Saturday, 28 March 2015 09:07

‘ተጨማሪ አርባ ከመቶ’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(9 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሰውየው ጓደኛውን…
“እስቲ የወር ገቢህን ለምን፣ ለምን እንደምታውለው ንገረኝ…” ይለዋል፡፡ ጓደኝየውም ያብራራለት ገባ…
“ሠላሳ ከመቶ ለቤት ኪራይ፣ ሠላሳ ከመቶ ለልብስ፣ አርባ ከመቶ ለምግብ፣ አርባ ከመቶ ደግሞ ለመዝናኛ፣” ይለዋል፡፡
ሰውየው ሂሳቡን ሲያሰላ የጓደኛው ወጪ ከሚያገኘው የወር ገቢ ይበልጥበታል፡፡ “አሁን የነገርከኝ እኮ መቶ አርባ ከመቶ ነው የሚመጣው…” ይለዋል፡፡ ጓደኝየውም ምን አለ መሰላችሁ…
“ይኸውልህ ዘንድሮ ኑሯችን ገቢ መቶ ከመቶ፣ ወጪ መቶ አርባ ከመቶ ሆኗል፣” ብሎት አረፈ፡፡
እናማ… እንደ አያያዛችን ከሆነ ‘መቶ አርባ ከመቶ’ ወጪንም “እሱማ ተገኝቶ ነው!” የምንልበት ጊዜ ሊመጣ ይችላል፡፡ አብዛኞቹ ነገሮች (በተለይ የምግብ ሸቀጦች) በየሳምንቱና ሲብስበትም በየሁለትና ሦስት ቀኑ የሚጨምርባት አገር ብትኖር የእኛዋ ብቻ ሳትሆን አትቀርም!
የደላቸው አገሮችማ ‘ኮንሲዩመር ፕሮቴክሽን’ ምናምን የሚባሉ መብቶቻቸውን የሚያስከብሩላቸው ህጎችና ቡድኖች አሏቸው። ሲብስና ዋጋ እየጨመሩ የሚያስቸግሩ ካሉ…አለ አይደል… “በቃ፣ አንገዛም፡፡ ምን ምን እንደምትሆኑ እናያለን…” ብለው መደብሮቹን የዝንብ መፈንጫ ያደርጓቸዋል፡፡ እኛ ዘንድ ግን የሆነ ነገር ዋጋ በጨመረ ቁጥር… “ነገ ደግሞ እንዳይጨምሩ ቶሎ እንግዛ…” ተብሎ ግፊያ ነው፡፡ ከዛም በየድራፍቱ ላይ… “በረሀብ ሊገድሉን ነው…” እያልን ማማረር ነው፡፡
የምር ግን…ነገሬ ብላችሁ እዩማ…በዚህ ወር ለምግብ ሸቀጦች የምታወጡት ወጪ ከመጪው ወር ጋር እኩል ከሆነ… አለ አይደል…‘ታስበው የሚውሉና የሚያድሩ’ ምሳና እራቶች አሉ ማለት ነው፡፡
እናማ… ‘ተጨማሪዋን አርባ ከመቶ’ ያለወለድ በማበደር ‘ታሪክ የሚያስመዘግብ’ ባንክ ይፈጠርልንማ!
ከ‘ተጨማሪ አርባ ከመቶ’ የምንድንበት ጊዜ ይምጣልንማ!
(የኮንዶሚኒየም ዕድለኞች እንኳን ደስ አላችሁ! ‘የዋጋ ማስተካከያው’ እንዴት ነው… ነገርዬው ‘ተጨማሪ አርባ ከመቶ’ አይነት እንዳይሆን ብዬ ነው፡፡ ቢሆንም ይሁን… ልጄ፣ “ምነው ሰጥተውኝ የፈለገውን ክፈል ቢሉኝ…” የሚል ስንትና ስንት ሺህ ህዝብ አለ!)
ከ‘ተጨማሪ አርባ ከመቶ’ የምንድንበት ጊዜ ይምጣልንማ!
ስሙኝማ…የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ…ተመሳስለው የተሠሩ ነገሮች አልበዙባችሁም!“….ምርቶቻንን አስመስለው የሚሠሩ እንዳሉ ስለደረስንበት…” ምናምን የሚሉ ነገሮች እየተለመዱ ነው፡፡ እናማ… ግራ የሚገባን… አለ አይደል…ይሄ ሁሉ ‘አስመስሎ ሠሪ’ እያለ እንዴት ነው የሆነ ‘ጋማውን የሚያዝ’ የሌለው! ልክ ነዋ…“እከሌ ድርጅት የእከሌን ድርጅት ምርት አስመስሎ መሥራቱ ስለተረጋገጠበት…” የሚል ነገር የማንሰማሳ! አሀ…አንዳንድ ጊዜ “ይቺ እንኳን የፕሮሞሽን ‘ፊንታ’ ነች…” የሚል ጥርጣሬ ሊያድርብን ይችላላ!
ለነገሩ ምን መሰላችሁ… “ያልጠረጠረ ተመነጠረ” የምትለው ተረት ዘመኗ ነው፡፡ ልክ ነዋ…ብዙ ነገሮችን ተመሳሰለው የተሠሩ ይሁኑ ‘እውነተኛዎቹ’ ለመለየት እየተቸገርን ነዋ!
ለነገሩማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… የተለያዩ ምርቶች ብቻ ሳይሆኑ ‘ተመሳስለን የተሠራን’ ሰዎችም ቁጥራችን ቀላል አይደለም፡፡ በአለባበስ በሉት፣ በአነጋገር በሉት፣ በአረማመድ በሉት፣ በቢራ አጨላለጥ በሉት፣ …ምን አለፋችሁ በየፊልሙ በየምናምኑ ላይ ካየነው ጋር ‘ተመሳስለን የተሠራን’ ለመምሰል የምንሞክር መአት ነን፡፡
ታዲያላችሁ…በቀደም አንድ መዝናኛ ቦታ የሆኑ ወጣት ሴቶች የ‘ታቱ’ ዋጋ በጣም እየጨመረ መሆኑን እየተናገሩ ሲበሳጩ ነበር፡፡ ‘ተጨማሪ አርባ ከመቶ’ አይነት ነገር በሉት፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ‘ታቱ’ እየተለመደ አይደል! በነገራችን ላይ የሆነ ግርም የሚለኝ ነገር አለ… ‘ንቅሳት’ የሚለውን ቃለ ላለመጠቀም “ታቱ እንሠራለን…” ከተማችን በተለያየ ቦታ ታያላችሁ፡፡ የምር እንነጋገር ከተባለ… “ታቱ እንሠራለን…” ከሚለውና “ንቅሳት እንነቅሳለን…” ከሚለው አሪፉ የቱ ነው! ምን ይደረግ… ‘በእንግሊዝኛ የማነጠስ’ አይነት ‘ተመሳስሎ የመሠራት’ አባዜ ስላለብን አልለቀን ሲልስ! እናላችሁ… ድሮ ‘ኒቂሴ’፣ ‘አዲስ ዘመን ጋዜጣ’ ምናምን እየተባለ ይቀለድባት የነበረችው ንቅሳት ዞራ ‘ታቱ’ ተብላ ስትመጣ እኛ ቀለብናታ!  ምናልባት ነገርየው ያልገባን ካለን… ‘ታቱ’ ማለት ‘ንቅሳት’ ማለት ነው፡፡ (‘አራት ነጥብ!’ የሚለውን ጨምሩልኝማ!)
ከ‘ተጨማሪ አርባ ከመቶ’ የምንድንበት ጊዜ ይምጣልንማ!
ይሄን ሰሞን በማህበራዊ ድረ ገጾች ላይ የሚቀባበሏት ነገር አለች… የተለቀቀብን ‘ስሪ ጂ ነው፣ ስሪ ጅብ’ የምትል፡ የምር እኮ…‘ሙልጭ የማድረግ’ አይነት አለው እንዴ! እኔ ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…በተለይ በዚህ ዘመን ብዙ ነገር ከኢንተርኔት ጋር የተያያዘ እየሆነ መጥቷል፡፡ ስለመጣ ሁላችንም ሳንሳቀቅ የምንጠቀምበት ‘ዋጋ’ ቢኖር አሪፍ ነው፡፡ ይኸው ባንኮቹ ሁሉ… አለ አይደል… ‘እኛ ዘንድ በመመላለስ እግራችሁ ሳይቀጥን ባላችሁበት ሆናችሁ ሁሉንም ነገር በኢንተርኔት መጠቀም ትችላላችሁ…’ አይነት ነገር እያሉን አይደል!
የምር ግን…ነገ፣ ተነገ ወዲያ ደግሞ እንደ ሌሎቹ ሀገራት እቤታችን ቁጭ ብለን ለመገበያየት፣ ታክስ ለመክፈል፣ …ምናምን እንዲያበቃን ከአሁኑ የሚያስፈሩን ነገሮች ባይኖሩ አሪፍ ነው፡፡ በዚሀ ላይ ደግሞ በኢንተርኔት አጠቃቀም በዓለም ያለንበትን ደረጃ እናውቀዋለን! ኢንተርኔት የመሳሰሉ አገልግሎቶች ‘እንደ ቦኖ ውሀ’ ለሁላችን የሚደርስበትን ዘመን ያምጣልንማ!
ከ‘ተጨማሪ አርባ ከመቶ’ የምንድንበት ጊዜ ይምጣልንማ!
እኔ የምለው…ስልክ ምናምን ሰፈር ከደረስን አይቀር… የአገልግሎት ጥራት ይሻሻልንማ! ልክ ነዋ…ጥሪያችን መሀል ላይ እየተቋረጠ…“እንዴት ጆሮዬ ላይ ትዘጋለህ!…” ምናምን አይነት ጠብ ያመጠብናላ!
እግረ መንገዴን ይቺን ስሙኝማ…ሰውየው ሌሊት የተሳሳቱ ጥሪዎች እየረበሹት ተቸግሯል፡፡ ለቴሌፎን ኩባንያው አቤት ቢልም ምንም መፍትሄ ሊሰጡት አልቻሉም፡፡ ታዲያላችሁ…አንድ ቀን ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ላይ የሆነ ቁጥር ላይ ይደውላል። ስልኩም ይነሳል፡፡ ከወዲያኛው ጫፍ  እንቅልፍ ያንጎላጀጀው ድምጽ “ሄሎ ማን ልበል?” ይላል፡፡
“የቴሌፎን ኩባንያው ሥራ አስኪያጅ ነህ?”
“አዎ ነኝ፣ በዚህ ሰዓት የሚደውለው ማነው?”
“በተሳሳተ የስልክ ጥሪ ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት መቀስቀስ ምን እንደሚመስል እንድታውቀው ብዬ ነው…” ብሎ ስልኩን ጠረቀመው፡፡
ብቻ ሆነም ቀረ በምንም ይሁን በምን ከ‘ተጨማሪ አርባ ከመቶ’ የምንድንበት ጊዜ ያምጣልንማ!
ይቺን የሆነ ቦታ ያነበብኳትን ነገር እዩልኝማ…ወጣቷ አለቃዋ ሴት ነበረች፡፡ እናላችሁ… አንድ ቀን አለቃዋ ጎኗ ሆና ስልኩ ይጠራል፡፡ ወጣቷም ታነሳና…“ሄሎ ማን በል?” ትላለች፡፡ ከዚያም ዝም ብላ ከወዲያኛው ስታዳምጥ ትቆይና፤ “ለአንቺ መሰለኝ…” ብላ ለአለቃዋ ታቀብላታለች፡፡ አለቅየዋም ቆጣ ትልና…
“ወይ ላንቺ ነው፣ ወይ ላንቺ አይደለም ይባላል እንጂ መሰለኝ ብሎ ነገር ምንድነው!” ትላለች፡፡ ወጣቷ ምን ብትል ጥሩ ነው…
“አይ ሰውየው፣ ‘አንቺ ደደብ አሁንም አለሽ’ ሲል ላንቺ መስሎኝ ነው፣” ብላት እርፍ!
ከ‘ተጨማሪ አርባ ከመቶ’ የምንድንበት ጊዜ ይምጣልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2373 times