Saturday, 28 March 2015 09:23

የዓለማችን ግዙፉ “አውሮፕላን” ከ6 ወራት በኋላ ይበርራል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

በዓለማችን በግዙፍነቱ አቻ እንደማይገኝለት የተነገረውና ሃይብሪድ ኤር ቪሄክልስ በተባለው የእንግሊዝ ኩባንያ ዲዛይን የተደረገው “ኤርላንደር 10” የተሰኘ አዲስ አይነት አውሮፕላን ከስድስት ወራት በኋላ ስራው ሙሉ ለሙሉ ተጠናቅቆ በእንግሊዝ ሰማይ ላይ የሙከራ በረራ እንደሚያደርግ ሲኤንኤን ዘገበ፡፡
በአሜሪካ የጦር ሃይል ለወታደራዊ አሰሳ ስራ እንዲውል ታስቦ የተሰራው ይህ አውሮፕላን፤ርዝማኔው ከአንድ የእግር ኳስ ሜዳ እንደሚበልጥ የጠቆመው ዘገባው፣ 302 ጫማ ቁመት እንዳለው፣ዲዛይኑም ከተለመደው ወጣ ያለና የአውሮፕላንና የሄሊኮፕተር ቅልቅል እንደሆነ አመልክቷል፡፡
ኩባንያው የአውሮፕላኑን ፕሮጀክት ከጀመረ ቆየት ቢልም፣ በበጀት እጥረት ምክንያት ሥራው  ሲጓተት መቆየቱን ያስታወሰው ዘገባው፣ በመጨረሻም ከእንግሊዝ መንግስት ባገኘው የ5.1 ሚሊዮን ዶላር ብድር ስራውን ከዳር ማድረሱን አስታውቋል፡፡
አውሮፕላኑ 10 ቶን ክብደት የመጫን አቅም ያለው ሲሆን አጠቃላይ አሰራሩ ዘመናዊና በቴክኖሎጂ የታገዘ ነው ተብሏል፡፡ ነዳጅ ቆጣቢነቱ፣ በአስቸጋሪ የአየር ንብረት ሁኔታዎችን ተቋቁሞ የመብረር ብቃቱና በአካባቢ ብክለት እምብዛም አለመታማቱም ተመስክሮለታል፡፡
ኤርላንደር 10 ለመነሳትና ለማረፍ ሰፊ ማኮብኮቢያና የተመቻቸ የአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ የሚፈልግ አለመሆኑና በቀላሉ መንቀሳቀስ በሚችልበት መልኩ መሰራቱ ደግሞ፣ ከወታደራዊ አሰሳ ባለፈ በአደጋ ጊዜ የፈጥኖ ደራሽ ስራን ለማከናወን ተመራጭ አድርጎታል ብሏል ዘገባው፡፡

Read 2783 times