Print this page
Saturday, 28 March 2015 09:24

ኢቦላ እስከ ነሐሴ በቁጥጥር ስር ይውላል ተባለ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በሽታው እስካሁን ከ10 ሺ በላይ ሰዎችን ገድሏል

    ከአንድ አመት በፊት በምዕራብ አፍሪካ አገራት የተቀሰቀሰውና ከ10ሺህ በላይ ሰዎችን ለህልፈት እንደዳረገ የተነገረለት የኢቦላ ወረርሽኝ እስከ መጪው ነሐሴ ወር ድረስ ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥር ስር ይውላል ተብሎ እንደሚጠበቅ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማስታወቁን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
የተመድ የኢቦላ ምላሽ ግብረ ሃይል ሃላፊ ኢስማኤል ኦውልድ ቼክን ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በጊኒ የተከሰተውንና ወደ ሌሎች የምዕራብ አፍሪካ አገራት የተስፋፋውን የኢቦላ ቫይረስ ወረርሽኝ በቁጥጥር ስር በማዋል ረገድ፣ በመጀመሪያዎቹ የወረርሽኙ ወራት በተመድ የተሰሩት ስራዎች ያልተቀናጁና በእውቀት ላይ ያልተመሰረቱ ነበሩ፡፡
ይሄም ሆኖ ግን ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠት የሚደረጉት እንቅስቃሴዎች በሂደት እየተሻሻሉ መጥተዋል ያሉት ሃላፊው፤ ባለፈው አንድ አመት ኢቦላን ለመግታት በተደረገው እንቅስቃሴ ልምድ ቀስመናል፤ ወረርሽኙን እስከ መጪው ነሐሴ ወር ሙሉ ለሙሉ መግታት የሚቻልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል ብለዋል፡፡
የኢቦላ ቫይረስ ዳግም በወረርሽኝ መልክ እንዳይከሰት ለመከላከልና አፋጣኝ መፍትሄ ለመስጠት ሲባል፣ ራሱን የቻለ አለማቀፍ የኢቦላ ፈጣን ምላሽ ቡድን ለማቋቋም የሚያስችል ዕቅድ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት መውጣቱንም ዘገባው አስታውቋል፡፡
ድንበር የለሹ የሃኪሞች ቡድን በበኩሉ፤እስካለፈው ጥር ወር ድረስ በምዕራብ አፍሪካ አገራት በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ ቢመጣም፣ ከዚያ በኋላ አልቀነሰም፤ ወረርሽኙ ገና ሙሉ ለሙሉ አልተገታም ብሏል፡፡
የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚጠቁመው፣እስከያዝነው ሳምንት መጨረሻ ድረስ፣4ሺ 296 ላይቤሪያውያን፣ 3ሺ 742 ሴራሊዮናውያን፣ 2ሺ 261 ጊኒያውያን፣ 8 ናይጀሪያውያን፣ ስድስት ማሊያውያንና አንድ አሜሪካዊ በኢቦላ ሳቢያ ህይወታቸው አልፏል፡፡

Read 1509 times
Administrator

Latest from Administrator