Saturday, 21 March 2015 11:19

በሽብር የተከሰሱት ተቃዋሚዎች የቀረቡባቸውን ክሶች አልፈጸምንም አሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(9 votes)

“ዜጐችን እያሸበረ ላለው የፀረ ሽብር ህግ እውቅና መስጠት ስለሆነ መልስ የለኝም”  
- ዘላለም ወ/አገኘሁ
“አሸባሪው ህወሓት/ኢህአዴግ ነው፤ እኔ የአሸባሪ ቡድን ተቃዋሚ ነኝ”
- አብርሃ ደስታ
ተከሳሾች ካልተገባ ንግግር እንዲቆጠቡ ፍ/ቤቱ ተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ሰጥቷል
      በአሸባሪነት የተከሰሱት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና ግለሰቦች በቀረበባቸው ክስ ላይ የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ተጠይቀው ሁሉም ተከሳሾች የተመሰረተባቸውን ክስ ክደው በመከራከራቸው አቃቤ ህግ ማስረጃውን እንዲያቀርብ ፍ/ቤት ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
የቀድሞ የአንድነት ፓርቲ አመራሮች አቶ ሃብታሙ አያሌውና አቶ ዳንኤል ሺበሺን ጨምሮ የሠማያዊ ፓርቲ አመራር አቶ የሸዋስ አሠፋ፣ የአረና ትግራይ ፓርቲ አመራር አቶ አብርሃ ደስታ እንዲሁም ሌሎች 6 ግለሰቦች፤በኢትዮጵያ መንግስት በአሸባሪነት የተፈረጀው የግንቦት 7 ድርጅት አባል በመሆንና በመገናኘት ለተለያዩ የሽብር ተግባራት ሲሰናዱ ነበር በሚል ክስ እንደተመሰረተባቸው የሚታወስ ሲሆን ከትናንት በስቲያ በዋለው ችሎት ተከሳሾቹ የእምነት ክህደት ቃላቸውን  ሰጥተዋል፡፡
1ኛተከሳሽ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስ ተማሪው ዘላለም ወ/አገኘሁ ለፍርድ ቤት በሰጠው ቃል፤ “በማላውቀው ጉዳይ ላሠረኝ ፖሊስና የደህንነት አካል እንዲሁም ዜጐችን እያሸበረ ላለው የፀረ-ሽብር ህግ እውቅና መስጠት ስለማልፈልግ መልስ የለኝም” ብሏል፡፡ ሁለተኛ ተከሳሽ አቶ ሃብታሙ አያሌው በበኩሉ፤“በክሱ ላይ የተመለከተውን ድርጊት የመፈፀም ሃሳቡ እንደሌለኝ እኔን ያሠረኝ አካልም በሚገባ ያውቀዋል፤አቃቤ ህግም ለምን እንደከሰሰኝ አውቃለሁ” ብሏል፡፡  “እኔን በማሠር ህጋዊ ፓርቲዬ አንድነትን በማፍረስም ኢህአዴግ ተሣክቶለታል፣ በማለት ቃሉን ሰጥቷል፡፡
 3ኛ ተከሣሽ አቶ ዳንኤል ሺበሺ ለፍርድ ቤቱ በሰጠው ቃል፤“እኔ ሽብር የሚባለውን የሰማሁት ከአልቃይዳው መሪ ኦሳማ ቢንላደን እና ከአቶ መለስ ዜናዊ ነው፣ እኔ አሸባሪ አይደለሁም፣ የሽብር ድርጊት የመፈፀም ፍላጐትም አላማውም የለኝም፣ ኢህአዴግ እኔን አስሮ ፓርቲዬን ለማፍረስ የፈነቀለው ድንጋይ ነው” ብሏል፡፡
4ኛ ተከሣሽ አብርሃ ደስታ በበኩሉ፤“አሸባሪ ማለት ለሚፈልገው አላማ ሠላማዊ ዜጐችን የሚያሸብር ነው፤ በዚህም ብቸኛ አሸባሪው ህወኃት /ኢህአዴግ ነው፤እኔ የአሸባሪ ቡድን ተቃዋሚ ነኝ” ሲል ቃሉን የሰጠ ሲሆን ዳኞች በቀጥታ ድርጊቱን ስለመፈፀሙና አለመፈፀሙ ቃሉን እንዲሰጥ በተደጋጋሚ ቢጠይቁም በቀጥታ ባለመመለሱ ድርጊቱን እንደካደ ይቆጠራል ብለዋል፡፡ በክሱ ላይ ስለ ህወኃት/ኢህአዴግ የተጠቀሰ ነገር አለመኖሩን የገለጹት ዳኞች፤ተከሣሹ ካልተገባ ንግግር እንዲቆጠቡ አሳስበዋል፡፡
5ኛ ተከሳሽ የሠማያዊ ፓርቲ አመራሩ አቶ የሸዋስ አሠፋ፤ስለፍርድ ቤቱና ስለ ዳኞች ነፃ አለመሆን ከተናገሩ በኋላ “ፍ/ቤቱ የጦር ፍርድ ቤት እየመሰለ ነው፤አሻንጉሊት የሆነ ፍ/ቤት ነው” በማለት ሲቀጥሉ ዳኞች ያስቆሟቸው ሲሆን ተከሣሾቹ ከተጠየቁት ጉዳይ ጋር ተያያዥነት የሌለው ቃል እንዳይናገሩ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል፡፡
6ኛ ተከሣሽ አቶ ዮናታን ወልዴ፤ “በክስ መልክ የተዘጋጀልኝን ተውኔት ያለፈቃዴ እንድተውን እየተገደድኩ ነው” ሲሉ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ 7ኛ ተከሣሽ አቶ አብርሃም ሠለሞን በበኩላቸው፤ “የተቀነባበረ ክስ ስለሆነ ምንም ማድረግ አይቻልም፤ያው መካድ ነው” ብለዋል፤ለፍ/ቤት በሰጡት ቃል፡፡  
 8ኛ ተከሣሽ አቶ ሠለሞን ግርማ፤“ድርጊቱን አልፈፀምኩም” ሲሉ የተመሰረተባቸውን ክስ በመካድ የተከራከሩ ሲሆን 9ኛ ተከሳሽ አቶ ባህሩ ደጉ፤ለሃይማኖቱ ታማኝ ከሆነ ማህበረሰብ ተፈጥረው ሽብር ሊፈጽሙ እንደማይችሉ በመጠቆም “ጊዜ ይፈታዋል” ብለዋል፡፡ 10ኛ ተከሣሽ አቶ ተስፋዬ ተፈሪ በበኩላቸው፤በማላውቀው ጉዳይ ተገድጄ ነው ፈጽሜያለሁ ብዬ የፈረምኩት እንጂ ድርጊቱን አልፈፀምኩም” ሲሉ ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡
ተከሣሾች ካልተገባ ንግግር ተቆጥበው ድርጊቱን ስለመፈፀምና አለመፈፀማቸው ብቻ ለፍ/ቤቱ የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ በተደጋጋሚ ያሳሰበው ፍ/ቤቱ፤ ሁሉም ተከሣሾች የቀረበባቸውን ክስ ክደው በመከራከራቸው አቃቤ ህግ ማስረጃዎቹን እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡  
አቃቤ ህግ በተከሳሾቹ ላይ 15 ምስክሮች መቁጠሩን በማስታወስም፣ ግንቦት 13‚ 14 እና 17 የአቃቤ ህግ ምስክሮች የሚሰሙባቸው  እንዲሆኑ ፍ/ቤቱ ወስኗል፡፡ ባለፈው ሳምንት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮቹ፤አብርሃ ደስታ፣ የሺዋስ አሠፋና ዳንኤል ሺበሺ ሁለት ጊዜ  ፍ/ቤት ተዳፍረዋል ተብለው  የ14 ወራት እና የ16 ወራት እስራት እንደተፈረደባቸው ይታወሳል፡፡

Read 2652 times