Saturday, 28 March 2015 08:59

አሜሪካ በግድቡ ዙሪያ የተደረገውን ስምምነት አደነቀች

Written by 
Rate this item
(13 votes)

የአሜሪካ መንግስት ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያለባቸውን አለመግባባት ለመፍታትና ፍትሃዊ የውሃ ክፍፍል እንዲረጋገጥ ለማድረግ ባለፈው ሰኞ የፈረሙትን የትብብር ስምምነት እንደሚያደንቅ ማስታወቁን ኢጂብት ኢንዲፔንደንት ዘገበ፡፡
የአሜሪካ መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጄን ፓስኪ ባለፈው ረቡዕ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ አሜሪካ ሶስቱ አገራት በአባይ ወንዝ የውሃ ድርሻ ላይ የሚያነሱትን ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያስችላል የተባለውን ስምምነት፣ አገራቱ በጉዳዩ ዙሪያ አንድ እርምጃ መራመዳቸውን የሚያሳይ ጠቃሚ ሁነት በመሆኑ ታደንቀዋለች ብለዋል፡፡
መንግስታቸው በአገራቱ መካከል የትብብር መንፈስ እንዲፈጠር ለማድረግና የሁሉንም አገራት ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ አባይን በዘላቂነት ለማልማት ከኢትዮጵያ፣ ከግብጽና ከሱዳን ጋር በትብብር እንደሚሰራም አስታውቀዋል፡፡
ሶስቱ አገራት የአባይን ውሃ በፍትሃዊነት መጠቀም የመቻላቸው ጉዳይ፣ በአገራቱ መካከል ዋነኛ የውጥረት መንስኤ ሆኖ መቆየቱን የጠቆመው ዘገባው፣ የተፈረመው ስምምነት በሁሉም አገራት የውሃ ደህንነት ላይ ጉዳት እንዳይከሰት የሚያደርግ መሆኑንና ግብጽና ሱዳን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ይፋዊ እውቅና መስጠታቸው የታየበት ነው መባሉን አመልክቷል፡፡
በሌላ በኩል በአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር የሆኑት አቶ ዳር እስከዳር ታዬም፤ የግብጹ ፕሬዚዳንት ወደ ድርድር መምጣታቸውና የግድቡን መገንባት አለመቃወማቸው ከዚህ በፊት አገራቸው ስታራምደው ከነበረው አቋም የተለየና አንድ እርምጃ ወደፊት የተራመደ ነው ብለዋል፡፡ የትብብር መንፈሱ ጠቃሚነት እንዳለው የጠቆሙት ምሁሩ፣ የትብብሩ መንፈስ እውነት መሆንና አለመሆን ግን በስምምነቱ አፈጻጸም ላይ የሚታይ ይሆናል ብለዋል፡፡
የቀድሞው የኢዴፓ ሊቀመንበር አቶ ልደቱ አያሌው በበኩላቸው፤የግብጹ ፕሬዚዳንት የአባይን ውሃ ከፈጣሪ እንደተበረከተ የግል ስጦታ ከማየት አስተሳሰብ ተላቀው፣ ውሃው የሌሎች አገራትም ሃብት እንደሆነ እውቅና መስጠታቸውን አድንቀው፣ስምምነቱን መፈረማቸው ብስለታቸውን ያሳያል ብለዋል፡፡ “ትብብሩ የሁለቱንም አገራት ህዝቦች በሚጠቅም መልኩ እንዲቀጥል ማድረግ ይገባል፤ የአልሲሲ ጅምር መልካም ቢሆንም ውጤቱ በሂደት የሚታይ ይሆናል” ሲሉ አቶ ልደቱ አስተያየታቸውን ገልጸዋል፡፡

Read 3792 times