Saturday, 21 March 2015 10:49

የአሜሪካው ዕጩ ፕሬዚዳንትና ሆሊፊልድ ቦክስ ይጋጠማሉ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

ግጥሚያው የምር አይደለም ተብሏል
  የቀድሞው የማሳቹሴትስ ገዢና የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዕጩ ተወዳዳሪ ሚት ሩምኒ  ከቀድሞው የከባድ ሚዛን ቦክስ የአራት ጊዜ የአለም ሻምፒዮን ኢቫንደር ሆሊፊልድ ጋር ቦክስ ሊጋጠሙ ነው ሲል ስካይ ኒውስ ዘገበ፡፡
በመጪው ግንቦት 15 ሶልት ሌክ ሲቲ በተባለችው የአሜሪካ ከተማ የሚከፈት አንድ ኤግዚቢሽን አካል እንደሚሆን የተነገረለት ይህ የምር ያልሆነ የቦክስ ግጥሚያ፣ አላማው ለድሃ አገራት ዜጎች የአይን ቀዶ ህክምና አገልግሎት ለሚሰጠው ቻሪቲ ቪዥን የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ገቢ ማሰባሰብ ነው ተብሏል፡፡
በዚህ ውድድር ላይ የዓለም ሻምፒዮኑን ቡጢኛ ለመግጠም ቆርጠው እንደተነሱ የገለጹት የ68 አመቱ ፖለቲከኛ ሚት ሩምኒ፣ ፍልሚያው በጣም በአጭር ጊዜ ውስጥ መጠናቀቅ አለበት፣ ያለዚያ አፈር ድሜ መግባቴ አይቀሬ ነው ሲሉ ስጋታቸውን አበክረው ገልጸዋል፡፡
ከ18 አመታት በፊት ከታዋቂው ቦክሰኛ ማይክ ታይሰን ጋር ባደረገው ግጥሚያ አንድ ጆሮውን በከፊል ያጣው የ52 አመቱ ኢቫንደር ሆሊፊልድ፣ ከ3 አመታት በፊት ከባራክ ኦባማ ጋር የፖለቲካ ፍልሚያ አካሂደው ከተረቱት ሚት ሩምኒ ጋር የሚያደርገው ግጥሚያ ከወዲሁ በጉጉት እየተጠበቀ እንደሆነ ተነግሯል፡፡

Read 3912 times