Print this page
Saturday, 21 March 2015 10:08

‘ሐሜተኛ ያፍራል፤ ሀሰተኛ…’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(11 votes)

የሃሜት ‹ብሬኪንግ ኒውስ› ከመሆን ያድነንማ!

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
የሆነ መዝናኛ ቦታ ነው፡፡ (እኔ የምለው…ከተማዋ ሁሉ በሬስቱራንትና በምሽት ክበብ ተሞላች ማለት ነው! ልክ ነዋ…ከዛሬ፣ ነገ “የኮምፒዩተር ቺፕ ፋብሪካ…” ይከፈታል፣ “የኑክሌር ማብላያ…” ምናምን ነገር ይመረቃል እያልን ስንጠብቅ የሚከፈተው ምግብ ቤት፣ ‘ሲፕ’ ቤት፣ ‘ኩሼ’ የሚባልበት ቤት…ምናምን ነገር ሆኗል፡፡ እንግዲህ…ዋና ችግሮቻችን እነሱ ከሆኑ ይሁና! በቀደም በቲቪ ያየነው ሬስቱራንት የሚወስድ አቅም ያለው ወዳጅ እስኪደውልልን እየጠበቅን ነው፡፡)  
እናላችሁ…እዚህ መዝናኛ ቦታ ቁጭ ብለን አጠገባችን ‘የሰለጠኑ’ የሚመስሉ ሦስት ወንዶች ነበሩ፡፡ (የምር ግን…‘ስልጣኔ ምንድነው?’ በሚባለው ነገር ላይ አገር አቀፍ ኮንፍረንስ ምናምን ነገር ያስፈልገናል፡፡ (ለ‘ስንቱ ነገር’ እንሰበሰብ የለ እንዴ!) ልክ ነዋ…በፊት ‘የእርጥቦች ነገር’ የምንለው ነገር ሁሉ አሁን…‘የጨሱ’ ሰዎች የሚያደርጉት ሲሆን የሆነ ቦታ ላይ የተለወጠ ነገር አለ፡፡  እናላችሁ… ስለሆነ ጓደኛቸው ‘የመኝታ ቤት ታሪክ’ ነበር የሚያወሩት፡፡ ይሉት የነበረውን ነገር መጥቀስ…አሪፍ አይሆንም፡፡ ምን አለፋችሁ…የሆነ ‘የፖርኖ መጽሐፍ’ የሚተርኩ ነበር የሚመስሉት፡፡ የሆነ ‘ፊፍቲ ሼድስ ኦፍ ግሬይ’ ምናምን በሉት፡፡
የሚገርመው ነገር ምን መሰላችሁ… ልክ የአዳራሹ ድምጽ ማጉያ አልሠራ ብሎ ሰብሳቢው ጮክ ብሎ እንደሚያወራው… አለ አይደል…እነሱም ድምጻቸውን ጥግ ድረስ ለቀው ነበር የሚያወሩት፡፡ ምን አለፋችሁ… መዝናኛው ውስጥ የነበረውን ሰው ከመጤፍ አልቆጠሩትም፡፡
እግረ መንገዴን..እንነዴ የሬስቱራንቱና ሻይ ቤቱ ይሄን ያህል እያስጮኸ የሚያስወራን…ምን ጉድ መጥቶ ነው! ስልጣኔ እኮ የሌላኛውን ሰው መብትም ማክበር ነው፡፡ ‘ባለማንበብዎ እናመሰግናለን’ አይነት ለታሪክ የሚቀመጥ ነገር ከመለጠፍ….‘እባካችሁ ስታወሩ ድምጻችሁን ዝግ አድርጉ…’ ምናምን የሚል ነገር ቢለጥፉ ይሻላል፡፡
ሌላ ደግሞ… ሁለት  አሳላፊዎች ለመቶ ሰው በተመደቡበት ቡና ምናምን መባያ ውስጥ… “ካምቦሎጆ ኳስ አለ እንዴ!...” የሚያሰኝ ጭብጨባ አሥር ጊዜ የምናጨበጭብ ሞልተናል፡፡ ብቻ ምን አለፋችሁ… ጸጥ ያለ፣ አእምሮ ማሳረፊያ የሚባል አይነት መዝናኛ ማግኘቱ አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ሀሜት የሚሉት ነገር ምን ደረጃ እንደደረሰ የሚያሳይ አይመስላችሁም? ልክ ነዋ… በፊት አፍና ጆሮ እየገጠሙ በሹክሹክታ የሚነገረው ሁሉ በአደባባይ ሲወራ…ያውም የሰለጠኑ በሚመስሉ ሰዎች… የምር አስቸጋሪ ነው፡፡
እናላችሁ…‘በማያገባን እየገባን’ የሰውን ‘የአንሶላ ቀለም’ ካላወቅን የምንል ሰዎች ስንበዛ አሪፍ አይደለም፡፡ (እንትናዬ… ‘ቤድሺቱን’ ቡራቡሬ አደረግሽው የሚባለው እውነት ነው እንዴ! እንኳንም አደረግሽው፡፡ ልክ ነዋ…ከላይ እስከ ታች ነገረ ሥራችን ሁሉ ‘ቡራቡሬ’ በሆነበት ምን በወጣሽ አንድ ቀለም ብቻ!)
ስሙኝማ… ‘አማሪካኖቹ’…በተለይ የታዋቂ ሰዎችን የጓዳ ኑሮ ማውራት… አለ አይደል…የለመዱት ብቻ ሳይሆን…የ‘ቢዙ’ ጉዳይ ነው፡፡ (‘የሌሎችን መቅዳት’ ለመደብንና…እኛም አሁን፣ አሁን እንደዛ አይነት ነገር እየለመደብን ነው፡፡ ስሙኝማ…ታዋቂ ሰዎቻችን፣ መቼም ስንት ነገር ሹክ ሲባል እንሰማ መሰላችሁ! ነገ ተነገ ወዲያ ‘ኢ.ቲ’… ‘ዘ ኢንሳይደር’ ምናምን የተጀመረ ዕለት… አቤት ያኔ!…)
እናማ…የእኛ ችግር’ኮ፣ ምናምኒት፣ ‘ቤሳ ቤስቲኒ’ የሌለው ሰው የግል ህይወት ሁሉ… አለ አይደል…‘ብሬኪንግ ኒውስ’ ምናምን ነገር ሲሆን ቀሺም ነው። ቢለብሱም ባይለብሱም፣ ቢታዩም ቢደበቁም፣ ቢዘፍኑም ቢያለቅሱም፣ ቢወዱም ቢጠሉም…ምን አለፋችሁ…ምንም ነገር ቢሆኑ ‘ከሀሜት መትረፍ’ አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ይሄ ‘ጨዋነት’ ምናምን የሚባለው ነገር ሁሉ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት አይነት ነገር ሆኖ ቀረ ማለት ነው! የምር ግን…ከዚህ ቀደም እንዳወራነው ዓይናፋርነት …‘የጨዋነት’ መገለጫ መሆኑ ቀርቷል፡፡ እንደውም የአእምሮ ችግር አይነት ነገር ሊሆን ምንም አልቀረው።
እናላችሁ…‘ጨዋ አንገቷን የደፋች፣ ቀና ብላ ሰው የማታይ…’ ምናምን የሚለው መለኪያ ፊልም ላይ እንኳን እየቀረ ነው፡፡ (ከአእምሮ ጤንነት፣ ወይም ከስሜት መዛባት ከመሳሰሉ ነገሮች ጋር የሚመጣ፣ የባለሙያ ክትትል የሚይስፈልገው ዓይነአፋርነት’ የሚመስሉ ነገሮች እንዳሉ ሳንረሳ ማለት ነው፡፡)
እኔ የምለው… ነገርዬው ይብራራልና!” ልክ ነዋ…‘ዓይናፋር’ ስትገጥም የምንወስደው እርምጃ ግራ እንዳይገባን ነገሩን ‘አድምቶ የሚነግረን’ ያስፈልገናል። … “ጉዞ ወደ ሀኪም ቤት ነው ወይስ ‘የክፉ ቀን’ ኮንዶሚኒየም ወዳለው ጓደኛ!” ብሎ ለመወሰን ያስችላላ! እንትና… “ኮንዶሚየም ለኢመርጀንሲ እያገለገለ ነው…” ያልከኝ ለካስ እውነት ኖሯል!)
ኸረ መላ ምቱ ዘመድ ወዳጆቼ
ዓይናፋር ሆኛለሁ ዓይናፋር ወድጄ፣
የሚል ዘፈን ነበር…ያኔ ዓይናፋርነት ‘እሴት’ ምናምን ነገር በነበረበት ዘመን፡፡
እኔ የምለው…ትንሽ ወደ ቀልቡ የተመለሰ ይመስል የነበረው መብራት ደግሞ ጀመረው እንዴ! ምን ይደረግ… “አራት ቀን የጠፋው መብራት በአምስተኛው ቀን ሲመጣ ‘ኢሮ!’ ተብሎ የሚጨበጨብበት ዘመን ሊያልፍ ይሆን!” ብሎ ለመመኘት ጊዜ ሳይሰጠን ይሄን ሰሞን ሳናስበው…‘ድርግም’ ማለት ጀምሯል፡፡
ሀሳብ አለን…“ደግሞ፣ ደግሞ ጀመረኝ…” የሚለው ዘፈን ለኮረንቲዎችና እንደ ኮረንቲዎች ‘ደግሞ ለሚጀምራቸው’ እንዲሆን ግጥሙ ተቀይሮ “ኢሮ!” ከምንለው ጩኸታችንና ጭብጨባችን ጋር ‘ሪሚክስ’ ይደረግልንማ! ማስተካካያ… “ኢሮ!” ከሚለው ድምጽ ቀጥሎ በሹክሹክታ “ድንቄም!” የሚል ድምጽ በሹክሹከታ ይግባልን፡፡ ዘንድሮ ልጄ… ‘ዋና፣ ዋና’ ጉዳያችንን በሹክሹክታ ነዋ የምናወራው!)
በበፊት ጊዜ እናቶቻችንና እህቶቻችን በ‘ቡና ወሬ’ ምናምን በሚባለው ነገር ይታሙ ነበር፡፡ ዘንድሮ እሷ የለ፣ እሱ የለ…ሁላችንም ‘አንድ ሳጥን’ ውስጥ ሆነናል፡፡ የምር…ቡና ላይ ከሚወራው ሀሜት የማኪያቶውና ድራፍቱ ባይብስ ነው! ደግሞላችሁ… እንደሚነገረን ከሆነ ከዚሀ በፊት ነደልነው..የእንትናን ሚስት እኮ እንትን አልኳት እየተባለ የሚፎከርበት ዘመን ነው፡፡
‘የእንትናን ሚስት እንትን ማለት’ ለምስጢረኛ ጓደኛ የሚነግሩት ብቻ ሳይሆን በአደባባይ የሚፎክሩበት ሲሆን…ሀዲዱ የሆነ ቦታ ላይ አቅጣጫውን ስቷል ማለት ነው፡፡
እና እንትና… ‘ዋይፎቻችሁን’ ጠብቁ፣ ኋላ እኛ የለንበትም፡፡ የሚያሳስቱ ነገሮች በበዙበት ዘመን…“ምነው የማምንህ ወዳጄ አልነበርክም ወይ!” ብሎ…ዳኛ ፊት አቅርቡኝ አይነት አቤቱታ አይሠራም፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…የ‘ዋይፎችን’ ነገር ካነሳን አይቀር…ይቺን በሁለት ጓደኛሞች መካከል የተደረገች ልውውጥ ስሙኝማ…
“ለሚስቴ ቃል ልገባላት እፈልጋለሁ፡፡”
“ምን አይነት ቃል?”
“በሆነ ጊዜ ውስጥ ለልደቷ አርባ ሺህ ብር ልሰጣት ቃል መግባት አለብኝ፡፡“
“ታዲያ ምንድው ችግሩ?”
“አርባ ሺህ ብር ልሰጣት አልፈለግማ!”
“ለእሱ መፍቴውን ልንገርህ…”
“እባክህ ንገረኝ…”
“ልክ ሠላሳ አምስት ዓመት ሲሞላሽ አርባ ሺህ ብሩን እሰጥሻለሁ በላት፡፡ እሷ ሠላሳ አምስት ዓመት ሳይሞላት ሁለታችሁም ታረጃላችሁ፡፡”
አሪፍ አይደል!
እናላችሁ…አባቶቻችን ‘ሐሜተኛ ያፍራል፡ ሀሰተኛ ይረታል’ ይሏት የነበረችው አባባል ከተማችን ውስጥ የትራፊክ መብራቶች ባሉባቸውና በሌሉባቸው ስፍራዎች ሁሉ በትልቁ ተጽፋ ትለጠፍልንማ!
የሀሜት ‘ብሬኪንግ ኒውስ’ ከመሆን ያድነንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3323 times