Saturday, 21 January 2012 10:12

በችግር የተተበተቡት ተከላካይ ጠበቆች

Written by  ሰላም ገረመ
Rate this item
(0 votes)

ገና በልጅነታቸው ጠበቃ መሆን ይፈልጉ እንደነበር የሚናገሩት አቶ ሳሙኤል አባተ ተሰማ፤ በአሁኑ ሰዓት በተከላካይ ጠበቃነት እየሰሩ እንደሚገኙ ይናገራሉ፡፡ ከእሳቸው ጋር አብረው የተማሩ ጓደኞቻቸው የግል የጥብቅና ስራ ላይ በመሰማራት ከፍተኛ ገቢ እንደሚያገኙ የገለፁት አቶ ሳሙኤል፤ ደሞዛቸው እርካታን የማይሰጥ ቢሆንም አቅም ለሌላቸውና የህግ ግንዛቤ ለሌላቸው ተከሳሾች ጥብቅና መቆማቸው ደስታ እንደሚሰጣቸው ይናገራሉ፡፡ ችግሩ ግን የሥራ ጫና ስለሚበዛባቸው የሚያገለግሏቸውን ታራሚዎች እንደልብ አለማግኘታቸው መሆኑን በመጠቆም ወደፊት እንደሚሻሻል እምነታቸውን ገልፀዋል፡፡ በአዲስ ከተማ ቂርቆስ ክ/ከተማ የሚኖሩትና በአናጢነት ሙያ የሚተዳደሩት ግለሰብ የሦስት ልጆች አባት ናቸው፡፡

ለ10 ዓመት የቀን ስራ እየሰሩ ቤተሰባቸውን ሲያስተዳድሩ የቆዩት ግለሰቡ፤ በአናጢነት መስራት ከጀመሩ ጥቂት ዓመታት ቢሆናቸው ነው፡፡ ባለፈው ዓመት በህዳር ወር ላይ በአንድ ህንፃ ላይ የተለመደ ስራቸውን ሲያከናውኑ ሲሰሩበት የነበረው መዶሻ ከእጃቸው ወድቆ ከሥራቸው የነበረው የስራ ባልደረባቸውን አናት በመምታት አደጋ ያደርሳል፡፡ ባልደረባቸው በአደጋው ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት ሲሆን ጭንቅላቱ ውስጥ ደም በመፍሰሱና የጭንቅላቱ አጥንት በመሰበሩ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተኝቶ እንዲታከም ይደረጋል፡፡ ጉዳቱን አድርሰዋል ተብለው የተጠረጠሩት አናጢ፤ ተይዘው ጉዳዩን ፖሊስ ካጣራ በኋላ ወደ ፍርድ ቤት ይልኳቸዋል፡፡ ሆን ብሎ ሰውን ለመግደል በማሰብ ከፍተኛ የመግደል ሙከራ በማድረስ በሚል የተከሰሱት እኚህ ግለሰብ፤ ራሳቸው ህጉን ተንተርሰው ለመከራከር በቂ ትምህርት የላቸውም፤ ጠበቃ ለማቆም ደግሞ ገንዘብ የላቸውም፡፡

 

ስለዚህ በዳኞት ፊት ቀርበው አቅም እንደሌላቸው ከተረጋገጠ በኋላ ከመንግስት ተከላካይ ጠበቃ እንዲቆምላቸው ታዘዘ፡፡ ሆኖም እስካሁን ከጠበቃቸው ጋር ለመገናኘት አልቻሉም፡፡ ስለዚህም የፍርድ ሂደቱ እንደተራዘመባቸው ምንጮች ይናገራሉ፡፡

የተከላካይ ጠበቆች ጊዜያዊ ሃላፊ የሆኑት አቶ አብርሃም ታከለ ጉዳዩ አሳሳቢ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በፌደራል ሲቪል ሠርቪስ ለመቅጠር የተፈቀደላቸው  21 ተከላካይ ጠበቆችን  እንደሆነ የሚናገሩት ሃላፊው፤ ሆኖም እስከ 2001 ዓ.ም ድረስ አስር የማይሞሉ ጠበቆች እንደተቀጠሩ ያወሳሉ፡፡ በልደታ ከፍተኛ ፍ/ቤት አራት ተከላካይ ጠበቆች ብቻ ያሉ ቢሆንም ፍ/ቤቱ በአንድ ወር ውስጥ የ564 ሰዎችን የክስ ጉዳይ  ተረክቧል፡፡ ይሄ ደግሞ አንድ ጠበቃ ከ68-75 ለሚደርስ ተከሳሽ ወይም የክስ ጉዳእ እንደ ማለት ነው፡፡

በዚህ የሥራ ጫና ምክንያትም ጠበቆቹ ከታራሚዎች ጋር ለመገናኘት እንዳልቻሉ  ምንጮች ይናገራሉ፡፡ ማንኛውም የጥብቅና ስራ የሚሠሩ ሰዎች የሚያሟሉትን መስፈርት በማሟላት ከጀማሪ ተከላካይ ጠበቃ እስከ ደረጃ 4 ተከላካይ ጠበቃ ድረስ እንደሚቀጠሩ የተናገሩት አቶ አብርሃም፤ ቁጥራቸው ግን አነስተኛ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ ተከላካይ ጠበቆቹ ከሽብርተኝነት እስከ ስርቆት ድረስ በወንጀል ለተጠረጠሩ አቅም የሌላቸው ተከሳሾች ጥብቅና ይቆማሉ፡፡

ባለፈው ህዳር ወር ብቻ ፌደራል በሚያስተዳድራቸው ፍ/ቤቶች ስር ያሉ 13 ተከላካይ ጠበቆች 1026 ጉዳዮችን ማየታቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ አብዛኛዎቹ ጠበቃ የማቆም አቅም የሌላቸው ተከሳሾች የሚገኙት በቃሊቲ፣ በሸዋ ሮቢት፣ በዝዋይ እና በክልል ማረሚያ ቤቶች ሲሆን ተከላካይ ጠበቆች ከእነዚህ ተከሳሾች ጋር ለመገናኘት የትራንስፖርት ችግር እንዳለባቸው ምንጮች ይናገራሉ፡፡ በሳምንት ሦስት ቀን ያውም ግማሽ ቀን ከከፍተኛ ፍ/ቤት በሚሰጣቸው መኪና ሄደው ነው ታራሚዎቹን የሚያነጋግሩት፡፡

አንድ ታራሚ የክሱ ቻርጅ ከደረሰው ጀምሮ ቢያንስ አራት ጊዜ ተከላካይ ጠበቃውን ማግኘት እንደሚገባው መመሪያው ቢገልጽም እስካሁን ግን ከሁለት ጊዜ በላይ ደንበኛውን ያገኘ ተከላካይ ጠበቃ የለም - በመኪና እጦት ምክንያት፡፡

ሌላም የሚጠቀስ ችግር አለ፡፡ ተከላካይ ጠበቆች እንደ አቃቤ ህግ በቂ ደሞዝና አበል፤ እንዲሁም የቤት አበልና ሌሎች ጥቅማጥቅሞች እንደሌላቸው ምንጮች ይገልፃሉ፡፡ አቃቤ ህጐች ተሿሚዎች ስለሆኑ ጥቅማጥቅም ያገኛሉ የሚሉት ምንጮች፤ ተከላካይ ጠበቆች የሥራ ውጥረት ቢኖራቸውም  የተከላካይ ጠበቆች መነሻ ደሞዝ 1ሺ 968 ብር ሲሆን ጣራው 2ሺ 570 ብር ነው፡፡

በአንፃሩ አቃቤ ህግ 3ሺ ብር ደሞዝ 1500 ብር ለቤት ኪራይና 500 ብር ለትራንስፖርት እንደሚሰጣቸው የሚናገሩት ምንጮች፤ ተከላካይ ጠበቆች የትራንስፖርት ችግር እንዳለባቸውና ለአንዳንድ ወጪዎች ከኪሳቸው ለማውጣት እንደሚገደዱ ይገልፃሉ፡፡  በዚህም የተነሳ ሥራቸውን በመልቀቅ ፈቃድ አውጥተው የግል ጥብቅና ሥራ ላይ ይሰማራሉ፡፡ የባለሙያዎቹ ቁጥር መቀነስ እየጨመረ ከመጣው የወንጀል ብዛት አንፃር  የፍትህ መጓተቱን እያባባሰው እንደመጣ የህግ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

በታህሳስ ወር 2004 ዓ.ም የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በሰው መግደል ወንጀል 72 ተከሳሾችን፣ በሰው መግደል ሙከራ 134 ተከሳሾችን፣ በከባድ ውንብድና ደግሞ 160 ተከሳሾችን ተቀብሏል፡፡ በተለይ ደግሞ በመገናኛ አውታሮች ላይ ጉዳት በማድረስ 39 ተከሳሾችን፣ በሽብርተኝነት 160 ተከሳሾችን ጉዳይ እየተከታተለ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡ በአሁኑ ጊዜ በተከላካይ ጠበቃነት ተመድበው የሚሰሩት ባለሙያዎች ቁጥር 12 ሲሆን  ቦሌ ምድብ 2፣ በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት 5፣ በጠቅላይ ፍ/ቤት 2፣ ድሬዳዋ 1፣ የቃሊቲ ምድብ (በምልልስ) 1 ተከላካይ ጠበቆች እንዳሉ ተገልጿል፡፡

 

 

Read 2855 times Last modified on Saturday, 21 January 2012 10:17