Saturday, 21 March 2015 11:04

“...አላስፈላጊ የሆኑ ሪፈራል ኬዞች ቀንሰዋል...”

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

ባለፈው እትም WATCH  የተሰኘውን ፕሮጀክት ማብቃት ምክንያት በማድረግ ስለፕሮጀክቱ አንዳንድ ሀሳቦችን ማንሳታችን ይታወሳል፡፡ በኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር የዋች ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ቢኒያም ጌታቸው ለዚህም እትም እንግዳ ሲሆኑ በጅማ ዞን ተዘዋውረን ካየናቸው ጤና ጣብያዎች ያገኘናቸው የህክምና ባለሙያዎችም ሀሳባቸውን ያጋሩናል፡፡
ለማስታወስ ያህል፡-  
WATCH  ምህጻረ ቃል ሲሆን በእንግሊዝኛው (women and their children health) የእናቶችና የልጆቻቸው ጤንነት ላይ ያተኮረ ፕሮጀክት ነው፡፡ ፕሮጀክቱ በካናዳ መንግስት ድጋፍ የሚደረግለት ነው፡፡ ፕላን ካናዳ እና የካናዳ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ጋር በመሆን ገንዘቡን ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት ኢትዮጵያ ውስጥ ፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር በጋራ ፕሮጀክቱን ሲተገብሩ ቆይተዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በ2015 ማርች ላይ የሚጠናቀቅ ሲሆን በሶስት ክልሎች ማለትም በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች ክልል በሲዳማ ዞን ሠበዲኖ፣ ጎርቼ እና ቦና ዙሪያ የሚባሉ ወረዳዎች ላይ በኦሮሚያ ክልል በጅማ ዞን ቀርሳ ወረዳ እና ጢሮ አፈታ ወረዳዎች ላይ እና በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን በመቂት፣ ላስታ እና ቡግና ወረዳ     ላይ ነው፡፡
ስራው በዋናነት የእናቶችን እና የሕጻናትን ጤና መንከባከብ ነው፡፡ በተደረገው የዳሰሳ ጥናት መሰረትም Basic emergency obstetric and new born health care   ወይም  መሰረታዊ የሆነ የድንገተኛ፣ የወሊድና የጨቅላ ሕጻናቶች ጤና እንክብካቤ ስልጠናዎችን ለጤና     ባለሙያዎች በመስጠት ስራውን የጀመረ ሲሆን በአጠቃላይ በሁሉም ወረዳዎች በ 48 ጤና ጣቢያዎች ውስጥ የሚሰሩ ወደ 167/ የሚሆኑ ባለሙያዎች ስልጠናውን እንዲያገኙ ሆኖአል፡፡
ባለፈው እትም ከፕሮጀክቱ ኮኦርዲኔተር አቶ ቢኒያም ጌታቸው ጋር የተነጋገርነው ከላይ እስካነበባችሁት ድረስ ያለውን መረጃ ነው፡፡ ከስልጠናው በሁዋላስ ክትትሉ ምን ይመስላል ለሚለው እና ሌሎች ነጥቦችን በተመለከተ ታነቡ ዘንድ እነሆ፡፡
---////---
ጥ/ ከስልጠናው በሁዋላ የጤና ባለሙያዎቹ ወደ ስራቸው ሲመለሱ ምን ክትትል ተደርጎአል?
መ/    ከስልጠናው በሁዋላ ተመድበው በሚሰሩባቸው ቦታዎች ሁሉ በተወሰነ ጊዜ በመዙዋዙዋር ድጋፋዊ ክትትል ተደርጎላቸዋል፡፡ በተለይም ከአርባ ስምንቱ ጤና ጣያዎች አርባ አራቱ ተገቢውን ክትትል ያደረግንላቸው ሲሆን 4ቱ ግን የመንገድ ችግር     ስለነበረባቸው መድረስ አልተቻለም፡፡ ድጋፋዊ ክትትሉም በየሶስት ወሩ ሲደረግ የነበረ ሲሆን በዋናነት የሚመራውም በጽንስና ማህጸን ሐኪሞች አማካኝነት ነው፡፡ በድጋፋዊ ክትትሉም ወቅት የተለያዩ ለማሰልጠኛነት የሚረዱ ሞዴሎችን ይዘን በመጉዋዝ ባለሙያዎቹ የሰለጠኑትን ክህሎት እና ችሎታ ይዘው እንዲቆዩና እናቶችንና ሕጻናቱን እንዲረዱ ለማስቻል የሚደረግ ክትትል ነበር፡፡ ይህ ከትትልም ለአምስት ጊዜ ተካሂዶአል፡፡
ጥ/     የተቀናጀን ስራ ለመስራት እንዲያስችል የተጠቀማችሁት ዘዴ ምንድነው?
መ/    ፕሮጀክቱ ያተኮረው በጤና ባለሙያዎቹ ላይ ብቻ ሳይሆን አመራሩም ጥሩ አመለካከት እንዲኖረው ስለሚያስፈልግ የጤና አመራሮችን በየአመቱ እየተሰበሰቡ ለሶስት ጊዜ ያህል ለጤና ባለሙያው ምቹ የሆነ የስራ አካባቢ እንዲፈጥሩ፣ እየተሰበሰቡ እንዲወያዩ፣ እቅድ እንዲያወጡ፣ በቀጣይ ስብሰባም ምን ሰርተናል፣ ምን ችግር ነበር የሚለውን አንዱ ከአንዱ ልምድ በመቅሰም እና በመወያየት የመንግስት የትኩረት አቅጣጫም በመሆኑ     ሁሉም ተረባርበው ለውጥ እንዲያመጡ የሚያስችላቸውን መድረክ ፈጥረናል፡፡
ጥ/ ለሪፈራል ታካሚዎች ምን ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮአል?   
ወላዶችን ሪፈር የሚያደርጉባቸው ሆስፒታሎች ውስጥ የሚገኙ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞችን እንደ ተጠሪ ሰው focal person  በማስቀመጥ ጤና ባለሙያው ከጤና ጣቢያው ወደ ሆስፒታል ሊልክ ሲል ማታም ይሁን ቀን ደውለው በመነጋገር ታካሚ እንዳላቸው፣ በምን መልክ መላክ እንዳለባቸው፣ ቢልኩስ ለመቀበል ዝግጁነት አለ ወይ የሚለውን ከfocal person ጋር በመነጋገር እና ቀጠሮ እንዲያዝላቸው በማድረግ እነዚያ ባለሙያዎች ታካሚዎቹን እንዲረዱ የሚያስችል አሰራር ተዘርግቶ በተቀናጀ መልክ ሲካሄድ ቆይቶአል፡፡ focal person  የሆኑት የጽንስና ማህጸን ሐኪሞቹም በፈቃደኝነት ጥራቱን የጠበቀ ስራ ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡
ጥ/     ፕሮጀክቱ ቆይታውን ወደማጠናቀቁ ሲሆን በሂደቱ ምን ለውጥ ታይቶአል?
ከስልጠና በሁዋላ ባለሙያዎቹ ለስራ በተሰማሩባቸው ቦታዎች ሁሉ ድጋፋዊ ክትትል ባደረግንበት ወቅት በዚያውም አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን በመሰብሰብ ላይ ነበርን፡፡ በዚህም ወቅት ያየናቸው ለውጦች አሉ፡፡ ለምሳሌም ከዚህ በፊት የማይጠቀሙዋቸውን     አገልግሎቶች መጠቀም፣ አላስፈላጊ የሆኑ ሪፈራል ኬዞች ቀንሰዋል፣ ሪፈር የሚያደርጉት ታካሚ ቢኖርም ደረጃውን የጠበቀ ጥሩ የሆነ አላላክ እንደሚልኩ አረጋግጠናል፡፡ ይህ ፕሮጀክት ከሚሰራባቸው እና ከሌሎች ወረዳዎች ጤና ጣቢያዎች የሚላኩ ሪፈራሎች ጥራትና ደረጃ እንደሚለዩም አረጋግጠናል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ፕሮጀክቱ በሚሰራባቸው ቦታዎች ያሉ ጤና ጣቢያዎች ውስጥ ከሚሰሩት የጤና ባለሙያዎች የተወሰኑቱ በስልጠና እና በድጋፋዊ ክትትሉ ምክንያት እውቀታቸው በመጨመሩ ነው፡፡ ከዚህም     በላይ ይህ ፕሮጀክት በሚሰራባቸው ወረዳዎች ጤና ጣብያዎች የወላዶች ቁጥር የጨመረ ለመሆኑ በቁጥር የተደገፈ መረጃ አለን፡፡ ለምሳሌም በደቡብ የሲዳማ ዞን ሸበዲኖ ወረዳ     በሶስት ወር ውስት አምስት መቶ እናቶችን ሲያዋልድ የነበረ ጤና ጣቢያ አሁን ግን እስከ አንድ ሺህ ሁለት መቶ ድረስ በሶስት ወር ውስጥ እያዋለደ ይገኛል፡
ጥ/ በአጠቃላይ ከፕሮጀክቱ ምን ተገኘ?
መ/    ከአሁን በፊት የእውቀት ክፍተት ነበር ማለት ቻላል፡፡ ባለሙያዎች ወደ ስልጠናው ሲመጡ ብዙዎቹ እንደ አዲስ ተማሪ ግራ የመጋባት ሁኔታ ይታይባቸው ነበር፡፡ አሁን     ግን በቂ ክህሎት ስላላቸው እንደልባቸው በተገቢው መንገድ አገልግሎቱን በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡
ሌላው ደግሞ አንዳንድ ጊዜ የህክምና መገልገያ መሳሪያው በጤና ጣቢያው ውስጥ እያለ ነገር ግን በምን መልክ ለምን አይነት ታካሚ መጠቀም እንዳለባቸው ካለማወቅ የተነሳ ከግምጃ ቤትም የማይወጣበት ሁኔታ ነበር፡፡ በዚህ ስልጠናና ክትትል ወቅት ግን መጋዘን ድረስ በመግባት እና እቃዎቹን በማውጣት መሳሪያዎቹን ለምን እና መቼ መጠቀም እንዳለባቸው አስተምረን አሰልጥነን ስራ ላይ እንዲያውሉአቸው አድርገናል፡፡ መሳሪያው የሌላቸውም በፕላን ኢንተርናሽናል በኩል የሚሟሉት እንዲሟሉ እየተደረገ የማይችሉትን ደግሞ መንግስት በምን መልክ ሊያሟላላቸው እንደሚችል መንገዱን በመጠቆምና የምክር አገልግሎት በመስጠት ዛሬ እናቶችና ሕጻናቱ በተገቢው የህክምና አገልግሎትን እንዲያገኙ አስችሎአል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ስልጠናውን ከመስጠት ባሻገር በየጤና ጣቢያዎቹ እየተገኘን ድጋፋዊ ክትትል በማድረጋችን የጤና ባለሙያዎቹ በጣም ተነሳሽነት አሳይተዋል፡፡ ስለሆነም አንዲት እናት ስትመጣ ሁሉም ተረባርበው የየድርሻቸውን የሚያበረክቱበት ሁኔታ ተፈጥሮአል፡፡ ይህም ከእለት ወደእለት እየተለወጠ እየተሻሻለ የመጣ እና በተለይም አምስተኛውን ድጋፋዊ ክትትል ስናደርግ የተመለከትነው እውነታ ነው፡፡ ስለዚህም እነዚህን የመሳሰሉ ለውጦች ባጠቃላይ ፕሮጀክቱ ያመጣቸው ለውጦች ናቸው ማለት     ይቻላል፡፡ ስለዚህም የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ ስለሆነና ሁሉም የመንግስት አመራሮች እዚህ ላይ ትኩረት አድርገው ስለሚንቀሳቀሱ ፕሮጀክቱ ለሚያፈራው ፍሬ አስተዋጽኦው ከፍ ያለ ነው፡፡
ጥ/ እናቶች ከፕሮጀክቱ ምን ያህል ተጠቃሚ ናቸው?
የሰለጠኑት የጤና ባለሙያዎች በአሁኑ ወቅት የሙያ ብቃታቸው በተጨማሪም የሚጠቀሙባቸውን የሕክምና መገልገያዎች በተገቢው ስራ ላይ በማዋላቸው እንዲሁም አንዲት እናት መቼ እና በምን ሁኔታ ላይ ስትገኝ ሪፈር መባል እንዳለባት ጠንቅቀው በማወቃቸው በአሁኑ ወቅት ፕሮጀክቱ በሚካሄድባቸው ቦታዎች የአንዲትም እናት ሞት ሪፖርት ደርሶን አያውቅም፡፡
ጥ/     ፕሮጀክቱ ሲያበቃ ስራው በምን መልክ ይቀጥላል?
መ/    ምንም እንኩዋን ፕሮጀክቱ ስራውን ቢያበቃም በነበርንባቸው የጤና ጣቢያዎች እና ሆስፒታሎች ውስጥ የሚመለከታቸው ባለሙያዎች አብረውን የድጋፍ ክትትሉን ሲሰሩ     ስለቆዩ እናቶችን እና ልጆቻቸውን በህክምና መርዳቱ በነበረበት እንዲያውም ተሻሽሎ     ይቀጥላል የሚል ግምት አለን፡፡ ይህ እንደ ሀገር የሁሉንም ትኩረት የሚስብ ከመሆኑም ባሻገር ይዘን የገባነው እውቀትን ማስጨበጥ በመሆኑ እውቀቱ ለምንጊዜውም ከባለሙያዎቹ ጋር ይኖራል፡፡ ስለዚህም እናቶችን እና ጨቅላ ሕጻናቱን በተገቢው የማገልገል ሂደቱ በጤና አመራሮቹ አማካኝነት ይቀጥላል የሚል ሙሉ እምነት አለን፡፡

Read 2268 times