Print this page
Saturday, 21 March 2015 11:04

ስስ ፌስታል ማምረትም ሆነ ከውጪ ማስገባት ተከለከለ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(7 votes)
  • ያገለገሉ ጐማዎችን ለማስወገድ ወደ አገር ውስጥ ማስገባትም ተከልክሏል
  • የአካባቢ ብክለት የሚያስከትሉ ድርጅቶች ላይ እርምጃ መውሰድ ተጀምሯል

   ለተለያዩ ዕቃዎች መያዣነት ሲያገለግሉ የቆዩትንና አካባቢን በመበከል የጤና እክል ያስከትላሉ የተባሉትን ከ0.03 ሚ.ሜትር በታች የሆኑ ስስ ፌስታሎች ማምረትም ሆነ ከውጭ ማስገባት ተከለከለ፡፡
ፌስታሎቹን ሲያመርቱም ሆነ ሲያስመጡ ባገኘኋቸው ህገወጦች ላይ እርምጃ እወስዳለሁ ብሏል የአካባቢና የደን ሚኒስቴር፡፡ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ሰሞኑን በአዳማ ከተማ ለጋዜጠኞች ባዘጋጀው “የአካባቢ ጥበቃና ለአየር ንብረት የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ” ግንዛቤ ማስጨበጫ አውደ ጥናት ላይ የሚኒስቴር መ/ቤቱ የአካባቢ ህግ ማስከበር ባለሙያ አቶ ግርማ ገመቹ እንደተናገሩት፤ አካባቢን ከብክለት ለመከላከል የሚያስችል የአካባቢ ፖሊሲ በ1989 ዓ.ም ወጥቶ ተግባራዊ መደረግ ቢጀምርም የህጐችን ተፈፃሚነት ለማረጋገጥና በሚደርሱ ጉዳቶች ላይ ተጠያቂነትን ለመፍጠር የሚያስችል አሠራር ባለመኖሩ እንዲሁም የከተሞች የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ህግ ባለመከበሩ የከተማው ቆሻሻ ለሰዎች እጅግ አደገኛ ሊሆን ችሏል፡ ለዚህም ዋንኛውን አስተዋጽኦ የሚያደርጉት በአገሪቱ በስፋት በጥቅም ላይ የሚውሉትና እንደ ቀልድ በየስፍራው የሚጣሉት ስስ ፌስታሎች ናቸው፡፡
ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከአለም ባንክ ጋር በመተባበር በ2005 ዓ.ም ጥናት ማድረጉን የጠቆሙት አቶ ግርማ፤ በጥናቱም በህጋዊም ሆነ በህገወጥ መንገድ እየተመረቱ ወይንም ከውጪ አገር እየገቡ ጥቅም ላይ የሚውሉት ስስ ፌስታሎች በአካባቢው ላይ የሚያደርሱት ጉዳት ዘላቂነት ያለውና እጅግ አደገኛም እንደሆነ መረጋገጡን ገልፀዋል፡፡ ስለዚህም እነዚህ ፌስታሎች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል ያሉት ባለሙያው አሁን ፌስታሎቹን በሚያመርቱና ከውጪ አገር እያስገቡ ጥቅም ላይ እንዲውል በሚያደርጉ ሰዎች ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ ውፍረቱ 0.03 ሚ.ሜ እና ከዚህ በታች የሆኑ ፕለስቲኮችን ማምረት፣ ማሰራጨትና ከውጪ አገር ማስገባት በጥብቅ መከልከሉንና በዚህ ተግባር ላይ የተሰማሩ ህገወጦችን ህብረተሰቡ ጥቆማ በማድረግ እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ህጋዊ ፌስታል አምራቾች በምርቶቻቸው ላይ ስለምርቱ አወጋገድ ምልክት እንዲያስቀምጡና የአምራቹን አድራሻ በግልጽ እንዲጽፉ ግዴታ መጣሉንም ገልፀዋል፡፡
የአካባቢ ብክለት ቁጥጥር አዋጅ አንቀጽ ዘጠኝ ያገለገለ ጐማን ለማስወገድ ወደአገር ውስጥ ማስገባት የተከለከለ መሆኑን እንደሚጠቁም የገለፁት አቶ ግርማ፣ ቀደም ሲል ከተለያዩ አገራት ገንዘብ እየተከፈለ እንዲወገዱ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ያገለገሉ ጐማዎችን መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለማድረግ የሚሰሩ ሰዎች ከፍተኛ ክምችት እንዲፈጠር በማድረጋቸው ምክንያት ያገለገሉ ጐማዎችን ለማስወገድ ወደ አገር ውስጥ ማስገባቱ እንዲቀር መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ነባር ምግብ ቤቶች የቆሻሻ አያያዛቸውን ኦዲት ማድረግና የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድና አያያዝ እቅድ ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው ህጉ እንደሚያስገድዳቸውም አቶ ግርማ ገልፀዋል፡፡
የኢንዱስትሪዎች ብክለት ቁጥጥር አዋጅ ነባር ኢንዱስትሪዎች ብክለታቸውን ለማስወገድ የሚያስችል አቅም እስከሚፈጥሩ ድረስ የእፎይታ ጊዜ ሰጥቷቸው እንደነበር ያስታወሱት አቶ ግርማ፣ የእፎይታ ጊዜው በመጠናቀቁ ምክንያትም ሰሞኑን ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ እርምጃ መውሰድ መጀመሩንና እርምጃው ፋብሪካዎቹን እስከመዝጋት የሚደርስ እንደሆነም ጨምረው ገልፀዋል፡፡ 

Read 3386 times