Monday, 06 April 2015 07:44

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ 2ኛዋ ተፅዕኖ ፈጣሪ አገር ተባለች

Written by 
Rate this item
(5 votes)

የአፍሪካ ሀገራትን አጠቃላይ እንቅስቃሴና ተጨባጭ እውነታ በጥናት እየፈተሸ ደረጃ በመስጠት የሚታወቀው “አፍሪካ ክራድል” ድረገፅ፤ ሰሞኑን 10 ተፅዕኖ ፈጣሪ የአፍሪካ አገራትን ይፋ ያደረገ ሲሆን ኢትዮጵያ ከደቡብ አፍሪካ በመቀጠል ሁለተኛዋ ተፅዕኖ ፈጣሪ አገር ተብላለች፡፡ የሀገራቱ የተፅዕኖ ፈጣሪነት ደረጃ የተሠጠው በጦር ሃይል፣ በዲፕሎማሲ እና በአለማቀፍ ደረጃ ባላቸው እውቅና ሲሆን የመጀመሪያ ደረጃ የተሠጣት ደቡብ አፍሪካ በአህጉሪቱ ብቸኛ የ “ቡድን 20 እና የ “BRICS” አባል ሀገር እንዲሁም የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ቀዳሚ የንግድ ሸሪክ መሆኗ ለደረጃው አብቅቷታል ተብሏል፡፡
የደቡብ አፍሪካ ስም ሲነሳ የማንዴላ የአፓርታይድ ተጋድሎ አብሮ እንደሚነሣ የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ዛሬ በሀገሪቱ ለተገነባው ዲሞክራሲያዊ ስርአት የማንዴላና ተከታዮቻቸው የእነታቦ ኢምቤኪ አስተዋጽኦ የጐላ እንደሆነ ጠቁሟል፡፡
በተፅዕኖ ፈጣሪነት ሁለተኛ ደረጃ የተሠጣት ኢትዮጵያ፤ በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስሟ 44 ጊዜ ያህል መጠቀሱን፣ በታሪክ፣ ቅኝ ባለመገዛት፣ በጦር ሃይል፣ በፖለቲካና ዲፕሎማሲ ወደር የለሽ ታሪክና ተሞክሮ እንዳላት በማውሳት በዚህ ረገድ ከአፍሪካ አገራት የሚስተካከላት እንደሌለ ሪፖርቱ ጠቁሟል። አገሪቱ በአድዋ ጦርነት የተቀዳጀችውን ድል ተከትሎ ከ20 በላይ የሚሆኑ የአፍሪካ ሀገራት የኢትዮጵያን የባንዲራ ቀለማት በተለያየ ቅርፅና ይዘት ለመጠቀም እንደተገደዱ፣ የቡና የትውልድ አገር እንዲሁም፣ የሰው ዘር መገኛ መሆኗን፣ የራሷ የቀን አቆጣጠርና ፊደላት እንዳላትም የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ነዳጅ ሳይኖራት ከድህነት ለመውጣት የምታደርገው ጥረት ኢኮኖሚዋን በከፍተኛ መጠን እያሳደገው መሆኑን፣ በጦር ሃይልም ቢሆን ጠንካራ ሃይል ከገነቡ የአፍሪካ ሀገሮች ተጠቃሽ እንደሆነች አመልክቷል፡፡
ሀገሪቱ ለወደፊቱ በአለም ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራሉ ተብለው ተስፋ ከሚጣልባቸው የአፍሪካ ሀገራት አንዷ እንደምትሆንም ሪፖርቱ ተንብይዋል።
ከኢትዮጵያ ቀጥሎ ግብፅ በ3ኛ ደረጃ ተፅዕኖ ፈጣሪ ተብላለች፡፡ በርካታ የተማሩ ሰዎች አሏት የተባለችው ኬንያ 4ኛ ደረጃ ሲሰጣት፣ የአለማቀፍ ኩባንያዎች መቀመጫ የተባለችው ሞሮኮ 5ኛ፣ ቀዳሚ የኢኮኖሚና የሃይል ባለቤት የተባለችው ናይጄሪያ 6ኛ፣ ውጤታማ የኢኮኖሚ ገበያ ስርአት ባለቤት እንደሆነች የተነገረላት ኡጋንዳ 7ኛ፣ዜጎቿ ከእርስ በእርስ ግጭት ወጥተው በፍቅር ይኖሩባታል የተባለችው ሩዋንዳ 8ኛ፣ ህዝቧ ፈሪሃ አምላክ ነው የተባለችው ዚምባቡዌ 9ኛ ሲሆኑ በመጨረሻም የተረጋጋ የኢኮኖሚ ባለቤት የተባለችው አልጄሪያ 10ኛ ደረጃ ተሰጥቷል፡፡
 በአፍሪካ ተፅዕኖ ፈጣሪነት፡፡      

Read 4231 times