Saturday, 28 March 2015 09:01

ሞኝ ሁለቴ ይነደፋል! አንዴ እባቡ ሲነድፈው፣ አንዴ እባቡን ሲያሳይ

Written by 
Rate this item
(15 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት ቆቅ ሰባት ልጆቿን ይዛ ከቤት ወጥታ መንገድ ትጀምራለች፡፡
1ኛዋ ጫጩት - እማዬ ወዴት ነው የምንሄደው?
እናት - ቆቅ - ወደሩቅ አገር
2ኛዋ ጫጩት - እዚያ አገር ምን አለ?
እናት ቆቅ - የተሻለ ኑሮ
3ኛዋ ጫጩት - የተሻለ ኑሮ ምንድን ነው?
እናት ቆቅ - የተሻለ ምግብ፣ የተሻለ መጠለያ፣ የተሻለ ወጥቶ - መግባት
4ኛዋ ጫጩት - በመሬትም በአየርም እንደልባችን የመብረር መብት አለን?
እናት ቆቅ - አዎ፡፡ እንደልብ መሮጥ፣ እንደ ልብ መናገር፣ እንደልብ ሀሳባችሁን የመግለጥ፣ የምትወዱን መውደድ፣ የምትጠሉትን መጥላት ትችላላችሁ፡፡
5ኛዋ ጫጩት - የፈለግነው ከተማ ሄደን መኖርስ እንችላለን?
እናት ቆቅ - በደንብ ትችላላችሁ፡፡
6ኛዋ ጫጩት - ትንሽ ትልቅ፣ ቆንጆ አስቀያሚ፣ የተማረ፣ ያልተማረ፣ የዚህ ወፍ ዝርያ የዚያ ወፍ ዝርያ ብለው፤ አንዱን ጠቅመው ሌላውን ጎድተው አያዳሉብንም?
እናት ቆቅ - እንደሱ ቀርቷል፡፡ ጅግራም ሆናችሁ ቆቅ፣ ቁራም ሆናችሁ አሞራ፣ ወፍም ሆናችሁ ወማይ፣ ሣቢሳም ሆናችሁ ጥምብ አንሳ እንደየ ዝርያችሁ የመኖር መብት አላችሁ፡፡ በዝርያችሁ የሚነካችሁ ምንም የለም፡፡
7ኛዋ ጫጩት - እነዚህ የዘረዘርሺልን እርስ በርስ ቢጣሉስ ማን ያስታርቃቸዋል?
እናት ቆቅ - የሁሉም የበላይ የሆነ የአዕዋፍ ንጉሥማ ይኖራል፡፡ ያለንጉሥ መኖርማ አይቻልም፡፡
ይህን እየተጨዋወቱ መንገድ እያቆራረጡ ሄደው ዋናው አውራ ጎዳና ጋ ደረሱ፡፡ አውራ ጎዳናውን ከጠርዝ ጠርዝ በወርዱ አንድ ዘንዶ ተጋድሞበታል፡፡ እናት ቆቅ ዘላ ለመሄድ አልደፈረችም፡፡ ስለዚህ የተኛውን ዘንዶ ቀስቅሳ “ለምን ተኛህ?” ልትለው ፈለገች፡፡ አንገቱን በኩምቢዋ ነካ ነካ አደረገችና፤
“አያ ዘንዶ ምነው በደህና ነው የተኛኸው?” አለችው፡፡ ዘንዶው ለምን እንደተኛ አስቦ አስቦ፤
“ርቦኝ ነው የተኛሁት” አላት፡፡
“እንግዲያው ልጆቼን ልስጥህና ጥገብ፡፡ እኔን ተወኝ” አለችው፡፡
ልጆቿን ዋጠ፡፡ እሷ ተሻግራው ሄደች፡፡
ዘንዶው ጫጩቶቿን በልቶ አላበቃም፡፡ ሀሳብ ያዘው፡፡ “ይቺ ቆቅ እንዴት አምና ልጆቿን ብላ አለችኝ፡፡ ነገር ቢኖራት ነው” አለ፡፡ ቢያስበው ቢያስበው ለተንኮል ነው ብሎ ያሰበው ነገር አልመጣ አለው፡፡ በመጨረሻ፤
“እኔ ምን አሳሰበኝ? እራሷን ብበላት እገላገል የለም እንዴ?” አለና ሲምዘገዘግ ወደ ቆቋ ሄደ፡ ያዛትና “ዓላማሽ ምን እንደሆነ ስላልገባኝ መፍትሔው ራስሽን መዋጥ ነው” ብሎ፤ በልቷት ተገላገለ!
*       *      *
ከማይጠግብ ዘንዶ ይሰውረን፡፡ ልጅም ሰውቶ ራስን ከማጣት ያድነን፡፡ በተጓዝን ቁጥር የተኛ ዘንዶ ከማግኘት፣ እሱን ሳይቸግረን ቀስቅሰን ከመዋጥ የሚጠብቀንን ይዘዝልን፡፡ የማይፈራውን ፈርተን፣ የተኛውን ቀስቅሰን፣ ትውልዳችንን ገብረን፣ የተደሰትን መስሎን ዘራፍ ከማለት ግብዝነት ይሰውረን፡፡
ወደድንም ጠላንም ዘንዶው ዘንዶ ነው! መንገዱን የዘጋው በራሱ ተማምኖ ነው፡፡ ዓመታት መቁጠርና ዘንዶውን “ምስህ ምንድን ነው?” ብለን እንደ ቅድመ ታሪክ ዘንዶ መገበር ሳይሆን መብሰል፣ ራስን ማወቅ፣ ራስን መቻል፣ በራሴ መተዳደር እችላለሁ ማለት ያሻል፡፡
የሀገር ጉዳይ፤ “ያለቀበት” የሚባል የጉልበት ገበያና “ሁሉንም በአምሥት …” የሚባል ዓይነት ንግድ መሆን የለበትም፡፡ ትግልም፣ ልማትም፣ ዲሞክራሲም የሂደት ጉዳይ ነው፡፡ ቁርጥም ነገር፣ ቆረጣም ነገር የለበትም፡፡ እየተወራረደ፣ እየተሞራረደ የሚጠራ፣ የሚሻሻል፣ የሚለወጥ ሂደት ነው!! ዘመን መቁጠር “አዲስ ፍሬ ምን ያህል አፈራሁ?” የማለት የጠራ ዕድገት ከሌለበት እንደው “ዕድሜዬ ይሄን ያህል ነው ከማለት አያልፍም!”
የየራሳችንን የውስጥ ችግር ሳንፈታ ዕድሜዬ ይሄን ያህል ነው ብለን መፎከር የባሰ ምስቅልቅል ችግር ውስጥ መዘፈቅ ነው፡፡ ለአቅመ አዳም ከደረሰ በኋላ ቤተሰቦቹ ጋ የሚኖር ልጅ ከተጧሪ አንድ ነው!
“ፍሬ በስሎ የሚበላው
ወይ በራሱ ጊዜ ሲወድቅ፣ ወይ እኛ ስንለቅመው ነው”
እንደሚባል የገባው ዕውነተኛ ብስለት ያለው ነው፡፡ የውስጥ ደም መፍሰስ (Internal Bleeding) ከአዲስ ደም መቀበል (New Blood Injection) ጋር አይገናኝምና መጀመሪያ የአንጎል ውስጥ ደም ፍሰቱን መገላገል ዋና ነገር መሆኑን ማስተዋል ነው!
“እናቴን ያገባ ሁሉም አባቴ ነው!” ዓይነት አስተሳሰብ የትም አያደርሰንም፡፡ ጊዜን ባግባቡ መለካት ነው የፖለቲካ ቁም ነገር!
ቅዱስ አውግስቶስ ኑዛዜ (Confession) በተባለ ግጥሙ፤
ምንም ነገ ባያልፍ፤ ትላንትና የለም
ምንም ድርጊት ባይኖር፣ ነገ አይፈጠርም
ዛሬም ነገር ባይኖር፣ መኖርን አናቅም
ያለፈው፣ የመጪው፣ የአሁን ውዝዋዜ
ጊዜ ማለት ያ ነው፣ ያ ነው ለእኔ ጊዜ!
በዓላትን ስናከብር የሠራነውን ፍሬ - ነገር እናስተውል፡፡ ፈንጠዝያን ከብስለት እንለይ! አለበለዚያ፤ “ሞኝ ሁለቴ ይነደፋል፡፡ አንዴ እባብ ሲነድፈው፣ አንዴ እባቡን ሲያሳይ” የሚባለው ተረት ሰለባ እንሆናለን! የኋሊት ወደ ታሪክ ሳይሆን ወደፊት፣ ታሪክ ወደ መስራት እንጓዝ!!

Read 7455 times