Saturday, 21 March 2015 11:23

የደቡብ ሱዳን መንግስት የኢትዮጵያ አማፅያንን እየረዳ ነው ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(21 votes)

    በፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት የሚመራው የደቡብ ሱዳን መንግስት የኢትዮጵያ መንግስትን በጦር የሚፋለሙ አማፅያንን እየረዳ ነው ሲሉ በዶ/ር ሪክ ማቻር የሚመሩት የሃገሪቱ አማፅያን ወነጀሉ፡፡
በቀድሞ የሃገሪቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሪክ ማቻር የሚመራውን የአማፂ ቡድን ቃል አቀባይ ጀምስ ጋትዴት ዳክ ጠቅሶ የዘገበው ሱዳን ትሪቡን፤ የሳልቫኪር መንግስት ከኦሮሞ፣ አኙዋክ፣ ኑዌርና ሙሪሌ ብሄሮችና ጎሳዎች የተውጣጡ አማፅያንን እያስታጠቀና እያሰለጠነ ነው ብሏል፡፡
“የሳልቫኪር መንግስት አካባቢውን ለማተራመስ የኢትዮጵያ አማፂያንን የጦር መሳሪያ እያስታጠቀ፣ ወታደራዊ ስልጠና እየሰጠና እያደራጀ ለመሆኑ በቂ የሆነ ተጨባጭ ማስረጃ አለን” ብለዋል ቃል አቀባዩ፡፡
በደቡብ ሱዳን መንግስት አማካኝነት በጋራ ተደራጅቷል የተባለው የኢትዮጵያ አማፂ ቡድን፤ በደርግ ዘመን የጋምቤላ ክልል አመራር በነበሩት ቶዋት ፖል ቻይ እንደሚመራ የጠቆመው ዘገባው፤ አማፅያኑ የደቡብ ሱዳን መንግስት በዶ/ር ሪክ ማቻር አማፂ ቡድን ላይ በቅርቡ በከፈተው መጠነ ሰፊ ጥቃት ላይ በቀጥታ መሳተፋቸውን ቃል አቀባዩን  ዋቢ አድርጎ አስታውቋል፡፡ “የኢትዮጵያ አማፂ ቡድኖች በጦርነቱ የተሳተፉት በሚያገኙት ቀዳዳ የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰው ወደ ጋምቤላ ክልል ለመግባትና ክልሉን ለማተራመስ ነው” ብለዋል ቃል አቀባዩ፡፡ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በሁለቱ ሃገራት የጋራ ድንበር አካባቢ መስፈር መጀመሩንም ሱዳን ትሪቡን ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡
ዶ/ር ሪክ ማቻር የሚመሩትን የደቡብ ሱዳን አማፅያን የኢትዮጵያ መንግስት ይረዳል የሚል ጥርጣሬ የሳልቫ ኪር መንግስት እንዳለውና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአዲስ አበባና በጁባ መንግስታት መካከል ያለው ግንኙነት እየሻከረ መምጣቱን የጠቆመው ዘገባው፤ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ኬንያም የሪክ ማቻርን አማፅያን ትረዳለች ሲሉ በቅርቡ መናገራቸውንም አስታውሷል፡፡
የካርቱም መንግስትም “አማፂያኑን እያስታጠቀብኝ ነው” ሲሉ ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር በተደጋጋሚ መክሰሳቸው በዘገባው ተጠቅሷል፡፡  
የኢትዮጵያ መንግስት በጉዳዩ ላይ እስካሁን መረጃ እንደሌለው የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡

Read 6802 times