘርግታለች። ስለዚህ የሀገሪቱ ህገመንግስት በሚያዘው መሰረት በየጊዜው ብሔራዊ ምርጫ ይደረጋል፡፡ ይሁን እንጂ በምርጫው ከ95 በመቶ በላይ ድምጽ በማግኘት የሚያሸንፉት ለአራት አስርት አመታት በስልጣን ላይ የቆዩት ፕሬዚዳንት ቴወዶሮ አቢያንግ ንጉዌማ ምባሶጐ ብቻ ናቸው፡፡ ለምሳሌ በ2002 እና በ2008 ዓ.ም የተካሄደውን ምርጫ ያሸነፉት 97 በመቶ ድምጽ በማግኘት ነበር፡፡
እኒህ ፕሬዚደንትም ስለ ምርጫና ስለ ተፎካካሪዎቻቸው ብትጠይቋቸው መልሳቸው አጭርና ግልጽ ነው፤ “እስኪ ከቻሉ ያሸንፉኝ” ይላሉ። ህዝቡም እኒህ መሪዎች ለምን እንዲህ አይነት መልስ እንደሚሠጡና እንዴት 99.6 ከመቶ ድምጽ አግኝተው እንደሚያሸንፉ “ነቄ” ብሏል፡፡  

Read 1438 times